AMN-የካቲት 11 ቀን 2017 አ.ም
በእንግሊዝ ኤፍ ኤ ካፕ 4ኛ ዙር ሊቨርፑል ሳይጠበቅ በፕሌማውዝ ተሸንፎ ከውድድሩ መሰናበቱ የሚታወቅ ነው፡፡
በእለቱ ጨዋታ የሊቨርፑሉ ተከላካይ ዦ ጎሜዝ በ11ኛው ደቂቃ ተቀይሮ ሜዳ ገብቶ ነበር፡፡
ይሁንና ተጨዋቹ ከስድስት ሳምንታት ጉዳት በሁዋላ የመጀመሪያ ጨዋታውን ባደረገበት መርሀግብር ለተጨማሪ ጉዳት መጋለጡን ቢቢሲ ስፖርት ዘገቧል፡፡
በውድድር አመቱ ለክለቡ 10 ጨዋታዎችን ብቻ ያደረገው ተከላካዩ የደረሰበት የጡንቻ መሳሳብ ጉዳት ከባድ መሆኑን አሰልጣኝ አርን ስሎት ተናግረዋል፡፡
ተጨዋቹ የቀዶ ህክምና እንደሚያስፈልገው እየተነገረ ሲሆን የጉዳቱ መጠኑ ለረጅም ጊዜ ከሜዳ ሊያርቀው እንደሚችል አሰልጣኙ አክለዋል፡፡
ወደ አቋሙ ለመመለስ ጠንክሮ ሲሰራ ቆይቷል፤ነገርግን ከጉዳቱ ማገገም አልቻለም ምናልባት በውድድር አመቱ መጨረሻ አገግሞ ሊቀላቀለን ይችላል ነው ያሉት ስሎት፡፡
እ ኤ አ በ2015 ከቻርልተን አትሌቲክ የአንፊልዱን ክለብ የተቀላቀለው ተከላካዩ በቀዮቹ ማልያ 149 ጨዋታዎችን አድርጓል፡፡
በበላይነህ ይልማ