“በሰው ልጆች ህይወት ላይ ጠብ የሚል ለውጥ ማምጣት ነው”
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ
ያለፉት 7 የለውጥ ዓመታት የተለያዩ ውጣ ውረዶች የተስተናገዱባቸው ቢሆንም ከተማዋ አያሌ ስኬቶችን ያስመዘገበችበት እንደሆነ እሙን ነው። ከተማዋ በኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ዘርፎች ለሌሎች ከተሞች ተምሳሌት የሆኑ በርካታ እሴቶችን አንብራለች። ፕሮጀክቶችን በጥራት፣ በተያዘላቸው በጀትና የጊዜ ገደብ ውስጥ በማጠናቀቅ አዲስ የስራ ባህልን መፍጠር ችላለች፤ ለተለያዩ ማህበራዊ ችግሮች የተጋለጡ ዜጎችን ህይወት ማቃናትን ታሳቢ ያደረጉ የልማት ስራዎችም ከውናለች፡፡
ማህበራዊ ፍትሕን በማረጋገጥ ሂደት ውስጥ የጎላ ሚና ካላቸው ስራዎች መካከል ‘ለነገዋ’ የሴቶች ተሃድሶና ክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከል፣ ቀዳማይ የልጅነት እድገት፣ ገላን ጉራ የመኖሪያና የተቀናጀ የልማት መንደር፣ ጉለሌ የተቀናጀ የልማት ማዕከል፣ የግብርና ምርት መሸጫ ማዕከላት፣ የእሁድ ገበያ፣ ተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከላት፣ የተማሪዎች ምግባ መርሃ ግብር በሰው ልጆች ህይወት ላይ ተጨባጭ ልዩነት ያመጡ፤ በርካታ የከተማዋን ነዋሪዎች ህይወት ያስተካከሉ ናቸው፡፡ እነዚህ የልማት ስራዎች የሰዎችን ህይወት እያሻሻሉ ስለመሆናቸው ከተጠቃሚዎች አንደበትም ይሰማል፡፡
በተለምዶ ሽሮ ሜዳ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ አበበች ተፈራ በጉለሌ የተቀናጀ የልማት ስራዎች ውስጥ በእንጀራ ጋገራ ከተሰማሩ እናቶች አንዷ ናቸው፡፡ልጆቻቸውን ለማሳደግ ቅጠል ለቅመውና እንጨት ሰብስበው በጀርባቸው ተሸክመው በመሸጥ ሲተዳደሩ ለበርካታ ዓመታት መኖራቸውን አስታውሰው፣ በጉለሌ የተቀናጀ የልማት ስራዎች ውስጥ የተፈጠረላቸው የስራ ዕድል ‘ከጅብ ጋር ተጋፍቶ’ ከመኖር አውጥቶ በአዲስ የህይወት ጎዳና እንዲጓዙ እንዳስቻላቸው ገልፀዋል፡፡
ወይዘሮ አበበች፣ ከደቡብ ክልል ጋሞ ዞን ጨንቻ አካባቢ ከመጡበት ከ1972 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 2008 ዓ.ም ወገባቸው እስኪታመም ድረስ በእንጨት ለቃሚነት ህይወትን በስቃይ ሲገፉ መኖራቸውንም ጠቁመዋል። እንደ ወይዘሮ አበበች ሙሉ ቀን ጭራሮ እንጨት ለቅመው በየመንደሩ አዙረው በ60 እና በ70 ብር የሚሸጡት እናት ከድህነት ለመውጣት ከመቸገራቸውም በላይ እንጨቱ እየጠፋ፣ ክልከላውም እየበረታ ሲሄድ ከእድሜ መጫጫን ጋር ተስፋ መቁረጥ እየመጣ መሄዱም ሌላ ፈተና ነው፡፡
ለዓመታት ከቆዩበት የማገዶ እንጨት ለቀማና ሸክም መውጣታቸው ብቻ ሳይሆን ገቢያቸውን የሚያሳድግ ተስፋ መምጣቱ፣ “ነገ የተሻለ ህይወት ይኖረኛል” የሚል ተስፋን እንዳጫረባቸው ይናገራሉ። አክለውም “ከአንድም ሁለት ጊዜ በጅብ ከመበላት ድኛለሁ” የሚሉት እኝህ እናት፣ የእንጨት ለቀማ ስራ ማልዶ መውጣትን የሚጠይቅ በመሆኑ ሁለት ጊዜ ከጅብ መንጋ ጋር ፊት ለፊት ተፋጥጠው በሰዎች እገዛ መትረፋቸውን ነግረውናል፡፡

በጉለሌ ክፍለ ከተማ ተገንብቶ እንጦጦ አካባቢ ለሚኖሩ ወገኖች የተላለፈው ጉለሌ የተቀናጀ የልማት ስራዎች በአካባቢው እንጨት በመልቀም ለሚተዳደሩ 551 እናቶች የስራ እድል ተፈጥሮላቸዋል። የእንጀራ ማዕከሉ በውስጡ ሁለት የእንጀራ መጋገሪያ ህንጻዎች፣ የህጻናት ማቆያ፣ የእህል ማከማቻ፣ ወፍጮ እንዲሁም ልዩ ልዩ አገልግሎት የሚሰጡ ግንባታዎችን ያካተተ ነው፡፡ 551 እናቶች በሁለት ፈረቃ ተከፍለው እየሰሩበት ያለው ማዕከሉ 450 ዘመናዊ የእንጀራ መጋገሪያ ምጣድ የተገጠመለት፣ ዘመናዊ የሊጥ ማቡኪያ ማሽን፣ ዘመናዊ የአብሲት መጣያ ማሽንና ሁለት ወፍጮዎች ያሉት ነው፡፡
ከአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ጋር ቆይታ ያደረጉት የማህበራዊ ሳይንስ መምህር አንዋር ጫሚሶ፣ ባለፉት 7 ዓመታት በአዲስ አበባ ከተማ የተከናወኑ የልማት ስራዎች ጤናማ ማህበራዊ መስተጋብርን እውን ለማድረግ እንደሚያግዝ ተናግረዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ዜጎችን ታሳቢ ተደርገው ከተከናወኑ የልማት ስራዎች አንዱ ‘ለነገዋ’ የሴቶች ተሃድሶና ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል ነው፡፡ ማዕከሉ ለማህበራዊ፣ ለኢኮኖሚያዊ እና ለስነ ልቦና ስብራት የተጋለጡ ሴቶችን ካሉበት የህይወት ውጣ ውረድ እንዲወጡ በማድረግ፣ የስነ ልቦና ድጋፍ እና የሙያ ስልጠና በመስጠት ወደ ስራ በማሰማራት ላይ ይገኛል፡፡ በአንድ ጊዜ ከ2 ሺህ በላይ ሴቶችን ለማሰልጠን የሚያስችል ሲሆን፣ በዓመት እስከ 10 ሺህ ለሚደርሱ ሴቶች ስልጠና በመስጠት በዘላቂነት እንዲቋቋሙ፣ ገቢ እንዲያገኙና ራሳቸውን እንዲችሉ የሚያግዝ ነው፡፡ በ2ኛው ዙር ብቻ በ17 የሙያ አይነቶች የብቃት ምዘና ያለፉ 380 ሰልጣኞችን አስመርቆ የስራ እድል እንዲፈጠርላቸው አድርጓል፡፡
በማዕከሉ በጥልፍ ስራ የሰለጠነችው ወጣት እንግዳ አበባው፣ ከዚህ በፊት በአስከፊ የኑሮ ሁኔታ ውሰጥ እንደነበረች አስታውሳ፣ አሁን ላይ ማዕከሉ መሰረታዊ ፍላጎቶቿን ከማሟላት በተጨማሪ የሙያ ስልጠና ሰጥቶ በራሷ ለመቆም እዳስቻላት ተናግራለች፡፡ ወጣቷ በሰጠችው አስተያየት፣ ወደ ማዕከሉ ከመጣች ወዲህ የህይወት ክህሎት ስልጠና እንደ ወሰደችና ለወደ ፊት የህይወት ጉዞዋ መነሻ የሚሆኑ በርካታ ልምዶችን መቅሰሟን ተናግራ፣ ከዚህ ቀደም የነበሩባትን ሱሶች በመተው የተቃና የህይወት መስመር ውስጥ መግባቷን ገልፃልናለች፡፡
“ማንኛውም ሰው ድጋፍ ከተደረገለት መለወጥ እንደሚችል ግንዛቤ አግኝቻለሁ” የምትለው ወጣቷ፣ “ከእኔ ህይወት ብዙዎች መማር ይገባቸዋል” ብላለች፡፡ በሰለጠነችበት የሙያ መስክ ተሰማርታ ውጤታማ እየሆነች መሆኑንም ተናግራለች፡፡
በተመሳሳይ በማዕከሉ በልብስ ስፌት ሙያ የሰለጠነችው ፅጌረዳ ሽፈራው፣ ከዚህ ቀደም እንደዚህ አይነት የሙያ ስልጠና አግኝታ እንደማታውቅ ጠቁማ፣ አጋጣሚው ከአስከፊው የጎዳና ህይወት ከማላቀቅ አልፎ የቀጣይ ጊዜያ የህይወት ጉዞን መስመር የሚያስይዝ ስለመሆኑ ገልፃለች፡፡
‘ለነገዋ’ የሴቶች ተሃድሶና ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል በኮምፒዩተር ሙያ፣ በሞግዚትነት፣ በመስተንግዶ፣ በፀጉር ስራ፣ በኤሌክትሪክና ሸክላ ስራ፣ በእንጨት ስራዎች፣ በልብስ ስፌት እንዲሁም በሌሎች የሙያ ዘርፎች የሰለጠኑ ሴቶች የህይወት መስመራቸው እንደተስተካከለ ነው የሚያስረዱት፡፡
መምህር አንዋር እንደሚሉት ብልፅግናን ለማረጋገጥ እንደ ሀገር ከተቀመጡት የዘላቂ ልማት ግቦች መካከል አንዱ አካታች የሆነ እድገት ማምጣት ነው፡፡ ይህም ሴቶችን፣ አካል ጉዳተኞችን እና ሌሎች ለተለያዩ ማህበራዊ ችግሮች የተጋለጡ የህብረተሰብ ክፍሎችን ታሳቢ ያደረጉ የልማት ስራዎችን በመስራት ይረጋገጣል፡፡
ሌላኛው ሰው ተኮር ስራ ‘ተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከላት ማቋቋም ነው። በአሁኑ ጊዜ የእነዚህ ማዕከላት ቁጥር 24 እንደደረሰ መረጃዎች ያመላክታሉ። ማዕከላቱ በቀን አንድ ጊዜ መመገብ የማይችሉ ዜጎችን በመመገብ ተስፋቸውን አለምልመዋል፡፡

በተጨማሪም በየትምህርት ቤቶቹ በሚደረግ የተማሪዎች ምገባ መርሃ ግብር ከ835 ሺህ በላይ ተማሪዎች በቀን ሁለት ጊዜ የምገባ አገልግሎት እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡ በዚህም ተማሪዎች እና ወላጆች እፎይታን አግኝተዋል፡፡ በበጎ ፈቃድና በተለያዩ ተግባራት የአቅመ ደካሞችን ቤት በማደስና በተለያየ ጉዳዮች ችግር ውስጥ ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለማገዝ እየተሰሩ ያሉ ተግባራት ማህበራዊ ፍትህን በከተማዋ ማስፈን የሚያስችሉ እና መሰረታዊ ለውጥ እያመጡ ያሉ እንደሆኑ የማህበራዊ ሳይንስ መምህር አንዋር ተናግረዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ባለፉት 7 ዓመታት በከተማዋ ስለተከናወኑ ሰው ተኮር የልማት ስራዎች ዙሪያ በሰጡት ማብራሪያ፣ ሰባቱ የለውጥ ዓመታት በርካታ ስራዎች የተሰሩበትና ብዙ ተግዳሮቶችም የታለፉበት ነው ብለዋል። በጥቅሉ ለውጡ በርካታ ስኬቶችን አሳክቷል የሚል እምነት እንዳላቸው ጠቅሰው፣ “በተለይም የፖለቲካ ባህላችን ላይ የነበረውን ህመም አክሞ ስብራቶችን በመጠገን፣ የፖለቲካ ባህላችን እየተለወጠ የመጣበት፣ የኢኮኖሚያዊ ስብራቶች ከመሰረቱ መጠገን የጀመሩበትና መሰረት የተጣለበት ነው”፡፡
አዲስ አበባ ደግሞ የለውጡ ትልቅ መሳያ ናት ያሉት ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች፣ “ለውጡን ማየትና ማገናዘብ ለፈለገ ዋናና መሰረታዊ ማሳያ የምትሆነው አዲስ አበባ ናት፡፡ በከተማዋ የኢትዮጵያን ብልፅግና ለማሳካት የሚያስችሉ መሰረቶች ተጥለዋል፡፡ ለዚህም አንዱ ማሳያ የሥራ ባህላችን መቀየሩ ነው፤ ስምንት ሰዓት ሰርተን፤ የእረፍት ቀን እና በዓላትን ቆጥረን ለውጡን በፍጥነት ማሳካት ስለማይቻል ሌት ተቀን የመስራት አስፈላጊነት ላይ ታምኖበት ወደ ተግባር ተገብቷል”፡፡
ኢትዮጵያ በድህነት የተጎዳች ሀገር እንደመሆኗ የኢትዮጵያ ብልፅግና ማሳካት ለኢትዮጵያውያን ወሳኝ አጀንዳ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ክብራቸው የሚነካበት እና የሀገር ክብር የሚዋረድበት ሁኔታ ነበር፤ ከዚህ ዝቅታ ለመውጣት ከከተማዋ ነዋሪዎችና ከተለያዩ ባለድርሻ አካላትጋር በቅንጅት ለመስራት የተደረገው ጥሪ በጎ ምላሽ በማግኘቱ አዲስ አበባ ላይ የሀገርን መፃኢ ዕድል የሚያሳዩ መሠረታዊ ሥራዎች መስራት ተችሏልም ብለዋል ከንቲባ አዳነች፡፡
ብልጽግና ሲመሰረት በፖሊሲና በፕሮግራሙ ያጸደቀው ሰው ተኮር ስራዎችን እንደሆነ ከንቲባ አዳነች አውስተው፣ በመሆኑም የምንሰራው ለሰው ነው ብለዋል፡፡ አክለውም፣ “ሀገር ብናበለጽግ ለሰው ነው፡፡ ኢኮኖሚውን ብናሳድግ ለሰው ነው፡፡ የሰው ህይወት እንዲሻሻል፣ በምንሰራው ስራ አንዳች የሰው ህይወት ላይ ጠብ የሚል ለውጥ ማምጣት መቻል ነው ዓላማችን፤ ሰዎች ክብር እንዲያገኙ ነው፡፡ በእያንዳንዱ ስራችን ውስጥ ይህንን ታሳቢ ያደረገ ስራ ነው መስራት ያለብን የሚል ፕሮግራም አለ፡፡ የመጀመሪያው ደግሞ በተግባር የተገለጸውና የተተገበረው አዲስ አበባ ላይ ነው”፡፡
ከንቲባ አዳነች በማብራሪያቸው፣ የከተማዋ በጀት መጀመሪያ መዋል ያለበት የህጻናት ረሀብ ማስወገድ ብቻ ሳይሆን የነገ ትውልድ ግንባታ ለማረጋገጥ ነው ብለው፣ ይህ ውሳኔ የተወሰነው እንደ ፓርቲ ነው፡፡ በመሆኑም ወዲያው የከተማዋ በጀት ለተማሪዎች ምገባ ዋለ። አሁን ለ820 ሺህ ተማሪዎች በቀን ሁለት ጊዜ ምገባ ይደረጋል፡፡ ይህም የአዲስ አበባ እናቶችን አሳርፏል፡፡ ልጆች እኩልነት ተሰምቷቸዋል፡፡ አንድ አይነት ምሳ ይበላሉ፡፡ ምሳ እና ቁርስ ትምህርት ቤት ውስጥ ስላለ ማርፈድ የለም፡፡ በቁርስ ፍለጋ ወይም ቁርስ ባለመብላት ምክንያት የሚያረፍዱ ተማሪዎች የሉም ሲሉ ተናግረዋል፡፡
`ለነገዋ’ የሴቶች የታሃድሶና ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል ሲገነባ አዲስ አበባ ውስጥ ህጻናት ልጆች ሳይቀር ለሴተኛ አዳሪነት መንገድ ላይ የሚቆሙበት ነበር ያሉት ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች፣ በራሳቸው ጥፋት ባልሆነ፣ ማህበረሰቡ ውስጥ ስር በሰደደ የአስተሳሰብ መዛባት፣ የኢኮኖሚ እና የማህበራዊ ስብራት አንዳንዶቹ በዚያ ምክንያት የሚገኘውን ገቢ እንኳን ለራሳቸው የማያገኙበት፣ ሰው ሲነግድባቸው የነበሩ ነበሩ፡፡ ይህንን ማህበራዊ ቀውስ ለማቃለል ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ሆኖ ነው የተገኘው፡፡ ስለዚህ በርካታ እህቶቻችን በክብር ወደ ማዕከሉ ገብተው ተምረው፣ ሰልጥነው ውስጣቸው ያለውን ችሎታ እና የመለወጥ ፍላጎት ወደ ውጤት ለመለወጥ የቻሉበትን በር የከፈተ ነው፡፡ ከሚደርስባቸው ትልቅ ጫና እና ጥቃት አረፍ የሚሉበትን፣ ተስፋ የሚሆናቸውን ቤት እንዲያገኙ ያደረግንበት ነው ብለዋል፡፡
በበጎ አድራጎት በርካታ ባለሃብቶችን አስተባብረን፣ መሬት አዘጋጅተን፣ መሰረተ ልማቶችን አዘጋጅተን ለአቅመ ደካሞች፣ ለሀገር ባለውለታዎች፣ ቤት ለወደቀባቸው፣ የድሮ የቀበሌ ቤት ለፈራረሰባቸው ወደ 38 ሺህ የመኖሪያ ቤቶችን ገንብተን ሰጥተናል፡፡ ቤቱ መጸዳጃቤት ያለው፣ ውሃ ቤት ውስጥ ማግኘት የሚችሉበት ሁኔታ መፍጠር ተችሏል፡፡ በርካታ የዘመሙ ጎጆዎችን ያቀናንበት በዚህ የለውጥ ዘመን ነው ማለት ይቻላል፡፡ ይህ የፍትሐዊነት ጉዳይ ነው፡፡ ሰው ተኮርነታችን ደግሞ ያረጋገጥንበት እሳቤ ነው ሲሉም በማብራሪያቸው አፅንኦት ሰጥተውበታል፡፡
የማህበራዊ ሳይንስ ምሁሩ አቶ ሶፎንያስ ፍስሃ ከተማዋ በተስፋ ብርሃን እና በተማሪዎች የምገባ መርሃ ግብር፣ በቤቶች ዕድሳት እና ለተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎች በሚዘጋጁ የማገገሚያ ማዕከላት የተጋላጭ ወገኖችን ተጠቃሚነት ማረጋገጡን ገልፀዋል። አክለውም በተለያዩ መልኮች ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን ዜጎች ታሳቢ ተደርጎ የተገነቡ የልማት ማዕከላት ማህበራዊ ፍትሕን ለማረጋገጥ ከሚደረጉ ጥረቶች መካከል ተጠቃሽ ናቸው፤ የዜጎችን እምባ ከማበስ አንፃርም ጠቀሜታቸው ጉልህ ነው ብለዋል፡፡
እነዚህ ተግባራት በሀገሪቱ ያለውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ጤናማ ለማድረግ ያላቸው አበርክቶ ትልቅ በመሆኑ መንግስት ከሚያደርገው ጥረት በተጨማሪ ባለሀብቶች እና ሁሉም ዜጋ የሚችለውን ድጋፍ በማድረግ ሊረባረብ ይገባል፡፡ መንግስት የበጎ ፈቃድ ስራውን በበላይነት እየመራ ሲሆን ማህበራዊ ኃላፊነትን ከመወጣት አንፃር እነዚህን ጅምሮች አጠናክሮ ማስቀጠል ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
አዲስ አበባ የዲፕሎማሲ ከተማ በመሆኗ ገፅታዋን ከመገንባት አንፃር የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ማጥበብ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ደግሞ የሁሉንም ጥረት ይጠይቃል፡፡ በዋናነት ግን ሰው ኢኮኖሚውን እንዲያሳድግና በአቅሙ ልክ ቤተሰቡን እንዲመራ ትምህርት ላይ መስራት ያስፈልጋል፡፡ እንደ አዲስ አበባ ከተማ ግን በተለያዩ ዘርፎች ማህበራዊ ፍትህን ለማንገስ እየተሰሩ ያሉ ተግባራት የሚበረታቱ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
በጋዜጣዋ አዘጋጆች