የሙስና ወንጀልን በተቋማዊ አሰራር በጽናት መታገልና በዘላቂነት መከላከል ይገባል ፡-ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ

AMN – ታኅሣሥ -2/2017 ዓ.ም

የሙስና ወንጀልን በተቋማዊ አሰራር በጽናት መታገልና በዘላቂነት መከላከል ይገባል ሲሉ የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ ገለጹ።

የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ በተገኙበት 21ኛው ዓለም አቀፍ የፀረ-ሙስና ቀን የማጠቃለያ መድረክ በአድዋ መታሰቢያ ተካሂዷል።

በመርኃ ግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት ፕሬዝዳንቱ፥ የሙስና ወንጀል የቆዩ ማህበራዊ ጥረቶችና ወረቶችን የሚያሽመደምድ እና ከድህነት የመውጣት ተስፋን የሚያቀጭጭ በመሆኑ የጋራ ትግል ይጠይቃል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ለሙስና ባህላዊና ሃሳባዊ ሽፋን ሲሰጠው መቆየቱን አስታውሰው፦ወንጀሉ ከሚያስከትለው ውስብስብ ችግር አንጻር በመደበኛ ክስ እና ምርመራ ለመፍታት ቀላል አለመሆኑን አንስተዋል።

በመሆኑም የሙስና ወንጀልን በተቋማዊ አሰራር በጽናት መታገልና በዘላቂነት መከላከል ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በሁሉም ረገድ ልማትን በማስቀጠል ብልፅግናዋን እውን ለማድረግ እየሰራች መሆኑን አንስተው፥ ለዚህ ዋነኛ እንቅፋት የሆነውን ሙስና መከላከልና መታገል ተገቢ መሆኑን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ መሻት እውን እንዲሆን በዋነኝነት ወጣቶችን መሰረት ያደረገ አሰራር በመዘርጋት ዘላቂ ልማትና እድገትን ማረጋገጥ ተገቢ መሆኑንም ተናግረዋል።

የትምህርት ተቋማት ከመደበኛ የመማር ማስተማር ጎን ለጎን ስነ ምግባር እና ሞራል ላይ በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባም ፕሬዝዳንቱ አስገንዝበዋል።

የመገናኛ ብዙሃንም ሙስናን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት የላቀ ሚናቸውን መወጣት ይገባቸዋል ነው ያሉት።

በመድረኩ ፕሬዝዳንቱን ጨምሮ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እውነቴ አለነ፣ የምክር ቤት አባላት፣የፌደራል የስነ-ምግባር እና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ሳሙኤል ኡርቃቶ (ዶ/ር)፣ ሚኒስትሮች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች መገኘታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

21ኛው ዓለም አቀፍ የፀረ-ሙስና ቀን “ወጣቶችን ያማከለ የፀረ-ሙስና ትግል የነገን ስብዕና ይገነባል” በሚል መሪ ሃሳብ ሲከናወን ቆይቷል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review