- ባለፉት አስራ አንድ ወራት 246 ሺህ የሚደርሱ ጎብኚዎች ሙዚየሙን በክፍያ ጎብኝተዋል
- 126 ሚሊዮን ብር ገቢ አስገኝቷል
ሱልጣን ከድር ይባላል፡፡ በዕድሜው ሃያዎቹ መጀመሪያ ላይ የሚገኝ ወጣት ሲሆን፤ የዓድዋ ድል መታሰቢያን 150 ብር ከፍሎ ሲጎበኝ ነበር ያገኘነው፡፡ ወደ ውስጥ ገብቶ ስለተመለከተው እና ስለተፈጠረበት ስሜት፣ “ውስጥ ከገባሁ በኋላ የተመለከትኩት ከገመትኩት በላይ ነው የሆነብኝ፡፡ የሁላችን የጋራ የድል ታሪክ የሆነው ዓድዋን በታሪክ ስንሰማው የነበረውን በቀላሉ ለመረዳት የሚያስችሉ ቅርሶችን፣ ስዕሎችን፣ ሰነዶችን፣ ቅርፃ ቅርፆችን፣ ሃውልቶችን ይዟል፡፡ ስለመታሰቢያው የሚወራውና በተጨባጭ ያለው ነገር መገጣጠሙ በራሱ ለጎብኚ የሚፈጥረው ልዩ ስሜት አለው፡፡” ሲል አብራርቷል፡፡
“ኢትዮጵያ ብዙ ሃብት ያላት ሀገር መሆኗን አንዱ ማሳያ የዓድዋ ድል መታሰቢያ ነው” የሚለው ወጣት ሱልጣን፤ ሀገሪቷ ያላትን ፀጋ በአግባቡ የሚያውቅ፣ ያንንም አልምቶ ወደ ውጤት መቀየር የሚችል አመራር ካለ ሀገርም ሕዝብም በቀላሉ የሚያድጉበት ሁኔታ እንደሚፈጥር አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡ እንደወጣቱ ገለፃ፤ መታሰቢያው በመሃል ፒያሳ የተገነባ የከተማዋም የሀገርም ሃብት ነው፡፡ በውስጡ ከያዘው ታሪካዊ ቅርስ እና ሃብት በተጨማሪ፤ የሕንፃው ንድፍ፣ የግንባታ ጥራት፣ የያዛቸው ቴክኖሎጂዎች በራሱ ጎብኚዎችን መሳብ የሚችል ነው፡፡
ወጣት ሱልጣንን ጨምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ ጎብኚዎች መታሰቢያውን መዳረሻቸው ያደርጉታል፡፡ ስለ ታላቁ የዓድዋ ድል ያላቸውን ዕውቀትና ግንዛቤ የሚያሳድጉበትን ዕድል ይፈጥርላቸዋል። የመጡበት ዓላማ ለስብሰባ፣ ለዓውደ ርዕይ እና በመሰል ሁነት ላይ ለመታደም ከሆነ፤ ለዚህ ምቹ ሆነው የተሰናዱ ዘመናዊ የመሰብሰቢያ አዳራሾች በራቸውን ከፍተው ይጠብቋቸዋል፡፡ ሲደክማቸው አረፍ ብለው የሚዝናኑባቸው ካፌዎች፣ የምግብ እና መጠጥ አገልግሎት መስጫዎች ከተሟላ መስተንግዶ ጋር ዝግጁ ናቸው፡፡ ተሽከሪካሪዎችን ይዘው ከሆነም “የት እና እንዴት አቆማለሁ?” የሚለው በዓድዋ ድል መታሰቢያ አያስጨንቅም፡፡ በአጠቃላይ በሞቀ እንቅስቃሴ ውስጥ ያለው መታሰቢያው ለአካባቢው ብቻ ሳይሆን ለመዲናዋ ትርጉም ያለው የኢኮኖሚ ማዕከል እየሆነ መምጣቱን ለመረዳት በሥፍራው ተገኝቶ መመልከት ይበቃል፡፡

“መታሰቢያው ለአገልግሎት ከበቃ ከአስራ አንድ ወር በላይ አልፎታል። በእነዚህ ወራት ውስጥ ከፍተኛ እንቅስቃሴ ውስጥ መግባት ችሏል። አሁንም ቀጥሏል። ከተማዊ፣ አገር አቀፋዊ፣ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፍ ሁነቶችን የማስተናገጃ ማዕከል ሆኗል። የሀገር ውስጥ እና የውጪ ሀገር ጎብኚዎች ለጉብኝታቸው መዳረሻነት እያገለገለ ይገኛል” የሚሉት የዓድዋ ድል መታሰቢያ ዋና ዳይሬክተር አቶ ግሩም ግርማ በበኩላቸው፤ መታሰቢያው በኢኮኖሚው ዘርፍ እያበረከተ ስላለው አስተዋፅኦ ጠይቀናቸው ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተውናል፡፡ መታሰቢያው ከመገንባቱ በፊት፣ በግንባታ ሂደት፣ ለአገልግሎት ከበቃ በኋላ እና በቀጣይ ያለውን ዕድልም በዘርፍ በዘርፉ አብራርተዋል፡፡
መታሰቢያው በግንባታ ሂደት
“የዓድዋ ድል መታሰቢያ የተገነባበት ቦታ ከግንባታ በፊት ከሃያ ዓመት በላይ በልማት ምክንያት ታጥሮ ያለአገልግሎት የቆየ መሆኑ ይታወቃል፡፡ የቦታውን የቀደመ ሁኔታ እና ገፅታ ከጥቂት ዓመታት በፊት በፒያሳ የመንቀሳቀስ ዕድል የነበረው ሁሉ የሚያስታውሰው ነው፡፡ ቦታው ከሁለት አስርት ዓመታት ለበለጠ ጊዜ ያለአገልግሎት መቆየቱ በራሱ ከተማዋንም ሆነ ሀገሪቷን የሚያሳጣው ኢኮኖሚያዊና መሰል ጠቀሜታ ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ በቦታው ላይ ይህንን የመሰለ ግዙፍ እና ወሳኝ ፕሮጀክት እንዲገነባ ከማቀድ፣ ዕቅዱንም ዕውን እንዲሆን ከማድረግ እና ለዚህ ደረጃ ለማብቃት የተደረሰበት ውሳኔ እና የተሰጠው አመራር የአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ማዕከል ከሆነው ፒያሳ ታጥሮ የቆየውን ውድ ፀጋ አውጥቶ ለመጠቀም አስችሏል” ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በግንባታ ሂደት ውስጥ ያበረከተውን አስተዋፅኦ አስታውሰዋል፡፡
መታሰቢያው በግንባታ ላይ በነበረበት ወቅት ያበረከተው ኢኮኖሚያዊ አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው፡፡ በአጠቃላይ ከ6 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጎበታል፡፡ ይህ ሁሉ የሀገር ገንዘብ ከኢትዮጵያ አልፎ ለጥቁር ሕዝቦች ምልክት ለሆነው የዓድዋ ድል መታሰቢያ ፕሮጀክት መገንቢያ ሆኖ ፈሰስ ሲደረግ፤ ገንዘቡ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በኢኮኖሚ ውስጥ የሚንቀሳቀስበት ዕድል ተፈጥሯል፡፡ በግንባታ ላይ በቆየባቸው አምስት ዓመታት በርካታ የግንባታ ሥራ ተቋራጭ ድርጅቶች፣ ማኅበራት፣ ግለሰቦች በቋሚነት እና በጊዜያዊነት የሥራ ዕድል ተፈጥሮላቸዋል፡፡
ለአገልግሎት ከበቃ በኋላ
የዓድዋ ድል መታሰቢያ ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ግሩም እንዳብራሩት፤ ፕሮጀክቱ ግንባታው ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ከበቃ በኋላም ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ እንደ ተቋም ወደ አገልግሎት መግባቱን ተከትሎ፤ የሚጠበቅበትን አገልግሎት ለመስጠት እንዲችል የሠው ኃይል በማሟላቱ ተግባር ለበርካታ ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል ፈጥሯል፡፡ የሥራ ዕድል ከተፈጠረላቸው ዜጎች መካከል 21 አባላት ያሉት የፎቶ ግራፍ ባለሙያዎች ማኅበር ይጠቀሳል፡፡ የአስተዳደራዊ ሥራውን ለማከናወን ቁጥራቸው 41 የሚሆኑ ዜጎች በአመራርነት እና ባለሙያነት በቋሚነት ተቀጥረውና ተመድበው የሚሠሩበትን ዕድል ፈጥሯል፡፡ በተጨማሪም፤ ቁጥራቸው 33 የሚሆኑ የተለያየ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት (የካፌ፣ የምግብ፣ የመጠጥ፣ የቴሌኮሙኒኬሽን፣ የፋይናንስ፣ የአልባሳት፣ የጌጣጌጥ እና የመሳሰሉት) አገልግሎታቸውን ለተጠቃሚዎች ለመስጠት ያስቻላቸውን ሁኔታ በዓድዋ ድል መታሰቢያ መፈጠሩ የራሱን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም አስገኝቷል፡፡
ተቋማቱ ከሚያገኙት ጥቅም በተጨማሪ፤ ለብዙ ተቀጣሪዎች የሥራ ዕድሎችን ፈጥረዋል፡፡ በአማካይ ከ65 በላይ ሠራተኞች ያሏቸው ሦስት የፅዳት እና የጥበቃ ሥራ ድርጅቶች፤ በዓድዋ ድል መታሰቢያ ውስጥ ያለውን የፅዳት እና የጥበቃ ሥራ በኮንትራት ወስደው በኃላፊነት እየተወጡ ይገኛሉ፡፡ ይህም ከመታሰቢያው ዕውን መሆን ጋር ተያይዞ የመጣ ኢኮኖሚያዊ ትሩፋት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ ምክንያቱም እነዚህ የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸው ዜጎች የሚያገኙት ገቢ ከራሳቸው አልፎ በስራቸው ላሉ ቤተሰቦቻቸው እስከመትረፍ የሚያደርሳቸውን አቅም ፈጥሮላቸዋልና፡፡

ለአዲስ አበባ ከተማ አንድ ሁነኛ የጎብኚዎች መዳረሻ መሆን የቻለው የዓድዋ ድል መታሰቢያ ለአገልግሎት ከበቃ በኋላ በነበሩት አስራ አንድ ወራት ውስጥ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ጎብኚዎች ጎብኝተውታል፡፡ ይህንን በተመለከተ የመታሰቢያው ዋና ዳይሬክተር እንደገለፁት፤ ወደ 246 ሺህ የሚደርሱ ጎብኚዎች መታሰቢያውን በክፍያ ጎብኝተዋል፡፡ ቁጥራቸው ከዚህ በእጅጉ የሚበልጡት (ከክልሎች፣ ከተቋማት፣ የትብብር ደብዳቤ ይዘው የሚመጡ፣ ከትምህርት ቤቶች) ዜጎች ያለክፍያ የጉብኝት መርሃ ግብርን አከናውነዋል። ከፍለው ከጎበኙ፣ ከሱቅ ኪራይ፣ ከአዳራሾች ኪራይ፣ ከመኪና ማቆሚያ (ፓርኪንግ) አገልግሎት ክፍያ፣ ከዓውደ ርዕይ ማሳያ ቦታ ኪራይ እና ከመሳሰሉ አገልግሎቶች በአስራ አንድ ወር ጊዜ ውስጥ ወደ 126 ሚሊዮን ብር ገቢ አስገኝቷል፡፡
የዓድዋ ድል መታሰቢያው ካለው ገቢን የማመንጨት አቅም አንፃር ያስገኘው ገቢ አነስተኛ መሆኑን ያስረዱት አቶ ግሩም፤ “ገቢው፤ መታሰቢያው ካለው ወደ ገንዘብ መቀየር የሚችል አቅም እና ፀጋ አንፃር በጣም አነስተኛ ነው። ያሉትን የመሰብሰቢያ አዳራሾች፣ የዓውደ ርዕይ ማሳያ ቦታዎች፣ በውስጡ የያዛቸውን ታሪካዊ ሃብቶች የመሳሰሉትን በሚገባ ማስተዋወቅ እና መረጃውን ተደራሽ ማድረግ ቢቻል፤ እንዲሁም ገቢ መሳብ እና መጨመር የሚችሉ የገበያ ልማት ሥራዎች ቢከናወኑ፤ ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እና በቅንጅት ቢሠራ የሚገኘው ገቢ አሁን ካለበት በብዙ እጥፍ እንደሚጨምር መገመት አያዳግትም” ብለዋል፡፡
የማይስ ቱሪዝም ዘርፍን ከመደገፍ አንፃር
አዲስ አበባ የማይስ ቱሪዝም ፀጋዎቿን በሚገባ እንዳትጠቀም ካደረጓት ምክንያቶች መካከል ደረጃቸውን የጠበቁ እና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሆኑ የስብሰባ አዳራሾች፣ የዓውደ ርዕይ ማሳያዎች እና ተያያዥ አገልግሎት መስጫዎች በሚፈለገው ልክ አለመሟላታቸው በቀዳሚነት ይጠቀሳል፡፡ የዓድዋ ድል መታሰቢያው ይህን ከመቅረፍ አንፃር እንደ ትልቅ አቅም ተደርጎ የሚወሰድ ነው፡፡
“ከዚህ ቀደምም ሆነ አሁንም ድረስ ለከተማዋ የማይስ ቱሪዝም ዕድገት የማይተካ ሚና የተጫወቱ እና እየተጫወቱ ያሉት ደረጃቸው ከፍ ያሉ ሆቴሎች ናቸው፡፡ እነዚህ ሆቴሎች አነስተኛ መጠን ያላቸውን ስብሰባዎች ለማካሄድ የሚያስችሉ አዳራሾች፣ ለእንግዶች የሚሆኑ ማረፊያዎች፣ የምግብ እና የመጠጥ አገልግሎቶች መስጠት ቢችሉም፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ተሳታፊዎች የሚታደሙባቸውን ትላልቅ መድረኮችን ማሰናዳት ላይ አቅማቸው አልደረሰም፡፡ የመኪና ማቆሚያ (ፓርኪንግ) እጥረት ደግሞ ሌላኛው ችግራቸው ሆኖ ዘልቋል” የሚሉት የመታሰቢያው ዋና ዳይሬክተር አቶ ግሩም፤ የዓድዋ ድል መታሰቢያ በሆቴሎች ላይ የሚታየውን ችግር ጨምሮ የማይስ ቱሪዝም ማነቆዎችን መፍታት በሚያስችል መልኩ ወደ ሥራ መግባቱን ተናግረዋል። በመታሰቢያው ትላልቅ መድረኮችን የማሰናዳትም ሆነ የመኪና ማቆሚያ ስፍራ የማመቻቸት ችግር እንደማይነሳ፣ በአንድ ጊዜ አንድ ሺህ ተሸከርካሪዎችን ማስተናገድ የሚችል ዘመናዊ፣ ፀጥታውና ደህንነቱ የተጠበቀ የመኪና ማቆሚያ እንዳለውም አብራርተዋል፡፡ እንግዶች (ተሰብሳቢዎች) ወደ መታሰቢያው ለስብሰባ በሚመጡበት ወቅት ታሪካዊውን መታሰቢያ የሚጎበኙበትን ዕድል ያገኛሉ፡፡ ይህ ለእነሱ ‘በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ’ እንደማለት ነው፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ከአዳራሽ ኪራይ ጋር በተያያዘ ለግለሰቦች ያወጣ የነበረውን ወጪ በማስቀረት ረገድ መታሰቢያው ትልቅ አበርክቶ እየተወጣ ስለመሆኑ አቶ ግሩም አንስተዋል፡፡ እንደሳቸው ገለፃ ከሆነ፤ የከተማ አስተዳደሩ በርካታ የዘርፍ ተቋማትን እና የልማት ድርጅቶችን ይመራል፡፡ እነዚህ ተቋማት ሥራቸውን በሚያከናውኑበት ወቅት የሚያዘጋጇቸው የተለያዩ መድረኮች አሉ፡፡ ከዚህ ቀደም እነዚህን መድረኮች በአብዛኛው በሚባል ደረጃ በከተማዋ በሚገኙ ትላልቅ ሆቴሎች እንዲሁም ከከተማዋ ወጣ በማለት የሚያከናውኗቸው ነበሩ፡፡ ለዚህ ደግሞ በመንግስት ደረጃ መድረኮችን በብቃት ለማስተናገድ የሚያስችል መሰረተ ልማት በሚገባ አለመሟላቱ እንደ አንድ ክፍተት ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ የዓድዋ ድል መታሰቢያ ለአገልግሎት ከበቃ በኋላ ይህንን የተቋማት ችግር ትርጉም ባለው ደረጃ መፍታት ችሏል፡፡ ለዚህ ማሳያው፤ በመታሰቢያው ከተከናወኑ መድረኮች እና ሁነቶች መካከል ከ60 እስከ 70 ከመቶው የሚሆኑት የከንቲባ ፅህፈት ቤትን ጨምሮ የተለያዩ የከተማ አስተዳደሩ ተቋማት ያከናወኑት መሆኑ ነው፡፡ መታሰቢያው ለተቋማቱ ለሚሰጠው ጥራት ያለው አገልግሎት ምክንያታዊ የሆነና በአንፃራዊነት ተመጣጣኝ የሆነ ክፍያ ያስከፍላል፡፡ ይህም የመንግስት ገቢ ከአንዱ ኪስ ወደ ሌላ ኪስ የሚገባበትን ሁኔታ ፈጥሯል፡፡

“እስከአሁን መታሰቢያው አምጥቷል የሚባለው ውጤትም ሆነ ያስገኘው ገቢ፤ እኛ ለፍተን በሠራነው ሥራ አይደለም፡፡ የዓድዋ ድል መታሰቢያን በሚገባ አጉልተን፣ አስተዋውቀን፣ ዜጎች አዕምሮ ውስጥ እንዲቀመጥ አድርገን፣ የተለያዩ አሠራሮችን በመጠቀም የመጣ ውጤት አይደለም፡፡ ይህንን እንደ ተቋም አመራርና ሠራተኞች ተሰብስበን ተወያይተን አረጋግጠናል” የሚሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ውጤቱ የመጣው ዓድዋ፤ ዓድዋ ስለሆነ ነው፡፡ መታሰቢያው ያለበት ቦታ፣ የታሪኩ ግዝፈት፣ የግንባታው ማራኪነት፣ ምቹነት፣ ዘመናዊነት … በራሱ ተፈላጊነቱን ከፍ አድርጎታል፡፡ ገበያንም ስቧል፡፡ ይህንን ዓድዋ መታሰቢያ በራሱ በልዩነት የያዘውን ውድ ፀጋ እንደ አቅም በመጠቀም፤ ገበያ መሳብ የሚችሉ የአሠራር ሥርዓትን ዘርግቶ መጠቀም ከተቻለ ትልቅ የገቢ ምንጭ መሆን እንደሚችል አያጠያይቅም፡፡ ይህንንም ለማድረግ እንቅስቃሴዎች እንደተጀመሩ ገልጸዋል፡፡
ይህም ሆኖ በመታሰቢያው ያሉ የመሰብሰቢያ አዳራሾችን እና የዓውደ ርዕይ ማከናወኛ ሥፍራዎችን የሚፈልጉ ሀገራዊና ዓለም አቀፍ ተቋማት ቁጥር እየጨመረ ይገኛል፡፡ ከወራት በፊት ቀድመው አዳራሾቹን የሚይዙም ብዙ ናቸው፡፡ ይህንን መረጃ ባገኘንበት ጊዜ (የካቲት አጋማሽ አካባቢ) እንደሰማነው ከሆነ፤ ከሦስት ወራት በኋላ ለሚከናወኑ ስብሰባዎች እና ውይይቶች የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ለመታሰቢያው ክፍያ ፈፅመው እየተጠባበቁ ይገኛሉ፡፡
እንደመውጫ
የዓድዋ ድል መታሰቢያ በኢትዮጵያ የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ውስጥ እንደ አዲስ የመጣ ትልቅ ዕድል መሆኑን የጠቆሙት የቱሪዝም ዘርፍ ምሁሩ አያሌው ሲሳይ፤ መታሰቢያውን ከዚህም በላይ ለመጠቀም መከወን ስለሚገባቸው ተግባራት የሚከተሉትን ምክረሃሳቦች ሰጥተዋል። የጎብኚዎችን ልምድ ማጎልበት ወሳኙ ሥራ በመሆኑ፤ ጎብኚዎች በተደጋጋሚ እንዲጎበኙ መሠራት ይኖርበታል፡፡ የጎብኚዎችን እርካታ ማሳደግ ከተቻለ ተደጋጋሚ ጉብኝቶችን የማድረግ ፍላጎታቸው ይጨምራል፡፡ መታሰቢያው ከጉብኝት እና መሰብሰቢያ ማዕከልነት ባሻገር የጥናትና ምርምር ማዕከልም ሆኖ የማገልገል አቅም ስላለው ይህንን ከትምህርት ተቋማት ጋር በመተባበር መፈፀም ይገባል፡፡
በተጨማሪም፤ የዓድዋ ድል መታሰቢያን ሁሉን አቀፍ የባህል ማዕከል ወደሚሆንበት ደራጃ ማሳደግ ይገባል። የዲጂታል ቴክኖሎጂን በመጠቀም ስለመታሰቢያው መገኛ፣ ይዘት፣ ገፅታ፣ አገልግሎት እና መሰል መረጃዎች የሚሰጥበትን አሠራር መፍጠርና ማስፋፋት ያስፈልጋል፡፡ ይህም ዓለም አቀፋዊ ተደራሽነቱን እና የጎብኝዎችን ተሳትፎ በእጅጉ ለመጨመር ያግዛል። ከሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃኖች በተጨማሪ ዓለም አቀፍ አማራጮችንም መጠቀም ይጠበቅብናል፡፡
በደረጀ ታደሰ