
AMN- ጥቅምት 25/2017 ዓ.ም
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ የትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልእክት በማሌዥያ ጉብኝታችን የኳላ ላምፑር ምክትል ከንቲባ ኢስማዲ ቢን ሳኪሪን እና የከተማ አስተዳደሩ አመራሮች ደማቅ አቀባበል አድርገውልናል ብለዋል።
በአዲስ አበባ እና ኳላ ላምፑር መካከል ትስስርን በማጠናከር በተለይም በከተማ ፕላን፣ በአረጓዴ ልማት፣ በአካባቢ ጥበቃና እንክብካቤ፣ በህዝብ መናፈሻዎች፣ በኢንቨስትመንት፣ በጤና፣ በንግድ እና ቱሪዝም ዘርፎች ላይ ይበልጥ ተቀራርበን መስራት በምንችልባቸው መንገዶች ዙሪያ ፍሬያማ ውይይት አካሂደናል ሲሉም አመልክተዋል።
በነበረን ቆይታም የስማርት የትራፊክ መቆጣጠሪያ ማዕከልን እንዲሁም የፐርዲና ቦታኒካል ጋርደንን ጎብኝተን የአዲስ አበባ ከተማ የማስታወሻ ችግኝ ተከላ መርሃግብር አካሂደናል ሲሉም ገልጸዋል።
የማሌዢያዋ ኳላ ላምፑር ከተማን ለነዋሪዎች ምቹ ለማድረግ እና በቱሪዝም ልማት እያካሄደች ያለው የትራንስፎርሜሽን ስራዎች የምንማርበት በመሆኑ የሁለቱን ከተሞች ግንኙነት አጠናክረን የምንቀጥል ይሆናልም ብለዋል።