AMN – የካቲት 5/2017 ዓ.ም
የአዲስ አበባ መብራት ኃይል አገልግሎት ንብረት የሆነ የመንገድ መብራት ምሰሶ ለመቁረጥ ሲመክሩ የተያዙ ተከሳሾችን በፅኑ እስራት ማስቀጣቱን የአራዳ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ
ተከሳሾች አስራት የሱፍ እና ፍቃዱ አለቃ ሲባሉ ወንጀሉን የፈፀሙት በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 ልዩ ቦታው አቧሬ ጭንጫ ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ ነው፤ ተከሳሾቹ ጨለማን ተገን በማድረግ ንብረትነቱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መብራት ሀይል አገልግሎት የመንገድ መብራት ምሰሶ የብረት መቁረጫ መጋዝ ወይም ሴጌቶ በመያዝ ለመቁረጥ ሲሞክሩ በአካባቢው የነበረ የጥበቃ ሰራተኛ ለፖሊስ በሰጠው ጥቆማ አማካኝነት ተከሳሾቹ እጅ ከፍንጅ መያዛቸውን የአራዳ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያ አስታውቋል፡፡
ጉዳዩን ሲከታተል የቆየው የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ አምስተኛ ወንጀል ችሎት እንደተሳፏቸው መጠን በተከሳሽ አስራት የሱፍ ላይ በ6ዓመት ከ6ወር እንዲሁም በተከሳሽ ፍቃዱ አለቃ ላይ ደግሞ 1ዓመት ከ6ወር ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡
በህዝብና በመንግስት ሀብት ላይ የሚፈፀሙ ማናቸውንም የወንጀሎች አይነቶች በመከላከል እና በመቆጣጠር ረገድ ህብረተሰቡ እያደረገ ያለው ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትና ጥቆማ በመስጠትም አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግ የአዲስ አበባ ፖሊስ መልዕክቱን ያስተላልፋል፡፡