
AMN – ታኅሣሥ 09/2017 ዓ.ም
በባሕርዳር ከተማ ሕዝባዊ ሰላማዊ ሰልፍ ተካሂዷል። በሕዝባዊ ሰልፉ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
በሰልፉ ላይ መልእክት ያስተላለፉት የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ሰላምን ለመደገፍ ጽንፈኝነትን ለማውገዝ ስለተገኛችሁ ምስጋናችን የላቀ ነው ብለዋል።
ጽንፈኛ ኃይሉ ለሰላም የተደረገን ጥሪ ለማደናቀፍ ጥረት ቢያደርግም እምቢ ብላችሁ ለሰላም የወጣችሁ ሁሉ አመሰግናለሁ ነው ያሉት። ኢትዮጵያ ተዝቆ የማያልቅ ሃብት ያላት፣ ብዝኀ ማንነት የገነባት ታላቅ ሀገር መኾኗን ተናግረዋል።
የአማራ ሕዝብ ከሌሎች ኢትዮጵያን ጋር ኾኖ ኢትዮጵያን ያጸና ለኢትዮጵያ ቀናዒ ሕዘብ መኾኑንም ገልጸዋል። በአማራ ሕዝብ ላይ በተሠራው ሥራ የአማራ ሕዝብ ጉዳት ሲደርስበት እንደነበርም ተናግረዋል። ዘረኞች እና መርዘኞች በሥርዓት እና በመዋቅር በሠሩት ሥራ በደል እንደደረሰበትም አስታውሰዋል። ሌሎች ኢትዮጵያውያንም የችግሩ ገፈት ቀማሾች እንደነበሩ ነው ያስታወሱት።
የአማራ ሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄዎችም በለውጡ መንግሥት መያዛቸውን ነው የተናገሩት። የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች እንዲመለሱ የአማራ ክልል መንግሥት ከፌዴራል መንግሥት እና ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር እየሠራ መኾኑን ነው የተናገሩት። ነገር ግን ጥያቄዎችን የማስመለስ ሂደት ብዙ ፈተናዎች እንደገጠሙት ነው የተናገሩት።
የሰሜኑ ጦርነት፣ በአማራ ክልል የተፈጠረው የጸጥታ ችግር የአማራ ሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄዎች በፍጥነት እንዳይመለሱ እንቅፋት መኾኑንም ገልጸዋል። በክልሉ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ወደ አንጻራዊ ሰላም እንዲመለስ መስዋዕትነት ለከፈለው ለሀገር መከላከያ ሠራዊት እና ሌሎች የጸጥታ ኃይሎች ምስጋና አቅርበዋል።
ጸረ ሰላምና ጽንፈኛው ኃይል በፈጠረው የጸጥታ ችግር ሰዎች ሞተዋል፣ ቆስለዋል ሃብትና ንብረት ወድሟል ነው ያሉት። ጽንፈኛው ኃይል ለአማራ ሕዝብ ቆሜያለሁ የሚል የአማራ ሕዝብ የሚያሳቃይ ነው ብለዋል። የአማራ ሕዝብን ጥያቄ የመመለስ ሞራልም አቅምም የለውም ነው ያሉት። የአማራ ሕዝብ ጥያቄ የሚፈታው በሰላም እና በውይይት ነው ብለዋል።
የአማራ ክልል መንግሥት በተደጋጋሚ የሰላም ጥሪ አቅርቧል፣ ለመወያየት እና ለመደራደር ዝግጁ ነው ብለዋል። ዛሬ የተደረገው ሰላማዊ ሰልፍ ሕዝብ ሰላምን የፈለገበት፣ ጦርነትን ያወገዘበት መኾኑንም ተናግረዋል። ሕዝብ ማኅበራዊ እረፍት ይፈልጋል፣ ድምጹን አክብራችሁ ሰላሙን አትንኩበት ብለዋል።
ከተማ አሥተዳደሩ ሰላሙን ከመጠበቅ ጎን ለጎን የልማት ሥራዎችን እየሠራ መኾኑንም አመላክተዋል። ደኅንነቱ የተጠበቀ ከተማና የከተማ ነዋሪ እንዲኖር የደኅንነት ካሜራዎች እየተገጠሙ መኾናቸውንም ገልጸዋል። ከዚህ በላይ ጉዳት እንዳይደርስ ለሰላም በጋራ ቆመን መሥራት ይጠበቅብናል ነው ያሉት። ጽንፈኛ ቡድኑን በቃህ ልንለው ይገባልም ብለዋል።
የባሕርዳር ከተማ ሕዝብ ላሳየው አስተዋይነት ምስጋና አቅርበዋል። የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች አደራቸውን እንዲወጡም ጥሪ ማቅረባቸውን አሚኮ ዘግቧል።