
ኢትዮጵያ እና ፈረንሳይ ዘመናትን ያስቆጠረ የሁለትዮሽ ግንኙነት አላቸው፡፡ ከ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በፊት የተጀመረው የሀገራቱ ወዳጅነት ወደ መደበኛ ዲፕሎማሲዊ ግንኙነት የተሸጋገረበት 125ኛ ዓመት በ2014 ዓ.ም ተከብሮ ነበር፡፡
በወቅቱ ሀገራቱ በሳይንስ እና ቴክኖሎጂ፣ በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በትራንስፖርት፣ በህክምና፣ በግብርና፣ በቅርስ ጥበቃ እና በሌሎች ዘርፎች ያላቸውን ትብብር ይበልጥ ለማሳደግ እንዲሁም የህዝብ ለህዝብ ትስስራቸውን ለማጠናከር መስማማታቸው ይታወሳል።
ሀገራቱ ባለፉት ዓመታት በመሪዎች ደረጃ ያደረጓቸው ጉብኝቶችም ይህን ስምምነት ዕውን ለማድረግ ትልቅ አቅም መፍጠራቸው ይታመናል።
ከሰሞነኛው
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በፈረንሳይ ፓሪስ በቴክኖሎጂ እና በአርቴፊሻል ኢንተሊጀንስ ላይ ያተኮረ የኢንዱስትሪ ጉብኝት አድርገዋል።
በጉብኝታቸው ‘ስቴሽን ኤፍ’ የተሰኘውን በዓለም ትልቁን የግል የቴክኖሎጂ ስታርት አፕ የቢዝነስ መፍጠሪያ ማዕከልን፣ የኖኪያ-ፈረንሳይ ዋና መሥሪያ ቤትን እንዲሁም ታሌ የተሰኘ የምርምር እና የቴክኖሎጂ ማዕከልን ተመልክተዋል፡፡
የተቋማቱ ተሞክሮ ገና በጅምር ላይ ለሚገኘው የኢትዮጵያ ስታርት አፕ እንዲሁም ሀገሪቱ በ5ኛ እና 6ኛ ትውልድ የኢንተርኔት አገልግሎት፣ በሳይበር ደኅንነት፣ በአርቴፊሻል ኢንተሊጀንስ እና በኦፕቲካል ትስስር መስኮች አቅሟን ለማደርጀት ለምታደርገው ጥረት ከፍያለ እገዛ ይኖረዋል።
ምልሰት (ጥቅምት 2011 ዓ.ም)
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከ6 ዓመታት በፊት ፈረንሳይን ጎብኝተው ነበር፡፡ ጉብኝቱ ኢትዮጵያ እና ፈረንሳይ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ከማጠናከር ባለፈ በባለ ብዝሃ ወገን መድረኮች ያላቸውን ትብብር ለማጎልበት የተስማሙበት እንዲሁም ሽብርተኝነትን እና የአየር ንብረት ለውጥን በጋራ ለመዋጋት የቆረጡበት ሆኖ ይታወሳል፡፡
ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የፈረንሳይ ጉብኝት ከ6 ወር በኋላ በኢትዮጵያ የሁለት ቀናት የሥራ ጉብኝት ያደረጉት የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ፤ በኢትዮጵያ ቆይታቸው ሀገራቱ የተለያዩ ስምምነቶችን ተፈራርመዋል።
ከእነዚህም ውስጥ የኢንቨስትመንት፣ የመከላከያ እና የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ዕድሳት ድጋፍ ይጠቀሳል፡፡ ፕሬዚዳንቱም በወቅቱ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን ጎብኝተውም ነበር፡፡
ምልሰት (ሰኔ 2015 ዓ.ም)
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በወርኃ ሰኔ 2015 ዓ.ም በፈረንሳይ ፓሪስ ከተካሄደው አዲስ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ስምምነት ጉባኤ ጎን ለጎን ከሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ጋር በተለይም የንግድ እና ኢንቨስትመንት ትብብርን ማጎልበት ላይ መክረዋል፡፡
ጉባኤው ላይም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኢትዮጵያ አልፎ በአፍሪካ እና በሌሎች የዓለም ክፍሎች የሚገኙ ታዳጊ ሀገራት በፋይናንስ ስርዓት ላይ እያጋጠማቸው የሚገኘውን ጫና በተመለከተ ንግግር አድርገው ነበር።
ምልሰት (ታህሳስ 2017 ዓ.ም)
ፕሬዚዳንት ማክሮን በታህሳስ ወር በኢትዮጵያ በነበራቸው የ1 ቀን ኦፊሴላዊ ጉብኝት በሁለቱ ሀገራት የጋራ ትብብር እንዲሁም በቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ መወያየታቸው ይታወሳል።
መሪዎቹ በፈረንሣይ ድጋፍ በኢትዮጵያ የሚከናወኑ ዓበይት የልማት ሥራዎችን በጋራ ገምግመው ነበር።
በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እድሳት የተደረገለት ብሔራዊ ቤተ-መንግሥት አሁን የደረሰበትን ውብ ገፅታ እንዲላበስ የአንበሳውን ድርሻ የሚወስዱት ፕሬዝዳንት ማክሮን ስለመሆናቸው ገልጸው ስለመልካም ወዳጅነታቸው አመስግነዋቸው ነበር።
ሀገራቱ በሲቪል አቪዬሽን፣ በአየር ትራንስፖርት እና መሰረተ ልማት ዘርፎች ያላቸውን ትብብር ለማሳደግ እየሰሩ ይገኛሉ።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነውን ኤር ባስ ኤ350-1000 የመንገደኞች አውሮፕላን ከወራት በፊት ከፈረንሳዩ ኤር ባስ ኩባንያ መረከቡም ይታወሳል።