AMN ህዳር 17/2017 ዓ .ም
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው 6ኛ መደበኛ ጉባኤው አቶ ሐጂ ኢብሳን የፌዴራል ዋና ኦዲተር ምክትል ዋና ኦዲተር አድርጎ ሾሟል፡፡
የአቶ ሐጂን ሹመት ያቀረቡት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጄጌ (ዶ/ር) ሲሆኑ፣ አቶ ሐጂ በዘርፉ ከፍተኛ ልምድ እና ብቃት እንዳላቸው አብራርተዋል፡፡
ምክር ቤቱም የአቶ ሐጂ ኢብሳን ሹመት በሁለት ድምጸ- ተዓቅቦና በአብላጫ ድምጽ አጽድቋል፡፡

በሌላ ዜና፣ ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ የተመሰከረላቸው የሂሳብ ባለሙያዎች ኢንስቲትዩት ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅን ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መርቷል፡፡
የማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጁን ያቀረቡት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጂጌ (ዶ/ር) ሲሆኑ፣ ረቂቅ አዋጁ በኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ የግልና እና የመንግስት ድርጅቶች ላይ ተግባራዊ የሚደረግ የተሟላ፣ ግልጽ እና በቀላሉ ሊረዱት የሚችሉት የፋይናንስ አዘገጃጀት እና አቀራረብ ስርዓት መዘርጋት በማስፈለጉ ነው ብለዋል፡፡
ሚኒሰትሩ አክለውም፣ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርት እና የኦዲት ደረጃዎችን ተግባራዊ ለማድረግ በቂና የተመሰከረላቸው የሂሳብ ባለሙያዎች ማፍራት አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል ነው ያሉት፡፡
ማቋቋሚያ አዋጁ፣ ለዝርዝር ዕይታ ለፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሙሉ ድምጽ መመራቱን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ትክክለኛውን የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዲጂታል ሚዲያ የትስስር አውታሮች