የሂዝቦላህ ታጣቂ ቡድን የሚጠቀምባቸው የመገናኛ መሳርያዎች ፈንድተው ቢያንስ 9 ሰዎች ሞቱ

You are currently viewing የሂዝቦላህ ታጣቂ ቡድን የሚጠቀምባቸው የመገናኛ መሳርያዎች ፈንድተው ቢያንስ 9 ሰዎች ሞቱ

AMN – መስከረም 8/2017 ዓ.ም

በመቶዎች የሚቆጠሩ የሂዝቦላህ ታጣቂ ቡድን አባላት የሚጠቀሙባቸው የመገናኛ መሳሪያዎች በሊባኖስ እና በሶሪያ በተመሳሳይ ጊዜ ፈንድተው የ8 ዓመት ህጻንን ጨምሮ ቢያንስ ዘጠኝ ሰዎች መሞታቸውን እና በብዙ ሺዎች መቁሰላቸውን ባለስልጣናት ተናግረዋል።

ሂዝቦላህ እና የሊባኖስ መንግሥት የተራቀቀ ላሉት ጥቃት እስራኤልን ተጠያቂ ያደረጉ ሲሆን ከእስራኤል በኩል የተሰጠ ምላሽ የለም፡፡

የኢራን የሊባኖስ አምባሳደር በተመሳሳይ ፍንዳታዎች ከቆሰሉት 2 ሺ 800 ሰዎች መካከል ይገኙበታል።

ምስጢራዊው ፍንዳታ በእሥራኤል እና በኢራን በሚደገፈው ሂዝቦላህ መካከል ውጥረት እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ የተከሰተ ነው።

የቡድኑ መሪ ባላፈው የካቲት ወር አባላቱ ከዚህ ቀደም ይጠቀሙበት የነበረውን ተንቀሳቃሽ ስልክ በእስራኤል ሊጠለፉ ይችላሉ በሚል ስጋት መጠቀማቸውን እንዲያቆሙ ትዕዛዝ ካስተላለፉ በኋላ ነበር አሁን ፍንዳታ ያስከተሉት የመገናኛ መሳርያዎች ጥቅም ላይ የዋሉት፡፡

አንድ የሂዝቦላህ ባለሥልጣን የመገናኛ መሳርያዎቹ አዲስ እንደሆኑ ለአሶሲዬትድ ፕሬስ ተናግረዋል፡፡

በትናንትናው ዕለት ከምሽቱ 3፡30 ገደማ መሳርያዎቹን የያዙ እና በተለያዩ እንቅስቃሴዎች ላይ የነበሩ ሰዎች በእጃቸው ወይም በኪሳቸው ውስጥ የነበሩት የመገናኛ መሳርያዎች ሙቀት መፍጠራቸው እና መፈንዳታቸው ነው የተነገረው፡፡

መሳርያውን ከያዙ ሰዎች መካከል አብዛኞቹ የሂዝቦላህ አባላት ሲሆኑ የቡድኑ አባላት ያልሆኑ ሰዎችም የፈነዱትን መሳርያዎች ይዘው ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል፡፡

የሊባኖስ የደህንነት ባለሥልጣናት እንደገለጹት፣ ፍንዳታው በአብዛኛው ቡድኑ ጠንካራ በሆነባቸው አካባቢዎች በተለይም በደቡባዊ ቤሩት ዳርቻ እና በምሥራቅ ሊባኖስ የቤካ ክልል እንዲሁም በደማስቆ የተከሰተ ነው።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review