ወደ መጨረሻ ምዕራፍ ላይ የደረሰው የሀገራዊ ምክክር ሂደት ከግብ እንዲደርስ ሁሉም ማህበረሰብ ሀላፊነቱን እንዲወጣ ተጠየቀ፡፡
የኢትዮጲያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የፌዴራል ተቋማት እና ማህበራት አጀንዳ የማሰባሰቢያ መድረክ መካሄድ ጀምሯል።
በመድረኩ የሃይማኖት አባቶች፣ ከፍተኛ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች፣ የፌደራል ተቋማት እና ማህበራት ተወካዮች ተገኝተዋል።
በመክፈቻ መርሐ-ግብሩ፣ የኢትዮጲያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርአያ (ፕ/ር) የጋራ እሴቶቻችንን የሚፈታተኑ ሁኔታዎች ሀገራችንን በርካታ ዋጋዎች አስከፍለዋታል፤ እነዚህን ሁኔታዎች በምክክር መፍታት ይገባናል ሲሉ ተናግረዋል።
ኮሚሽኑ ባለፍት 3 ዓመታት 14 ያህል ትልልቅ መድረኮችን ማካሄዱን የገለፁት ዋና ኮሚሽነሩ፣ ግጭቶችን በንግግር ለመፍታት እንደ ማህበረሰብ የተኬደው ጉዞ ውጤታማ መሆኑን አንስተዋል።
በዛሬውም መድረክ ሚሊየኖችን የሚወክሉ አጀንዳዎች እንደሚቀርቡ ተስፋ እንደሚያደርጉም አንስተዋል።
በዛሬ የቅድመ ምክክር እና አጀንዳ ማሰባሰብ ላይ ከ38 የፌዴራል ተቋማት እና ማህበራት የተወጣጡ 800 ተሳታፊዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ።
በወንድምአገኝ አበበ እና በአንዋር አህመድ