የሕይወት ትርጉም በክቡር ልጆች መጽሐፍ

You are currently viewing የሕይወት ትርጉም በክቡር ልጆች መጽሐፍ

አንድ ልጅ ከእናቱ ጋር እየተጓዘ ሳለ “እማ የህይወት ትርጉሙ ምንድን ነው” አላት በጣፋጭ አንደበቱ፡፡ እናትም የልጇ ጥያቄ ገርሟት ጉዞዋን ገታ አድርጋ በልጁ ቁመት ልክ በርከክ አለችና አይን አይኑን እያየች “ልጄ የህይወት ትርጉሙ አንተ ነህ” አለችው ይላል ብርሃኑ በላቸው “ክብሩ ልጆች” በተሰኘው መጽሐፉ መግቢያ ላይ፡፡

በመጽሐፉ ላይ እንደተጠቀሰው ዶኔልና ጓደኞቹ ባጠኑት ጥናት መሰረት በወላጆችና ልጆች መካከል ያለው ጥብቅ ግንኙነት የህይወትን ትርጉም ለመረዳት አስፈላጊና መሰረታዊ ነው፡፡ ይህ  ትስስር ደግሞ  የተቀባይነትና የተደማጭነትን  ስሜት በመፍጠር ለህይወት ትርጉም ይሰጣል፡፡ እንደ ስቲገር እና ጓደኞቹ ጥናት ደግሞ በወላጅና ልጅ መካከል ጥብቅ የስሜት ትስስር በመፍጠር ህይወትን የሚያጣጥም ቤተሰብ መገለጫው አላማ መር ህይወት መኖር ነው፡፡

ይህን ለማድረግ ደግሞ እያዝናኑ የሚያስተምሩ፣ በምሳሌ ህይወትን መስመር የሚያስይዙ፣ ደስተኛ ቤተሰብ እና ሀገርን ለመገንባት የሚያስችሉ መጽሐፍ ወሳኝ ናቸው። ከእነዚህ መጽሐፍት መካከል በብርሃኑ በላቸው የተጻፈው “ክቡሩ ልጆች” አንዱ ነው። የአዲስ ልሳን ዝግጅት ክፍልም እያዝናና የሚያስተምረውን፣ በአስገራሚ ምሳሌዎችና እውነተኛ የህይወት ልምዶች የተሞላውን እና ዋነኛ አላማው በወላጆችና  ልጆች መካከል ያለውን ትስስር ይበልጥ በማጠናከር ሁለንተናዊ የልጆች እድገትን ማበልጸግ በሆነው በዚህ መጽሐፍ ላይ አጭር ዳሰሳ አድርጓል፡፡

ቤተሰብነት

ደራሲው የልጆች የራስ መተማመን ምስጢር የቤተሰብ የጋራ ጊዜ መኖር ነው ይላል። “ልጅ ፊት ያለን ድንጋይ አታንሳ፤ ድንጋይ እንዳለ ንገረው” ይባላል፡፡ ይህ የሚባለው ልጅ ለገጠመው ፈተና ሁሉ ቤተሰብ እንዲፈታለት ሳይሆን በራሱ ችግሩን ተጋፍጦ የመፍታት አቅሙን እንዲያጎለብት ማስተማርና ማሰልጠንን ለማበረታታት ነው፡፡ ልጆቻችንን በራስ የመተማመን  አቅማቸውን የምናጎለብትበት መንገድ ከእነሱ ጋር በምናሳልፈው ጊዜ ይወሰናል ይላል፡፡ ይህ ጊዜ ደግሞ ብዛቱ ብቻም ሳይሆን ጥራቱ እና ፍሬያማነቱ መታየት ይኖርበታል፡፡

የፍሬያማ ጊዜ ዋነኛ ማእከል ልጆች ናቸው፡፡ በልጆች ምርጫ እና ፍላጎት የሚከናወን የጋራ ጨዋታ ነው፡፡ ለአብነትም ድብብቆሽ፣ መጽሐፍ ማንበብ፣ እንቆቅልሽ፣ ተረት ተረት፣ የልጅ እድሜን ያገናዘበ የቤት ውስጥ የጋራ ስራ ማከናወን እና በጋራ ወደ ውጭ አየር መቀበል ሊሆን ይችላል፡፡

ይህ ደግሞ የቤተሰብ ትስስርን ያጠናክራል። ደስተኛ ቤተሰብም ይፈጥራል። እነዚህ ልጆች ከቤተሰባቸው ጋር ባላቸው መልካም ግንኙነት መጥፎ ነገር ቢገጥማቸው ጠንክሮ ለመውጣት አቅም ይኖራቸዋል፡፡ ወላጆች ልጆቻቸው ጋር ፍሬማ ጊዜ የማዳበር ልምዳቸው ጠንካራ እንዲሆን ይመከራል ሲልም መጽሐፉ ያክላል፡፡

በተጨማሪም በወላጅ እና በልጅ መካከል ያለው ግንኙነት ያድጋል፡፡ አንዳንዴ በጨዋታ መካከል ይህቺ ልጅ ቀበጠች ወይም ቀበጠ እንላለን፡፡ ይሁንና ልጆች በህይወታቸው የሚፈልጉት እና የሚያረካቸው የፍቅር ከባቢ ሲያገኙ ስሜታቸውን የሚገልጹበት መንገድ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል ሲል ደራሲው በአጽንኦት ገልጿል፡፡

ክቡር ልጆች

ደራሲው መጽሐፉን በተለያዩ ምዕራፎች እና ርዕሶች የከፋፈለው ሲሆን፤ ሁለተኛው ምእራፍ በመጽሐፉ ርዕስ ክቡር ልጆች ተሰይሟል። ደራሲው እንደሚለው ልጆች ከሁሉም ቁስም ይሁን ሌላ ነገር በላይ ክቡር ናቸው፡፡ በመሆኑም የሚገባቸውን ክብር ልንሰጣቸው ይገባል ይላል፡፡

በዚሁ መጽሐፍ ገጽ 44 ላይ እንደሰፈረው ልጅን ማክበር ስንል የልጆችን ሃሳብ ለመስማት ዝግጁ መሆን፣ የልጆችን ማንነታቸው፣ ስብዕናቸው መቀበል፣ ለልጆች ፍላጎትና ስሜት ጆሮ መክፈት፣ ልጆችን በሚመለከት ጉዳይ በውሳኔ ሰጭነት ተሳታፊ ማድረግና በእነሱ ጫማ ውስጥ ሆኖ ለማየት መጣርን ያካትታል ይላል፡፡

ለልጆች ያለን  አመለካከት ቀጣይ የሀገር ተረካቢ ትውልድ እጣ ፋንታን ሊወሰን ይችላል። ጤናማ የቤተሰብ አመለካከት ብቁና ፍሬያማ ዜጋ ለማፍራት መሰረት ነው፡፡ ነገ ሀገር ምን ትመስላለች ቢባል የዛሬ ልጆቿን ማየት በቂ ነው፡፡ ያልዘራነውን ልናጭድ አንችልም፡፡ እንደተወደደ፣ እንደታየ እና ትኩረት እንደተሰጠው የተረዳ ልጅ ለቤተሰቡና ለሀገሩ ፍሬያማ  ዜጋ የመሆን እድሉ ሰፊ ነው፡፡

ወላጅ ብዙ ጊዜ ልጆቹን ሲያስብ ትልቅ ትኩረት የሚሰጠው ለአካላዊ ጤንነቱና ለትምህርቱ ነው፡፡ በእርግጥ ይህ ጉዳይ በእውነትም ሊያሳስብ ይገባል፡፡ ነገር ግን ለአካሉ እና ለትምህርቱ እንደሚያስበው ሁሉ ለአእምሮ እድገቱና ጤንነቱም መጨነቅ ይገባዋል የሚለው የመጽሐፉ ዋነኛ ይዘት ነው፡፡

በዚህ ወሳኝ ምዕራፍ ወቅት ታዲያ ልጆችን የማክበር ባህል ማሳደግ ያስፈልጋል። የተከበረ ልጅ ራሱን ያከብራል፡፡ ቤተሰቡን ያከብራል። ጎረቤቶቹንና ጓደኞቹን ያከብራል። ሀገሩን ያከብራል፡፡ ከዚህም አልፎ ተከብሮ ያደገ ልጅ ለሀገሩ ለመስራት ሃላፊነቱም፣ ብቃቱም ይኖረዋል፡፡

“ለልጅ ቅድሚያ በመስጠት ገንዘቡን፣ ጊዜውንና ጉልበቱን ያፈሰሰ ቤተሰብና ሀገር የሚያጭደው ትርፍን እንጂ ኪሳራን አይደለም” ሲል ገጽ 45 ላይ በስፋት ዳስሷል፡፡ መጽሐፉ ለዚህ ስኬት ደግሞ ልጆችን መቀበል ዋነኛው ነው ይላል፡፡ “ልጆችን መቀበል ማለት ልጆችን በዘር፣ በእድሜ፣ በጾታ እና በተለያዩ ሁኔታዎች ሳይለያዩ በማንነታቸው እውቅና መስጠትን ይመለከታል ይላል፡፡

በመጽሐፉ ውስጥ የልጅን ተቀባይነት ይገነባሉ ከተባሉ ነገሮች መካከል ደግሞ  ራስን መቀበል ላይ መስራት፣ የልጆችን የእድገት ደረጃ ማወቅ፣ ስብእናቸውን መረዳት ዋነኞቹ ናቸው፡፡ በአንጻሩ ቅቡልነትን  ያጣ ልጅ ለከባድ የህይወት ፈተና ተጋላጭ እንደሚዳርገው መጽሐፉ ያትታል፡፡

ልጅነትና ጨዋታ

ጨዋታ ለልጆች ቅንጦት ሳይሆን ስለራሳቸውና ስለአካባቢያቸው እንዲያውቁ የሚረዳቸው መሰረታዊ ፍላጎት እንደሆነ በመጽሐፉ ገጽ 75 ላይ ሰፍሮ ይገኛል፡፡ አንዳንድ ልጆች ደግሞ የደረሰባቸውን የሥነ ልቦና ጫና በቀጥታ ላይናገሩ ይችላሉ፡፡ ከዚህ ችግር እንዲወጡ ደግሞ ልጆችን ማዕከል ያደረገ ህክምና የሚያስፈልግ ሲሆን፤ ለዚህ ደግሞ ጨዋታ ዋናው ዘዴ ነው ተብሎ ተጠቅሷል፡፡ ምክንያቱም ጨዋታ ልጆች የጭንቀትና የሰቆቃ ሸክምን የሚያቃልል አንዱ የፈውስ መንገድ ነው። መጽሐፉ እንደሚያትተው ጨዋታ የልጆች ቋንቋቸው ሲሆን እየተዝናኑ ለቅርብ ወላጆቻቸው የማይናገሩትን ነገር በጨዋታ መልክ ያወጡታል።

ይህ የጨዋታ ህክምና ዘዴ ልጆች ስሜታቸውንና አመለካከታቸውን እንዲገልጹ፣ የትኩረትና የማስታወስ አቅማቸውን እንዲያሳድጉ፣ የቋንቋ ችሎታቸውን እንዲያዳብሩ፣ ፈጠራቸው ከፍ እንዲል እና በራስ መተማመናቸው እንዲያድግ ያደርጋል፡፡ እነዚህ ብቃቶች እውን እንዲሆኑ ያግዛሉ ተብለው በመጽሐፉ የተጠቀሱት ደግሞ ጭቃ ማቡካት፣ የመገጣጠም ጨዋታ፣ ዳንስ፣ መዝሙርና የመሳሰሉ ጨዋታዎች ናቸው፡፡

ልጆች መዝሙር በሚዘምሩበት ጊዜ የሚረዳቸው፣ የሚራራላቸውና የሚያስብላቸው የቅርብ አምላክ መኖሩን ይረዳሉ፡፡ ብቻቸውን እንዳልሆኑ ይሰማቸዋል፡፡ ተስፋን ይሰጣቸዋል፡፡ በመዝሙር ይጽናናሉ፡፡ ውስጣዊ ሰላም ያገኛሉ፡፡

የወላጅ እና ልጅ መቀራረብ

መጽሐፉ ለዚህ ጉዳይ የሜሪ አይንስዎርዝን ጥናት ጠቅሷል፡፡ አጥኝዋ የሥነ ልቦና ተመራማሪ ስትሆን በዋናነት በወላጅና ልጅ መካከል ያለውን ቅርርብ ጽንሰ ሃሳብ መሰረት በማድረግ ጥናት አድርጋለች፡፡ ጥናቱ እንዳረጋገጠው በጠንካራ የወላጅና ልጅ ስሜት ትስስር ያደረጉ ልጆች ከእንግዳ ሰዎች ጋርም የመቀራረብ እና የመነጋገር ሁኔታ አሳይተዋል፡፡ ምክንያቱም በአንድ ቤተሰብ መካከል ያለው የስሜት ትስስር ለልጆች ሁለንተናዊ እድገት ትልቅ አበርክቶ አለው ይላል መጽሐፉ፡፡ ይህ መስተጋብር ከልጆች አእምሯዊ፣ አካላዊ፣ ስሜታዊ እና ማህበራዊ ኑሮ ጋር በጥብቅ ግንኙነት ይኖራቸዋል፡፡

በመጽሐፉ ጠንካራ መቀራረብ ለመገንባት ይረዳሉ የተባሉ ሃሳቦች በስፋት ተዘርዝረዋል። እነዚህም ልጆች ደህንነት እንዲሰማቸው ማድረግ፣ መታየታቸውንና ለስሜታቸው እወቅና ማግኘታቸውን እንደሚፈልጉ መረዳት፣ የሆኑትን ሆኖ የሚያበረታታቸው ሰው እንደሚፈልጉ ልብ ማለት እና አስፈላጊ እና ዋጋ ያላቸው እንደሆኑ ማወቅ እንደሚሹ ማገናዘብ የሚሉት ናቸው። በወላጅ እና ልጅ መካከል የስሜት ትስስር ይፈጥራሉ የተባሉ ሌሎች ነገሮች ደግሞ የአይን፣ የድምጽ እና አካላዊ ተግባቦት እንዲሁም የፊት ገጽታ ናቸው፡፡

ስነ ምግባር

በአራት ምእራፍ የተከፋፈለው ክቡር ልጆች መጽሐፍ የመጨረሻ ጉዳዩ ያደረገው ስነ ምግባርን ነው፡፡ ልጆችን ለማረም ከመሞከር በፊት ጠንካራ ግንኙት እንደሚያስፈልግ መጽሐፉ ያነሳል፡፡ “ልጆች የሚሰሙት እነርሱ እንደተሰሙ ሲያረጋግጡ ነው” የሚባል አባባል አለ፡፡ ይህ አባባል ልጆች ወላጆቻቸውን ከመስማታቸው በፊት እነርሱ እየተሰሙ እንደሆነ ማረጋገጥ ይፈልጋሉ፡፡ ለዚህም ነው በወላጅ እና ልጆች መካከል ያለው መልካም ግንኙነት ልጆችን ለማረም ቁልፍ ሚና አለው የሚባለው። ይህን ለማድረግ ደግሞ ከልጅ ጋር የጋራ ጊዜ ማሳለፍ፣ ልጅን መስማት፣ መፍትሄ ተኮር ሃሳብ ማንሸራሸር እና ሌሎችም ይገኙበታል፡፡

ደራሲው በማጠቃለያ ሃሳቡ በልጅነትዎ ወቅት ጥሩ ስሜት እንዲሰማዎ ያደረገዎትን ሰው መለስ ብለው ያስታውሱ፤ መልካም ትዝታው ዛሬም ድረስ ይኖራል፡፡ በወላጅ እና ልጅ መካከል አይረሴ ትዝታዎች የሚኖሩት ጥብቅ ቤተሰባዊ ትስስር ሲኖር ነው፡፡ በልጅ አእምሮ ውስጥ መልካም ትዝታ ማኖር የሚችሉ ቤተሰቦች ውጤታማ ናቸው፡፡ በፍቅራቸው እና በመልካምነታቸው፣ በርህራሄያቸው፣ በእንክብካቤያቸው ይታሰባሉ፡፡ ምክንያቱም “የልጅነት ትዝታዎች ዘመን ተሻጋሪ የልብ መዝገቦች ናቸው” ይባላል፡፡

በጊዜው አማረ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review