AMN – የካቲት 18/2017 ዓ.ም
ዛሬ 129ኛውን የአድዋ ድል በዓልን አስመልክቶ በአዲስ አበባ ሁሉም ወረዳዎች በተካሄዱ ውይይቶች ስለ ሀገር ፍቅርና አንደነት የሚያንፀባርቁ መልዕክቶች ተላልፈዋል፡-
የአድዋ ድል ኢትዮጵያ ብቸኛ ነፃ የጥቁር ሃገር ሆና እንድትቆይ አባቶቻችን የከፈሉት ዋጋ በመሆኑ መላዉ የዓለም ጥቁር ሕዝብ እጅግ የሚኮራበት ሲሆን ታሪክንም ቀይሯል።
የአድዋ ድል ኢትዮጵያዊያን ወራሪ ጠላትን ድል ያደረጉበት ብቻ ሳይሆን አንድነትና ትብብርን ያሳዩበት፣ ለትዉልድ ያቆዩት ጠንካራ የማስተባበር፣ የመምራት፣ የመደማመጥ ችሎታ እንዳላቸዉ ያስመሰከሩበት ነዉ።
የአድዋ ድል ለእኛ ለኢትዮጲያዊያን የአሸናፊነት፣ የአይበገሬነት፣ የትብብር፣ የሀገር ፍቅር፣ የአድነት መገለጫና የጥቁር ህዝቦች ታሪክ በመሆኑ የአሁኑ ትውልድ የጀግኖች አያቶቻችንንና አባቶቻችን ታሪክ ማስቀጠል ያስፈልጋል።

አድዋ ለእኛ ኢትዮጲያዊያን የኩራታችን ምንጭ ለአፍሪካዊያን ደግሞ ወሳኝ ታሪክ የተፃፈበት የድል በዓል ነው፡፡
የአድዋ ድል የአብሮነትና የአንድነት ማሳያ፣ ለመላው የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ምልክት ስለሆነ በዓሉን ስናከብር ለሀገራችን ሰላምና ልማት በጋራ በመቆም ጀግኖች አያቶቻችን ወራሪን ጠላት ሀይል በአንድነት እንዳሸነፉት ሁሉ፣ የአሁኑ ትውልድ ደግሞ ድህነት ላይ በመዝመት የኢትዮጵያን ብልፅግና እውን ለማድረግ ጠንክሮ መስራት ያስፈልጋል፡፡
አድዋ ጀግኖች አባቶቻችን በአንድነት በመሆን የውጭ ወራሪን በመመከት የአልሸነፍም ባይነትና የነፃነት ተምሳሌታች በመሆን ለመላው የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ዓርማን ያሳዩበት ነው ብለዋል።
የአሁኑ ትውልድ ታሪክን በመጠበቅ በተለያዩ የልማት ስራዎች በመሳተፍ የልማት አርበኛነቱን ማረጋገጥ አለበት።
በአባቶቻችን ደምና አጥንት የተገነባችውን ኢትዮጵያን በብልፅግና ዳግም ከፍ ለማድረግ አመራሩ ባለው እውቀትና አቅም ህዝቡንና ሃገሩን ሊያገለግል ይገባል፡፡
የአድዋ ድል በዓልን ስናከብር ካለፉት አመታትና ዘመናት በላቀ ድምቀት ማክበር ይኖርብናል። የአድዋ ድል በዓል ከምንጊዜዉም በላይ በከፍተኛ ድምቀት በአንድነት እና በሃገራዊ ስሜት ይከበራል፡፡

ዘንድሮ የሚከበረው የአድዋ ድል መታሰብያ በጥሩ መንፈስ እና በአንድነት ስሜት፣ ሃገራችንን በብልፅግና ፓርቲ መሪነት ወደ ላቀ ከፍታ የምናሻግርበት መሆን አለበት፡፡
መንግስታት ቢቀያየሩም አገርና ህዝብ ግን ይቀጥላል፡፡ ሁሉም መንግስታት የራሳቸው የሆነ ጥንካሬና ድክመት አላቸው፡፡ታሪክ ደግም ጥንካሬ እንዲቀጥል ድክመት እንዲስተካከል የሚጠቅም ትልቅ ት/ቤት ስለሆነ ልዩነታችን አጥብበን አንድነታችን አጠናክረን አገርንና ህዝብን ለማስቀጠል የዓድዋ ድል የታሪክ መፃህፍትን ያጣበበ ትልቅ ት/ቤት ነው፡፡
ከዓድዋ የትግልና የድል ታሪካችን በትኩረት ልንመለከተው የሚገባ ትልቁ ቁምነገር ኢትዮጵያውያን የዘር፤ የሃይማኖት፤ የቋንቋ፤ የብሔር፤ የባህል ወ.ዘ.ተ ልዩነቶች እንዳሏቸው የማይካድ ሃቅ ቢሆንም በሀገራዊ ጉዳያቸው ላይ ግን ከ አለት በጠነከረ አንድነት ተሳስበውና ተሳስረው በመቆም ልዩነቶቻቸውን የውበት፤የአንድነትና የጥንካሬያቸው መለያ (ጌጥ) ማድረግ መቻላቸውን ነው፡፡
በኢኮኖሚና በተክኖሎጂ ያላቸውን አቅም ተማምነው የመጡባቸውን ጠላቶች ሁሉ ከመመከት አልፈው ድል በማድረግ የሸኙበት ሚስጥርም በእናት ሀገራቸው ዙሪያ በአንድነት መፅናታቸው መሆኑ በግልፅ ታይቷል፡፡
በሀገራዊ ጉዳይ ላይ የሚፈጠር ጠንካራ አንድነት በዚህ ዘመን ያለ ትውልድ ሁሉ ሊማርበት የሚገባ በተግባር ተሞክሮ የተገኘ እውቀት ነው፡፡
ዓድዋ ዝንተ-ዓለም የማይደበዝዝ ታሪክ የተፈፀመበት የኢትዮጵያ የህልውናዋ መጠንሰሻ፤ የስልጣኔዋ መነሻ፤ የማንነቷ መታወቅያ፤ የነፃነቷ መከበሪያ፤ ተተርኮ የማይነጥፍ፤ ተሰምቶ የማይሰለች የጀግንነት ታሪክ ነው፡፡ ዓድዋ የአፍሪካውያን መኩሪያ፤ የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ተምሳሌት የገናናው ታሪካችን ማህደር፤የኩራታችን መደበር ነው ፡፡
የዓድዋ ተራራዎች በቱሪዝም ውብ መስህብ ፀጋዎች በታሪክ ደግሞ የሚነበቡ የኢትዮጵያ ቋሚ ቅርሶች ሲሆኑ እነዚህ ተራራዎች በአከባቢው ስለተሰራው ገድል ብዙ የሚናገሩ ናቸው፡፡
ይህን ታሪክ በየዓመቱ በድምቅት የምናከብረው አባቶቻችን ባህርና ተራራ አቋርጦ ከመጣ ወራሪ ጋር ፊት ለፊት በመፋለም ጠላትን ድል ያደረጉበት የድል ታሪክ ብቻ አይደለም፡፡ ከኢትዮጵያውን አልፎ ለመላው ዓለም የማይቻል ነገር እንደሌለ መልዕክት የተላለፈበት፤ የአርቆ አስተዋይነትና ታጋሽነት በገሀድ የታየበት በመሆኑ ነው፡፡
የዓድዋ ድል የኢትዮጵያ ጥንታዊ ታሪክ ተበጥሶ እንዳይቀርና ተያይዞ እንዲቀጥል ያደረገልን ልዩ ክስተታዊ ኩራታችን ነው፡፡ ስለሆነም የዓድዋ ድል የጥንቶቹን አባቶቻችን እና አያቶቻችን ጀግንነት ለሀገር ያላቸው ፍቅር የተመሰከረበት፤ ባህላችን ተጠብቆ እንዲኖር የኢትዮጵያን አንድነት ዕውን ለማድረግ፤ ኢትዮጵያ በአለማቀፍ መድረክ በጀግንነት እንድትታወቅና እንድትከበር ያደረገ ነው፡፡
የአሁኑ ትውልድ በተለይ ወጣቶች ድህነትን ታሪክ ለማድረግ፣ የስራ ባህላችንን በማሳደግ፤ ድህነትንና ኋላ ቀርነትን ተረት በማድረግ የሃገራችን ዕድገት ማፈጠን ይጠበቅበታል፡፡
በአጠቃላይ በዛሬው 129ኛውን የአድዋ ድል በዓልን አስመልክቶ በአዲስ አበባ ሁሉም ወረዳዎች በተካሄዱ ውይይቶች የተላለፉ መልዕክቶች የአገር ፍቅር ስሜት የተንፀባረቀበት፣ የአያት ቅድመ አያቶቻችን አንድነትና መተባበር ለድል እንዳበቃቸው እና ቅኝ ያልተገዛች ነፃ ሀገር እንዳስረከቡን ሁሉ የአሁኑ ትውልድ ደግሞ በድህነት ላይ በአንድነት ተነስቶ ኢትዮጵያን ማበልፀግ እንደሚገባ አነቃቂ መልዕክቶች የተላለፉበት እንደነበር ከአዲስ አበባ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡