የመጋቢት 24ን ፍሬዎች በሁሉም የኢትዮጵያ መንደሮች ለማድረስ ተግተን እንሰራለን – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

You are currently viewing የመጋቢት 24ን ፍሬዎች በሁሉም የኢትዮጵያ መንደሮች ለማድረስ ተግተን እንሰራለን – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

AMN – መጋቢት 24/2017 ዓ.ም

የመጋቢት 24ን ፍሬዎች በየአንዳንዱ የኢትዮጵያ መንደሮች ለማድረስ ተግተን እንሰራለን ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የመጋቢት 24 ትሩፋቶች እና ሀገራዊ ለውጡን አስመልክተው ያስተላለፉት መልዕክት ሙሉ ቃል ከዚህ እንደሚከተው ቀርቧል:-

መጋቢት 24 በዘመናዊቷ ኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ልዩ ቦታ አላት፡፡ ትናንትን እና ዛሬን፤ ዛሬን እና ነገን፤ የዳርና የመሐልን፤ ግንባር እና አጋርን፤ አርሶ እና አርብቶ አደርን፣ ግለሰብና ቡድንን፣ አካቢያዊ እና ሀገራዊ ማንነትን፣ በመደመር ዕሳቤ ያግባባች ቀን ናት፡፡

ከዕዳ ወደ ምንዳ ለመጓዝ መነሻ ሆናለች፡፡ ለመፍጠርና ለመፍጠን የሚያስችል ዐውድ ዘርግታለች፡፡ በገበታ ለሸገር፣ በገበታ ለሀገር፣ በገበታ ለትውልድ አማካኝነት ሀገር የሚቀይሩ ፕሮጀክቶች ተጀምረው እንዲጨረሱ፤ ተጠናቅቀው እንዲመረቁ አስችላለች፡፡

እንደ ሕዳሴ ግድብ ያሉ ሀገራዊ ሐሳቦች ከዕንቅፋት ተርፈው ለብርሃን እንዲበቁ አድርጋለች፡፡

በይቅርታ እንሻገር፣ በፍቅር እንደመር፤ ጽዱና አረንጓዴ ኢትዮጵያ፤ አረንጓዴ ዐሻራ፤ ዲጂታል ኢትዮጵያ፤ የሌማት ትሩፋት፣ የምግብ ሉዓላዊነት፤ የትምህርት ቤት ምገባ፤ የኮሪደር ልማት፤ ወዘተ. ተነሣሽነቶች የመጋቢት 24 ውጤቶች ናቸው፡፡

የትምህርት ሪፎርም፤ የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም፤ የውጭ ግንኙነት ሪፎርም፤ የጸጥታ ተቋማት ሪፎርም፤ የፍትሕ ተቋማት ሪፎርም፤ የዴሞክራሲ ተቋማት ሪፎርም፤ የሚዲያ ሪፎርም፤ ወዘተ… የመጋቢት 24 ፍሬዎች ናቸው፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ትናንት እየራቀ፣ ነገ እየቀረበ ነው፡፡

ኢትዮጵያ በዓለም ላይ ተገቢዋን ቦታ ለመያዝ ተቃርባለች፡፡

በመደመር ጎዳና፣ ኢትዮጵያን ወደ ብልጽግና ለማድረስ የተጀመሩት ሥራዎች ሁሉ ፍሬያቸውን ማሳየት ጀምረዋል፡፡

ኢትዮጵያ በድህነትና ኋላቀርነት ይነሳ የነበረው ስሟ በስንዴ፣ አረንጓዴ አሻራ፣ ታላቁ የህዳሴ ግድብ፣ የቱሪስት መዳረሻ ምቹ ቦታዎች፣ በፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ወዘተ… በጎ ገፅታዎች መጠራት ጀምሯል።

ዘርፈ ብዙ የመጋቢት 24 የለውጥ ፍሬዎችን መከባከብና ማስፋፋት ብቻ ሳይሆን ፍሬዎችን ከጃርቶች እና ከቀበሮዎች መጠበቅም አለብን፡፡

ማንም ከመዳረሻችን አያስቀረንም፡፡ ማንም እንዲያዘገየንም አንፈቅድም፡፡ በሚወረወሩብን ድንጋዮች ብልጽግናን እንገነባበታለን፡፡ የመጋቢት 24ን ፍሬዎች በየአንዳንዱ የኢትዮጵያ መንደሮች ለማድረስ ተግተን እንሰራለን፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review