AMN – ጥር 01/2017 ዓ.ም
የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ማዕከል ብሔራዊ ጥቅም እና ሉዓላዊ ክብርን ማስጠበቅ መሆኑ የሀገሪቱ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ላይ የተቀመጠ ነው።
የነጮችን የቅኝ ግዛት ፍላጎት ከንቱ በማድረግ ገና ከጥንቱ ሉዓላዊነቷ አይነኬ መሆኑን ለዓለም ያስመሰከረችው ኢትዮጵያ ዛሬም በልጆቿ የዲፕሎማሲ ብልሀት እና አቅም ከዓለም ጋር ይበልጡን ተግባቢ ሆና ቀጥላለች።
በዚህም ምክንያት በተፈጥሮ ያላት ጂኦ ፖለቲካዊ አቀማመጥን ተከትሎ የተፈጠሩ ጠላቶችን ሳይቀር ድል ያደረገ አስደማሚ ዲፕሎማሲያዊ ስኬትን እየተጎናፀፈችም ትገኛለች።
መንግሥት ባለፉት 6 ዓመታት በዲፕሎማሲው ዘርፍ በርካታ ስኬቶችን ማስመዝገቡን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል በተለያዩ ጊዜያት ለመገናኛ ብዙኃን የሰጠው መረጃ ያመለክታል።
በተለይም መንግሥትን የሚመራው የብልፅግና ፓርቲ አካሂዶት በነበረው የመጀመሪያው ጉባኤ ላይ የኢትዮጵያን ክብር እና ጥቅም በተግባር በሚያስጠብቅ መንገድ ላይ ጠንካራ የዲፕሎማሲ ሥራዎችን መሥራት እንደሚጠበቅ አቅጣጫ ማስቀመጡ ስኬት ለተመዘገበበት የዲፕሎማሲው ዘርፍ መሠረት ጥሏል።
ከጉባኤው ውሳኔ በኋላ ኢትዮጵያ ከሌሎች ሀገራት ጋር ያላት ግንኙነት እየተጠናከረ መምጣቱ እሙን ነው።
የባለ ብዙ ወገን የዲፕሎማሲ ሥራ እና የኢትዮጵያ ብሪክስ አባል መሆን እንዲሁም የአንካራው ስምምነት ትልቅ የዲፕሎማሲ ድል ናቸው።
በዜጋ ተኮር የዲፕሎማሲ ሥራዎችም በተለያዩ ሀገራት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ዜጎች መመለስም ሌላኛው ውጤት ነው።
የዓለም አቀፉ የጥቁር ሕዝቦች የታሪክ፣ ቅርስ እና የትምህርት ማዕከል ዋና መቀመጫውን አዲስ አበባ ማድረጉም የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ ማዕከልነት ያፀና ሆኗል።
የፓርታው ውሳኔ ኢትዮጵያ የምትከተለው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም ከማስጠበቅ አልፎ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ፋይዳ እንዲኖረውም አስችሏል።
ለዚህም በአሜሪካ-አፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ ላይ የኢትዮጵያ አበርክቶ ጎልቶ መውጣት፣ አፍሪካዊ መፍትሔዎች የተገኙበት የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ እና ኢትዮጵያ ለአረንጓዴ ልማት ሥራ ትኩረት በመስጠት እየሠራች ያለውን ሥራ ዓለም የተረዳበት የፓሪሱ አዲስ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ስምምነት ጉባኤ ተጠቃሽ አብነቶች ናቸው።
በርካታ የመግባቢያ ስምምነቶች የተደረሱበት የሩሲያ-አፍሪካ ጉባኤ እና የኢትዮጵያ የʻብሪክስʼ አባልነት ጥያቄ ተቀባይነት ማግኘትም ከብልፅግና ፓርቲ የመጀመሪያው ጉባኤ ውሳኔ ወዲህ የተመዘገበ ድል ነው።
ለ11 ዓመታት ድርድር የተካሄደበት የናይል የትብብር ማዕቀፍ በአብላጫ ድምፅ መፅደቁም ለኢትዮጵያ ትልቅ የዲፕሎማሲ ስኬት ሆኗል።
ኢትዮጵያ የትብብር ማዕቀፍ ለማዘጋጀትም ሆነ ማዕቀፉ በናይል ተፋሰስ ሀገራት እንዲፈረም ጥበብ የተሞላበት ዲፕሎማሲዊ ጥረት እና ተጋድሎ አድርጋለች።
በጥቅሉ ኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿ፣ በሩቅ እና በቅርብም ካሉት የዓለም ሀገራት ጋር ያላት አዎንታዊ ተግባቦት ጠንካራ የዲፕሎማሲያዊ ሥራዎችን መሥራት እንደሚጠበቅ መሪው ፓርቲ ባካሄደው የመጀመሪያ ጉባኤው ያስቀመጣቸው አቅጣጫዎች እና ውሳኔዎች ተፈፃሚ መሆናቸውን አመላካች ነው።
ከሰላም አንፃር በበርካቶች ዘንድ አድናቆት የተቸረው የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እና የዜጎችን ደኅንነት ለማረጋገጥ ጉባኤው ያሳለፋቸው ውሳኔዎችን ተፈፃሚነት አጉልተው የሚያሳዩ አብነቶች ሆነው የሚጠቀሱ ናቸው።
ፓርቲው በቅርቡ በሚያካሂደው ሁለተኛ ጉባኤውም ሀገርን ወደ ፊት የሚያራምዱ፣ ኢትዮጵያ በአህጉር እና በዓለም አቀፍ መድረኮች ተሰሚነቷ ጎልቶ እንዲታይ የሚያደርጉ ዲፕሎማሲ ነክ ጉዳዮችን በጥልቀት ተመልክቶ አቅጣጫ እንደሚያስቀምጥ ይጠበቃል።
በማሬ ቃጦ