AMN- የካቲት 15/2017 ዓ.ም
ሀገር አቀፍ ህዝባዊ ኮንፈረንስ በአዲስ አበባ በተለያዩ መርሀ ግብሮች መካሄዱን ቀጥሏል፡፡
በመድረኩ በብልፅግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅ /ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ ሞገስ ባልቻ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ሁለተኛው የብልፅግና ፓርቲ ጉባዔ የብልፅግና ተምሳሌት በሆችው አዲስ አበባ የኢትዮጵያን መፃኢ ጊዜ ከፍ በሚያደርጉ ጉዳዮች ላይ መክሮ አቅጣጫዎችን ማስቀመጡን አውስተዋል።
የህዝባዊ ኮንፈረንሱ ዓላማ ብልፅግና ሀገር እየመራ ያለ ፓርቲ እንደመሆኑ ውሳኔዎቹን ህዝብ በማወያየት ተጨማሪ አቅም ለመፍጠር መሆኑን የጠቀሱት አቶ ሞገስ ከዛሬው የማጠቃለያ ኮንፈረንስ በፊትም ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ስኬታማ ውይይቶች መካሄዳቸውን ተናግረዋል።
እስካሁን በተደረጉ ህዝባዊ ውይይቶች የተነሱ ዋና ዋና ጉዳዮችን እና ለመፍታት የተደረገውን ርብርብም አቶ ሞገስ ለከተማ አቀፍ ውይይቱ ታዳሚዎች አቅርበዋል።

ከሴቶችና ከወጣቶች ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ፣ የመልካም አስተዳደር ፣ የልማት ጥያቄዎች ፣ የፅንፈኝነት አስተሳሰብና ተግባርን መታገል ላይ እንዲሁም አስተማማኝ ዘላቂ ሰላም ለመገንባት እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ምን እንደሚመስሉ ከህዝቡ ጥያቄዎች ሲቀርቡ እንደነበር አውስተዋል።
የህዝብ ጥያቄዎች ሁሉንም ባለድርሻ አካላት በማቀናጀትና ህዝብን በማስተባበር እየተመለሱ መሆናቸው ተገልጿል።
በከተማዋ ባለፉት ሶስት ዓመታት 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ቋሚ የስራ ዕድል መፈጠሩ ከወጣቶችና ከሴቶች ተጠቃሚነት አንፃር ተጠቅሷል።
የከተማዋ ገቢም 2011 ዓ.ም 30 ቢሊዮን ብር የነበረ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን በዚህ ዓመት 2030 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ በመልካም አፈፃፀም ላይ እንደሚገኝ ተመላክቷል።
ከከተማዋ በጀት 70 በመቶው የሚሆነውን ለካፒታል በጀት ማዋል በመቻሉ ተጨባጭ ስኬቶች መመዝገባቸው ተጠቅሷል።
በሌማት ትሩፋት ፣ በከተማ ግብርና፣ በአረንጓዴ ልማት እና በሜጋ ፕሮጀክቶችም አበረታች ስኬቶች ተመዝግበዋል ነው የተባለው።
በማህበራዊ ልማት በተለይም የትምህርት እና የጤና ተደራሽነትን እና ጥራትን ለማረጋገጥ ሰፋፊ ስራዎች መከናወናቸው ተገልጿል።
ለወጣቶችና ለታዳጊዎች 1300 የስፖርት ማዘውተሪያዎች ተገንብተው አገልግሎት እየሰጡ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
የአገልግሎት አሰጣጡ ላይ የሚስተዋሉ ብልሹ አሰራሮችን ለማረም በቴክኖሎጂ የታገዙ ሰፋፊ የሪፎርም ተግባራት እየተሰሩ መሆኑ መገለጹን የአዲስ አበባ ብልጽግና ፓርቲ ቅ/ጽህፈት ቤት መረጃ ያሳያል።
አዲስ አበባን እንደ ስሟ አበባ ያደረገውን የመጀመሪያውን ዙር የኮሪደር ልማት ውጤት ያነሱት አቶ ሞገስ ሁለተኛው ዙር ደግሞ በጥራት እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በበብልፅግና ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ እና ም/ቤት አባላት የሚመራው ሀገር አቀፍ የህዝብ ኮንፈረንስ በከተማ ደረጃ የብልፅግና ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልና የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ወ/ሮ አለሚቱ ኡመድ እንዲሁም የብልፅግና ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር እንዳሻው ጣሰው በተገኙበት ነው እየተካሄደ የሚገኘው፡፡