AMN – ጥቅምት 14/ 2017 ዓ.ም
የአዲስ አበባ የሀይማኖት ተቋማት ጉባኤ ከወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ህብረት ጋር በመተባበር “ሀይማኖታዊ ምክክር ለሰላምና አብሮነት ያለው ፋይዳ” በሚል መሪ ሀሳብ ምክክር እያደረገ ነው።
በምክክሩም የአዲስ አበባ የሀይማኖት ተቋማት ዋና ጸሀፊ መጋቢ ታምራት አበጋዝ እንደ ሀገር የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት መወያየትና መመካከር ይገባል ብለዋል።

ተቋማቱ በውይይት የተለያዩ ችግሮችን መፍታት ችለናል ብለዋል ።
በሠላም እሴት ግንባታ፣ በስነ-ምግባርና የሞራል ግንባታ ላይ በማተኮር መመካከር እንደሚገባም መክረዋል።
የሃይማኖት ተቋማት ሀገራዊ አንድነትን በሚያጠናክሩና ትውልድን በስነ-ምግባር በሚያንፁ ስራዎች ላይ አተኩረው በመስራት ለትውልዱ አርዓያ መሆን ያስፈልጋል ሲሉም የሀይማኖት ተቋማቱ ጠቁመዋል ።
የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ህብረት ፕሬዚዳንት ፃዲቁ አብዶ አንዳንድ ግለሰቦችና ቡድኖች ዜጎች እርስ በርስ እንዳይተማመኑና እንዲጋጩ ሀይማኖትን እንደ መሳሪያ ይጠቀማሉ።
ለዚህ ደግሞ ክፍተት ባለመፍጠር መከባበርና መመካከር ይገባል ብለዋል ፕሬዝደንቱ።
የሁሉም ሀይማኖት ቅዱሳት መጽሀፍ እንደሚያዝዙን አንዱ በሌላው ክፉ ባለመስራት ለሰላም መቆም፣ አንዱ የሌላውን ሀይማኖት ማክበር ይገባልም ብለዋል።
በሄለን ጀምበሬ