ዘመናዊ መንገዶቹ የትራፊክ ፍሰቱን ምን ያህል እያገዙት ነው?

You are currently viewing ዘመናዊ መንገዶቹ የትራፊክ ፍሰቱን ምን ያህል እያገዙት ነው?

የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን የከተማውን የመንገድ መሰረተ ልማት ከማሟላት አኳያ ባለፉት ዓመታት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ ጥቅም ላይ አውሏል፡፡ በየጊዜው የሚገነቡት መንገዶች የትራፊክ ፍሰቱን ከማሳለጥ ባሻገር የከተማዋን ገፅታ በመቀየርና የመንገድ ሽፋኑን  በማሳደግ ረገድ  ትልቅ አስተዋፅኦ አበርክተዋል፡፡

ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በ2017 በጀት ዓመት በአጠቃላይ አሥር መንገዶችና ሁለት ድልድዮችን በመገንባት ለአገልግሎት ክፍት ያደረገ ሲሆን፤ ከነዚህ ውስጥ ስምንቱ ፕሮጀክቶች በራስ ሀይል የተገነቡ እና አራት በስራ ተቋራጮች አማካኝነት የተገነቡ ናቸው፡፡

 በአጠቃላይ ከ 6 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ተጠናቅቀው ለአገልግሎት ክፍት የተደረጉ ሲሆን እነዚህ የመንገድ ፕሮጀክቶች 33 ነጥብ 9 ኪሎ ሜትር ርዝመትና በአማካይ ከ10 እስከ 50 ሜትር የጎን ስፋት አላቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ከ530 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ አንድ ዘመናዊ የተሽከርካሪና መሣሪያዎች ጥገና ማዕከል ገንብቶ ለአገልግሎት አብቅቷል፡፡

ግንባታቸው ተጠናቅቆ ለአገልግሎት የበቁት የመንገድ ፕሮጀክቶች አዳዲስና ነባር መንገዶችን ደረጃ ለማሻሻል ታሳቢ ተደርገው የተገነቡ በመሆናቸው በከተማዋ የሚስተዋለውን ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ ችግር በማቃለል ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ። በተጨማሪም ከዋና መንገዶች ጋር በቀላሉ ሊያገናኙ የሚችሉ አቋራጭ እና አማራጭ መንገዶች በመሆን አገልግሎት መስጠት የሚችሉ ናቸው፡፡

በዓመቱ ተጠናቅቀው ለአገልግሎት የበቁት መንገዶች ከቃሊቲ አደባባይ ቱሉ ዲምቱ፣ ቃሊቲ-ቂሊንጦ፣ ከአውጉስታ-ወይራ፣ ከአፍሪካ ህንፃ-ጀሞ መስታወት ፋብሪካ መንገድ፣ የቂርቆስ ማርገጃ -ቡልጋሪያ መንገድ፣ ከቤላ መንገድ-ፈረንሳይ ፓርክ፣ ፈረንሳይ ኤምባሲ-አቦ ቤተ ክርስቲያን መንገድ፣ ከናሳው ሪል ስቴት-አርሴማ ቀለበት መንገድ፣ ከቱሉ ዲምቱ ኮንዶሚኒየም መቃረቢያ አስፋልት መንገድ፣ በሻሌ ኮንዶሚኒየም የውስጥ ለውስጥ መንገድ፣ ከዮናስ ሆቴል-ኬብሮን ፋርማሲ ሲሆኑ በተጨማሪም ማዘር ቴሬዛና በላይ ዘለቀ/አጣሪ/ ድልድዮች ሲሆኑ እኛም ከማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታቸው አንፃር የተወሰኑትን ትላልቅ መንገዶች ለማሳያነት እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡

ከቃሊቲ አደባባይ ቱሉ ዲምቱ መንገድ

የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን ካስገነባቸው ትላልቅ የመንገድ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ የሆነው ከቃሊቲ አደባባይ ቱሉ ዲምቱ መንገድ 90 በመቶ የሚሆነው የሀገሪቱ ወጪ እና ገቢ ዕቃዎች የሚተላለፉበት መንገድ እንደመሆኑ መጠን የሀገሪቱን ንግድ በማቀላጠፍ የሀገሪቱን ህዝቦች የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ረገድ ጉልህ ድርሻ  እንዳለው ይታመናል፡፡ ግንባታው ሚያዝያ 2009 ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን 11 ነጥብ 2 ኪሎ ሜትር አጠቃላይ ርዝመትና 3 ሜትር የእግረኛ መንገድን ጨምሮ 50 ሜትር የጎን ስፋት ያለው ነው፡፡ መንገዱ በተጨማሪም አደባባይና ማሳለጫ ድልድዮችንም በውስጡ የያዘ ነው፡፡    

የቃሊቲ ማሰልጠኛ ቀለበት መንገድ አደባባይ

የቃሊቲ – ቱሉዲምቱ አደባባይ የመንገድ ፕሮጀክት ግዙፍነት አጉልተው ከሚያሳዩ የግንባታ ገፅታዎች መካከል የቃሊቲ ማሰልጠኛ ቀለበት መንገድ መጋጠሚያ ላይ የተገነባው ይህ  የመጀመሪያው ማሳለጫ ድልድይ 240 ሜትር ርዝመት አለው፡፡ 

የማሳለጫ ድልድዩ የቀድሞውን የቀለበት መንገድ አደባባይ ሳይነካ በቁመት ከፍ ብሎ የተገነባ በመሆኑ የትራፊክ እንቅስቃሴውን ከማሳለጡ ባሻገር ለአካባቢው ገፅታም ልዩ ውበት የሚያላብስ ነው፡፡

ጥሩነሽ ቤጂንግ  ሆስፒታል ማሳለጫ ድልድይ

ይህ የማሳለጫ ድልድይ 90 ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን፤ ከሥር ወደ አቃቂ ከተማ ለመግባትና ለመውጣት ሲያገለግል፤ ከላይ ደግሞ በቀጥታ ወደ ቱሉ ድምቱ እና ቃሊቲ አደባባይ በግራና ቀኝ የሚተላለፈውን የትራፊክ ፍሰት በሚገባ የሚያሳልጥ ነው፡፡

ጋሪ ድልድይ

ሦስተኛውና የመጨረሻው የትራፊክ ማሳለጫ ተሸጋጋሪ ድልድይ ቀደም ሲል ጋሪ ድልድይ እየተባለ በሚጠራው ሥፍራ ላይ የተገነባው ሲሆን 50 ሜትር ርዝመት እና 20 ሜትር የጎን ስፋት እንዲኖረው ተደርጎ በአዲስ መልክ የተገነባ ነዉ፡፡

የዚህን መንገድ ግንባታ የቻይና ኮሚኒኬሽን ኮንስትራክሽን ካምፓኒ ከ2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ያከናወነው ሲሆን ኢንጂነር ዘውዴ አማካሪ ድርጅት ደግሞ የማማከርና ቁጥጥር ስራውን አከናውኗል፡፡

የቃሊቲ-ቂሊንጦ መንገድ

መጋቢት 2009 ዓ.ም ግንባታው የተጀመረው የቃሊቲ-ቂሊንጦ መንገድ  10 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር ርዝመትና 50 ሜትር የጎን ስፋት ያለው ሲሆን፤ 5 ድልድዮችን አካትቶ የተገነባ መንገድ ነው። ከድልድዮቹ መካከል ሁለቱ ወንዝ ተሻጋሪ ድልድዮች ሲሆኑ ሦስቱ ደግሞ መንገድ ተሻጋሪ ድልድዮች ናቸው።

● የመጀመሪያው ድልድይ በቡልቡላ ወንዝ ላይ የተገነባው እና 175 ሜትር ርዝመት እና በግራና በቀኝ መተላለፊያው በኩል 34 ሜትር የጎን ስፋት ያለው ነው።

● የቡልቡላ ወንዝን አቋርጦ የሚያልፈው ይህ ድልድይ ከታች ወደ ላይ 30 ሜትር የሚረዝም ከፍታም አለው፡፡

● ሁለተኛው ወንዝ ተሻጋሪ ድልድይ በትልቁ የአቃቂ ወንዝ ላይ የተገነባው ሲሆን 325 ሜትር ርዝመት አለው።

● የትልቁ አቃቂ ወንዝ ድልድይ 42 ሜትር ከፍታ ያለው ሲሆን፣ እያንዳንዱ የድልድዩ ምሰሶ ከመሬት በታች እስከ 30 ሜትር በሚደርስ ጥልቀት መሠረት የተገነባ ነው፡፡

ቀሪዎቹ ሦስት የመንገድ ተሻጋሪ ድልድዮች በፕሮጀክቱ የተለያየ ስፍራዎች ላይ የተገነቡ ሲሆን፣ቂሊንጦ አካባቢ በሚገኘው ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ በሚገኙት መንገዶች በላይ ተሻግረው የሚያልፉ እና ወደ ውጨኛው የቀለበት መንገድ ጋር የሚያሻግሩ ናቸው፡፡

2 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ወጪ የሆነበትን ይህ መንገድ የገነባው የቻይና ኮንስትራክሽን ኮሙኒኬሽን ካምፓኒ ሲሆን ሀይ ዌይ ኢንጂነርስ እና ኮንሰልታንት ፕሮጀክቱን በማማከር ተሳትፏል፡፡

ይህ መንገድ የከተማዋን የኢንዱስትሪ ፓርክ በመንገድ መሠረተ-ልማት የሚያስተሳስርና በቱሉዲምቱ የክፍያ መንገድ አቅጣጫ ወደ ከተማዋ ለሚገቡና ለሚወጡ ተሸከርካሪዎች የወጪ ገቢ ኮሪደር ሆኖ የሚያገለግል ዋና መንገድ በመሆኑ በቃሊቲ ቱሉ ዲምቱ መንገድ ላይ የሚኖረውን የትራፊክ ጫና እንደሚያቃልል ይታመናል። በተጨማሪም የቂሊንጦ ኢንዱስትሪ ፓርክን ጨምሮ ለሌሎች ኢንዱስትሪዎች ጥሬ ዕቃዎችን በወቅቱ ለማቅረብና ምርትና አገልግሎቶችን ለአካባቢው ማህበረሰብ  ለማድረስ ይረዳል፡፡

በተጨማሪም የቃሊቲ – ቂሊንጦ መንገድ ፕሮጀክት፤ የውስጠኛውን ቀለበት መንገድ ከውጪ ጋር በቀጥታ በማስተሳሰር በአካባቢው ቀልጣፋ የትራፊክ ፍሰት እንዲኖር ከማስቻሉም በተጨማሪ በኮዬ ፈጬ እና አካባቢው ባሉ የጋራ መኖሪያ መንደሮችና በዙሪያው ያሉ ነዋሪዎች በአቋራጭ ወደ መሃል ከተማ እንዲጓጓዙ የሚያስችል ሌላው የደቡብ አዲስ አበባ ክፍል አዲስ የመንገድ ኔትወርክ አካል ነው፡፡

የአውጉስታ – ወይራ መንገድ

የትራፊክ ፍሰቱን በተገቢው መንገድ ማስተናገድ የማይችለው ነባሩ የአውጉስታ ወይራ መንገድ የከተማውን ማስተር ፕላን በጠበቀ መልኩ እንደ አዲስ ተገንብቶ ለአገልግሎት ክፍት ተደርጓል። 1 ነጥብ 4 ኪሎ ሜትር ርዝመትና 20 ሜትር የጎን ስፋት ያለው ይህ የመንገድ ግንባታ ስራ በሁለት ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ ተጠናቅቆ ለምረቃ በቅቷል፡፡

መጋቢት 2012 ዓ.ም ግንባታው የተጀመረው ይህ መንገድ ቲኤንቲ ኮንስትራክሽን ከ308 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የገነባው ሲሆን፤ ኦሜጋ ኮንሰልቲንግ አማካሪ ድርጅት ደግሞ የማማከር እና የቁጥጥር ስራውን  ተከታትሎታል፡፡

መንገዱ ከጦር ሀይሎች ወደ ቶታል የሚወስደውን የውጪ ቀለበት መንገዱ በመያዝ በአውጉስታ  ወደ ወይራ፣ ቤተል አደባባይ፤ እንዲሁም ከአውጉስታ በወይራ መጋጠሚያ ወደ ዘነበ ወርቅና አየር ጤና አደባባይ ለመሄድ አማራጭ መንገድ በመሆን የሚያገለግል ነው፡፡     

ከአፍሪካ ህንፃ- ጀሞ መስታወት ፋብሪካ መንገድ

በተለምዶ አፍሪካ ህንፃ ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ ጀምሮ እስከ ጀሞ መስታወት ፋብሪካ የሚደርሰው መንገድ 1 ነጥብ 6 ኪ.ሜ ርዝመትና 20 ሜትር የጎን ስፋት ያለው ሲሆን፤ ግንባታው በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የራስ ኃይል ነው የተከናወነው፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎች እንደሚናገሩት መንገዱ እና የመንገዱ አካል የሆነው ድልድይ ከመገንባቱ በፊት ጠጠር የእግረኛ መንገድ ብቻ የነበረ ሲሆን፤ በተለይ በክረምት ወቅት አካባቢው በጎርፍ ይጥለቀለቅ እና ለችግር ይዳረጉ ነበር፡፡ በተለይ ደግሞ የጀሞ ወንዝ በሚሞላበት ወቅት ድልድይ ባለመኖሩ ለመሻገር ይቸገሩ እንደነበር የአካባቢው ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡ አሁን ግን  በአንድ በኩል መንገድ በመሰራቱ በሌላም በኩል ከ9 ሜትር በላይ ርዝመት ያለው ድልድይ በመገንባቱ ችግራቸው እንደተቃለለ ይናገራሉ፡፡

ይህ መንገድ ከአየር ጤና አደባባይ ወደ ጀሞ ሦስት መሄድ ለሚፈልጉ አሽከርካሪዎች ሚካኤል አደባባይ ሳይደርሱ የቀለበት መንገዱን የዳር መስመር በመያዝና ወደ ቀኝ በመታጠፍ በቀጥታ በጀሞ መስታወት ፋብሪካ በኩል ወደ ጀሞ ሦስት አደባባይ ለመውጣት ያስችላቸዋል፡፡ በኢትዮጵያ  ኮንስትራክሽን ዲዛይንና ሱፐርቪዥን ሥራዎች ኮርፖሬሽን አማካሪነት በባለስልጣኑ የራስ ሀይል መንገድ ግንባታ ሎት 1 በታህሳስ 2013 ዓ.ም የተጀመረው ይህ መንገድ ለግንባታው 94 ሚሊዮን 849 ሺህ 437 ብር ወጪ የተደረገበት ሲሆን፤ ግንባታው ሙሉ በሙሉ ተጠናቅቆ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review