ዓድዋ ድል የኅብረ-ብሔራዊነት ካስማ፣ የጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ዓርማ ነው!-የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

You are currently viewing ዓድዋ ድል የኅብረ-ብሔራዊነት ካስማ፣ የጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ዓርማ ነው!-የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

AMN-የካቲት 22/2017 ዓ.ም

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ለ129ኛው የዓድዋ ድል በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፈ፡፡

የመልዕክቱ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

ዓድዋ ድል የኅብረ-ብሔራዊነት ካስማ፣ የጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ዓርማ ነው!

መላው ኢትዮጵያዊያን እንኳን ለ129ኛው የዓድዋ ድል በዓል በሰላም አደረሳችሁ!

ዘንድሮ “ዓድዋ የጥቁር ሕዝቦች ድል!” በሚል መሪ ቃል 129ኛው የዓድዋ ድል በዓል በሀገር ዓቀፍ ደረጃ፣ በሁሉም ክልሎች፣ በከተማ አስተዳደሮች በተቋማት፣ በመላው ዓለም በሚገኙ ኤምባሲዎች እና ቆንስላ ፅ/ቤቶች በኢ.ፌ.ዲ.ሪ የሀገር መከላከያ ሚኒስቴር አስተባባሪነት ይከበራል።

ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷን ለማስከበርና የሕዝቦቿን አንድነት ለማስጠበቅ በተለያዩ የዘመን አጋጣሚዎች ወረራ የፈፀሙባትን የውጭ ወራሪ ኃይሎች በመፋለም በበርካታ አውደ ውጊያዎች ላይ ተደጋጋሚ የሆኑ ሀገርን ያፀኑና ያስቀጠሉ ታሪካዊ ድሎችን ተጎናፅፋለች፡፡

ከእነዚህ ድሎች አንዱና ወሳኙ የሀገራችን ብቻ ሳይሆን የመላው ጥቁር ሕዝቦች ድል የሆነው የዓድዋ ድል ነው፡፡ ዓድዋ የኢትዮጵያ ከፍታ የታየበት፤ የቅኝ ገዥዎች ሕልም የከሸፈበት የመላው ጥቁር ሕዝቦች ድል ነው፡፡

የበርካታ ጀግኖች እና አርበኞች መፍለቂያ ምድር የሆነችው ሀገራችን ኢትዮጵያ በየዘመኑ የተቃጡባትን ትንኮሳዎችና ወረራዎች በመመከት የአፍሪካ የነጻነት ቀንዲል ሆና ዘልቃለች፡፡ በዓድዋ ተራሮችም የተፈፀመው ይሄው ክስተትና እውነታ ነው፡፡

በዓድዋ ጦርነት የነጮች የበላይነት አስተሳሰብ ከስር መሠረቱ የተናደበት እና ጥቁር ሕዝቦች በአጥንታቸውና በደማቸው ደማቅ ታሪክ መጻፍ እንደሚችሉ በተግባር ያረጋገጠ የድላችን ጌጥና ፈርጥ ነው፡፡

ዓድዋ በኅብር የተገኘ፣ የፀናች ኅብረ-ብሔራዊ ሀገርን ለመፍጠር መሠረት የጣለ የትውልዱ ዐሻራ ነው፡፡ የይቻላል ተምሳሌት፣ የአይበገሬነት መሠረት የሆነው የዓድዋ ድል ሁሉም ኢትዮጵያዊያን በአንድነት ተሰልፈው በደማቸውና አጥንታቸው የፃፉት የወል ታሪካችንና የነጻነት ሓውልታችን ነው፡፡

የዓድዋ ድል ከእኛም አልፎ የነፃነት ንቅናቄዎች እንዲቀጣጠሉ ያደረገ፣ የፓንአፍሪካኒዝም ዕሳቤን የፈጠረ የታሪክ ማህደር ነው፡፡ ለዚህም ነው ዓድዋ የኅብረ-ብሔራዊነት ካስማና የጥቁር ሕዝቦች የነፃነት አርማ ነው የምንለው፡፡

የዓድዋ ድል ሉዓላዊነታችንን ያስከበርንበት፤ ወራሪ ጠላትን ያሳፈርንበት ታላቅ ድል ከመሆኑም ባሻገር በርካታ የምንማርባቸው ቁም ነገሮችን ያዘለ ድል በመሆኑ እየዘከርንና ታሪኩን በልኩ እያወሳን ለቀጣይ ትውልድ ማሻገር የዛሬው ትውልድ ኃላፊነት ነው፡፡

ከቀደሙት ጀግኖች አያቶቻችን የተረከብናትን ሉዓላዊት ኢትዮጵያ አንድነቷ የተጠበቀ፤ ሰላሟ የተረጋገጠና የፀናች ሀገርን ለትውልድ የማሻገር ግዴታ አለብን፡፡

አሁን የሚስተዋሉ ፈተናዎች በውል በመገንዘብ ጊዜው የሚጠይቀውን የሰላም፣ የልማት እና በሁሉም መስክ የተጀመሩ የለውጥ ሥራዎችን በማሰቀጠል የበለፀገች፣ ከልመና የተላቀቀች፣ የምግብ ሉዓላዊነቷን ያረጋጠች ኢትዮጵያን በመገንባት የዓድዋ ጀግኖች ልጆች መሆናችንን ዳግም ማሳየት ይኖርብናል፡፡

የዓድዋ ጀግኖች ወራሽ የሆነው የሀገር መከላከያ ሠራዊታችን ያጋጠሙን ፈተናዎችን በድል እየተወጣ፣ የዚህ ትውልድ ዓድዋ የሆነውን ታላቁ የሕዳሴ ግድባችንን ደህነት እያረጋገጠ፣ ኢትዮጵያን እያፀና የዓድዋ ጀግኖች ወራሽ መሆኑን አረጋግጧል፡፡ በመሆኑም የዓድዋ የድል በዓልን ስናከብር ጀግናው ሠራዊታችን ለሀገራችን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት መከበር ከጥንት እስከ ዛሬ የሚከፍለውን ውድ መስዋዕትነት በመዘከር ሊኾን ይገባል፡፡

እኛም ልክ እንደ ጀግናው ሠራዊታችን በተሰማራንባቸው የሥራ መስክ ሁሉ ተግተን በመሥራት የጀመርነውን የብልጽግና ጉዞ ከግቡ በማድረስ የዓድዋን ድል መድገም ይጠበቅብናል፡፡

የዓድዋን የድል ምስጢርና ታሪክ በመማር፣ በመውረስና ለትውልድ በማሻገር በቀጣይ ተጨማሪ ድሎች ለማስመዝገብ ቃላችን በተግባር፣ ተግባራችን ደግሞ ባህል የምናደርግበት ወቅት ሊሆን ይገባል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review