AMN-ኅዳር 16/2017 ዓ.ም
አህጉራዊ እና አለም አቀፍ አጋሮች በአፍሪካ ዘላቂ ሰላም እና ልማትን ለማጎልበት የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ገለጹ።
“የበለጸገችና ሰላማዊ አፍሪካን እንገንባ” በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ የተካሄደው የመጀመሪያ ቀን የውይይት መርሐ ግብር ተጠናቋል፡፡
በውይይቱ ማጠቃለያ መርኃ ግብሩ የተገኙት የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ባስተላለፉት መልዕክት ሰላም ከፍ ያለ ሀሳብ ብቻ ሳይሆን ለህብረተሰባችን እድገት፣ ብልጽግና እና ደህንነት መሰረታዊ ፍላጎት ነው ብለዋል።
በዚህም አህጉራዊና አለም አቀፍ አጋሮች በአፍሪካ ዘላቂ ሰላም እና ልማትን ለማጎልበት የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው መቀጠል አለባቸው ነው ያሉት።
የአፍሪካን ችግሮች በፓን አፍሪካዊ መንፈስ ለመፍታት የጋራ ጥረት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

ይህ ጉባኤ ማጠቃለያ ሳይሆን አዲስ ጅምር ነው ያሉት አፈ ጉባኤው እጅ ለእጅ ተያይዘን የበለጸገች እና ሰላሟ የተረጋገጠ አፍሪካን በጋራ ለመገንባት የገባነውን የጋራ ቃል ኪዳን የምናድስበት ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ዛሬ የምናደርጋቸው የጋራ ተግባራት የመጪውን ትውልድ የወደፊት ዕጣ ፈንታ የሚቀርጹ መሆኑን አውቀን ውይይትን፣ እርቅን እና ትብብርን ለማጎልበት በምናደርገው ጥረት በአንድነት መቆም አለብን ብለዋል።
የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአህጉሪቱ ዘላቂ ሠላም ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት እንደሚደግፍ ማረጋገጣቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ትክክለኛውን የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዲጂታል ሚዲያ የትስስር አውታሮችን በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑን!