AMN – ታኅሣሥ 20/2017 ዓ.ም
የሀረሪን ባህላዊ እና ታሪካዊ ሀብት መሰረት ያደረጉ የኮሪደር ልማት ስራዎች የጎብኚዎች ቁጥር እንዲጨምር ማድረጋቸውን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ገለጹ።
የብልጽግና ፓርቲ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ኢትዮጵያ በርካታ የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ ጸጋዎችን ብትታደልም እነዚህን ጸጋዎች ወደ ሃብት ከመቀየር አኳያ ውስንነቶች እንደነበሩ አስታውሰዋል።
ይህን ጸጋ አሟጦ በመጠቀም ከቱሪዝም የሚፈለገውን ገቢ ለማግኘት ለውጡን ተከትሎ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል።
መንግስት ዘርፉን ለማነቃቃትና አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻ መሰረተ ልማቶችን ለማሟላት ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።
ከዚህ አኳያ የሀረሪ ክልል አዳዲስና ነባር የቱሪዝም መዳረሻ መሰረተ ልማቶች ላይ በስፋት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ይህንንም ተከትሎ ወደ ሀረሪ የሚመጡ የጎብኚዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል ብለዋል።
ይህም የስራ ዕድል በመፍጠርና ኢኮኖሚውን በማነቃቃት ረገድ ጉልህ ሚና እያበረከተ መሆኑንም አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያ ከዘርፉ የሚፈለገውን ጥቅም እንድታገኝ ያሏትን ሃብቶች ከማስተዋወቅና ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለመሙላት በቀጣይ በስፋት መስራት ይገባል ብለዋል።
የኮሪደር ልማት ስራዎች የከተሞችን ዕድገት ከማረጋገጥ ባለፈ ለጎብኚዎች ምቹ የእግረኛ መንገድ እንዲኖር ያላቸው አስተዋጽኦ የጎላ መሆኑን ነው የጠቀሱት።
በመሆኑም ክልሉ በዚህ ረገድ ለጎብኚዎች ምቹ የእግረኛ መንገዶችና መናፈሻ ቦታዎችን በስፋት እየሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
የቱሪዝም ዕድገት ለሌሎች ዘርፎችም መነቃቃት በመፍጠር ተጠቃሚነትን በእጅጉ እንደሚያሳድግ መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡