
AMN ታሕሣሥ 6/2017 ዓ .ም
በአዲስ አበባ ከተማ የመኖሪያ ቤት አቅርቦትን ለመጨመር ከተያዙ የመኖሪያ ቤት አቅርቦት አማራጮች አንዱ በሆነው የመንግስት እና የግል ዘርፍ አጋርነት የመኖሪያ ቤት ልማት መርሃ ግብር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ።
ከንቲባ አዳነች በመንግስት እና የግል ዘርፍ አጋርነት ከሚገነቡ የቤት ልማቶች ትላልቆቹ የሆኑትን 60ሺ ቤቶች የሚገነቡበትን የኦቪድ የገላን ጉራ ሳይት እና 18 ትላልቅ ህንጻዎች የሚገነቡበትን የጊፍት ሪልስቴት የለገሀር ሳይት የግንባታ ሂደት ተዘዋውረው በመጎብኘት አፈጻጸሙን ገምግመዋል።
የከተማዋን የመኖሪያ ቤት ችግር ለማቃለል አስተዳደሩ የተለያዩ የቤት ልማት አማራጮችን በመንደፍ ወደ ትግበራ የገባ ሲሆን ከዚህ ውስጥ አንዱ የሆነው በመንግስት እና የግሉ ዘርፍ አጋርነት የሚከናወነው የቤት ልማት መርሃ ግብር በግሉ ዘርፍ ፋይናንስ አድራጊነት እና በከተማ አስተዳደሩ መሬት እና እስከ ግንባታ ሳይቱ አስፈላጊ መሰረተ ልማቶችን አቅራቢነት እንደሚከናወን ገልጸዋል ከንቲባ አዳነች።
በመርሃ ግብሩ መሰረት ከሚለሙ ቤቶች 70 በመቶ ድርሻውን የግሉ ዘርፍ አልሚ የሚወስድ ሲሆን 30 በመቶውን ደግሞ የከተማ አስተዳደሩ ድርሻ ሆኖ በተለያዩ አማራጮች ለነዋሪው የሚያስተላልፍ ይሆናል።
በማንኛውም የልማት እንቅስቃሴ ለልማት ተነሺ ነዋሪዎች ቅድሚያ እንሰጣለን ያሉት ከንቲባ አዳነች አቤቤ በኦቪድ ገላን ጉራ ሳይት ለልማት ተነሺ አርሶ አደሮች ቅድሚያ በመስጠት ደረጃቸውን የጠበቁ የ770 ቤቶች ግንባታ በመፋጠን ላይ መሆኑን ገልጸዋል።
በመንግስት እና በግሉ ዘርፍ አጋርነት እየለሙ ባሉ ቤቶች በጋራ መኖሪያ ቤት በ40/60 እና 20/80 መርሃ ግብር ተመዝግበው እየቆጠቡ ያሉ ነዋሪዎች ተጠቃሚ የሚሆኑበት ሁኔታ እየታሰበበት መሆኑንም ተናግረዋል።
የቤት ልማት ግንባታው በፍጥነት መካሄድ እንዳለበት ያሳሰቡት ከንቲባ አዳነች በግንባታው ሂደት የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን ለመፍታት የከተማው አስተዳደር አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።
በሰብስቤ ባዩ