ሩሲያ በዩክሬን ዋና ከተማ ኬቭ በሰነዘረችው የጅምላ ሚሳኤል እና የሰው አልባ አውሮፕላኖች ጥቃት 23 የሚጠጉ ሰዎች መሞታቸውንና ከ100 በላይ የሚሆኑ መቁሰላቸውን የዩክሬን ባለስልጣናት ገለፁ።
በሰው አልባ አውሮፕላኖች አማካኝነት በአፓርታማዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን የገለፁት የዩክሬን የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር፤ ዩክሬን በ440 ሰው አልባ አውሮፕላኖች እና 32 ሚሳኤሎች መመታቷን አስታውቀዋል።
ትናንት ለሊቱን የተሰነዘረው ጥቃት የሩሲያ – ዩክሬን ጦርነት ከጀመረ ወዲህ በኬቭ ላይ ከተሰነዘሩ ጥቃቶች ከትላልቆቹ እንደሚመደብ የተነገረ ሲሆን ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ ከአሰቃቂዎቹ ጥቃቶች መካከል የሚመደብ ሲሉ ገልፀውታል።
ጥቃቱ ከደረሰባቸው 27 ቦታዎች መካከል አፓርታማዎች የሚገኙ ሲሆን ነፍስ አድኖች እስካሁንም እያገኟቸው ካሉ አስከሬኖች ጋር ተያይዞ የሟቾች ቁጥር እስካሁን በትክክል አልታወቀም።
ዩክሬን በበኩሏ ጥቃቶችን ወደ ሩሲያ የሰነዘረች ሲሆን 10 ሰዎች መቁሰላቸውን የሩሲያ ባለስልጠዓናት አስታውቀዋል።
147 የዩክሬን ሰው አልባ አውሮፕላኖችም በሩሲያ ክልሎች ተመተው መክሸፋቸውን የሩሲያ የዜና አውታሮች ዘግበዋል።
ዘለንስኪ በካናዳ ከተካሄደው የቡድን 7 አባል ሃገራት ስብሰባ ጎን ለጎን የአሜሪካ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕን ለማነጋገር እቅድ የነበራቸው ቢሆንም የአሜሪካው ፕሬዝደንት ቆይታቸውን አሳጥረው ወደሃገራቸው በመመለሳቸው እቅዳቸው መደናቀፉ በዘገባው ተካቷል።
በሊያት ካሳሁን