የህዝብን ጥያቄ መመለስ ዋነኛ አጀንዳችን ነው – ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር አባይ

You are currently viewing የህዝብን ጥያቄ መመለስ ዋነኛ አጀንዳችን ነው – ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር አባይ

AMN-የካቲት 12/2017 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የ2017 ዓ.ም 4ኛ የስራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ጉባኤውን እያካሄደ ይገኛል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለምክር ቤቱ ያቀረቡት የከተማ አስተዳደሩን የ6 ወራት እቅድ አፈፃፀም ተከትሎ የምክር ቤቱ አባላት የተለያዩ ሀሳብና ጥያቄዎችን አንስተዋል፡፡

በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የምክር ቤት አባላት ላነሱት ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ የሰጡት የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ እና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ ባለፉት 6 ወራት የህዝብን ጥያቄ መመለስ ዋነኛ አጀንዳችን ነበር ብለዋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ በየደረጃው እየገመገመ በመጣዉ የልማት ሥራዎች እንቅስቃሴ ላይ በዝርዝር መምከራቸውን የጠቆሙት ምክትል ከንቲባው ካለው መጠነ ሰፊ የህዝብ ጥያቄ አኳያ እስካሁን የተከናወነው ሥራ በጎና መልካም ቢሆንም ፣ ወደ እርካታ ደረጃ ሊወስድ የሚችል አለመሆኑን አብራርተዋል፡፡

ከግምገማው በመነሳትም በከተማዋ አሁንም ብዙ ችግሮች መኖራቸውን ፣ ድህነት ከማቃለል አንፃርም ብዙ መስራት የሚጠበቅብን መሆኑንና ለዚህ የሚመጥን ተግባራት ሊከናወኑ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

በከተማዋ በተለያዩ ዘርፎች ጥሩ ስራዎች ቢሰሩም ከችግሩ ስፋት አኳያ አሁንም ገና ብዙ መስራት እንደሚያስፈልግ በየደረጃው ባለው አመራር ዘንድ ተግባቦት መፈጠሩንም ነው አቶ ጃንጥራር ያመለከቱት፡፡

የኮሪደር ልማትን ስንጀምር ከቦታቸው የሚነሱ ነዋሪዎችን ወደ አዲሱ ቤታቸው እንዴት ማድረስ እንዳለብን እና ሌሎች ችግሮቻቸው እንዴት መፈታት እንዳለበት ግልፅ አቅጣጫ ተይዞ ወደ ሥራ መገባቱን አብራርተዋል፡፡

ከዚህ አኳያ አመራሩ በመሬት አቅርቦት ፣ በግምባታ ፈቃድ እና በካሳ አከፋፈል የሚነሱ ጉዳዮችን በልዩ ትኩረት እየገመገመ እንዲመራ አቅጣጫ ተቀምጦ ተግባራዊ ተደርጓልም ብለዋል፡፡

የተንጠባጠቡ ችግሮችን ለማረም እና ለማስተካከል ከዲዛይን ጋር በተያያዘ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመቅረፍ አመራሩ በትኩረት መስራቱንም ምክትል ከንቲባው ጠቁመዋል ፡፡

ለነዋሪዎች አገልግሎቱን በኣንድ መስኮት በመስጠት በሚገቡበት አካባቢ ሁሉ የገጠማቸውን የመሰረተልማትና መሰል ችግሮችን ለመፍታት አቅጣጫዎች ተቀምጠው ተግባራዊ በማድረግ ሥኬታማ ሥራዎች ተከናውነዋል ብለዋል ፡፡

በወርቅነህ አቢዮ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review