የሌተናል ጄኔራል ጃገማ ኬሎ ሁለት ጋሻዎች እና አምስት ጦሮች ፒተር ሹልዝ ከተባሉ ግለሰብ ለኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ተበርክቷል።
ጋሻዎቹና ጦሮቹ ታላቅ የትግል አርበኛ የነበሩት ጃካማ ኬሎ ግለ ታሪካቸው እንዲጻፍና እንዲታተም ከፍተኛ ሚና ላደረጉት የኤስ ጂ አይ አፍሪካ ሊሚትድ ባለቤት ሚስተር ፒተር ሹልዝ ከ16 ዓመታት በፊት በስጦታ ያበረከቱላቸው እንደነበረ በርክክቡ ወቅት ተገልጿል።
ቅርሶቹን የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው ተረክበዋል።
ረዳት ፕሮፌሰር አበባው የታዋቂውና የስመጥሩ አርበኛ ሌተናል ጄኔራል ጃካማ ኬሎ የሆኑ ቅርሶችን ለባለስልጣኑ በመለገሳቸው ደስታ እንደሰማቸው ገልጸዋል።
በተለይም ቅርሱ ለባለስልጣኑ እንዲሰጥ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ላደረጉት ለአቶ ማሞ ምህረቱ እና ለአቶ ተስፋዬ ኃይለሚካኤል ምስጋና አቅርበዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ ለፒተር ሹልዝ የምስጋና የምስክር ወረቀት ሰጥተዋል።
ታላቅ የትግል አርበኛ የነበሩት ጃገማ ኬሎ ጣሊያን ኢትዮጵያን ስትወር ቅኝ ግዛትን አልቀበልም ብለው በ15 አመታቸው ጠላትን ለመታገል የቆረጡና በአርበኝነት የታገሉ ጀግና እንደነበሩ ባለስልጣኑ በመረጃው አውስቷል።
በነበራቸው የትግል ቆይታ በወራሪው ኃይል ላይ ከፍተኛ ኪሳራና ጉዳትን ያደረሱ በስራቸውም በርካታ አርበኞችን በማሳለፍ ትግልን ያከናውኑ የነበሩ አርበኛ እንደነበሩም ተገልጿል።
ከጦርነትና ከድል በኋላ ጃገማ ኬሎ የሌተናል ጄነራል ማዕረግ የተሰጣቸው ሲሆን ጣሊያንን በመታገልና ለሀገራቸውም በተለያዩ መንገዶች ነጻነቷን ጠብቃ እንድትቆይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከታቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡