ኮሌጁ፣ በከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ ተሰማርቶ ዜጎች ላይ ሁለንተናዊ ጉዳት እያደረሰ በመሆኑ፣ ከዚህ ተግባሩ እንዲቆጠብ እና የከፍተኛ ትምህርት አገልግሎት መስጠት እንዲያቆም በባለስልጣኑ የተወሰነበትን ውሳኔ ተግባራዊ ማድረግ እንዳልቻለ ባለስልጣኑ ሲያሳስብ መቆየቱም ተጠቅሷል፡፡
ኮሌጁ በዋና ማዕከሉ አዲስ አበባ እና በተለያዩ የሀገራችን ክልሎች በባሌ ሮቤ፣ በሀዋሳ፣ በአርባምንጭ፣ በሳውላ፣ በወላይታ ሶዶ፣ በጋምቤላ፣ በጊምቢ፣ በጅማ፣ በሆሳዕና፣ በነቀምቴ፣ በቴፒ፣ በጀግጅጋ፣ በቻግኒ እና በባህር ዳር የቅርንጫፍ ማዕከላት በቅድመ ምረቃ ደረጃ ከሀምሌ 2004 ዓ.ም እስከ ሰኔ 2007 ዓ.ም ፈቃድ ባገኘባቸው ከተሞች እና የትምህርት መስኮች በርቀት መርሀ ግብር ሲያስተምር የቆየ ቢሆንም በፈፀመው የህግ ጥሰት ምክንያት ማስተማሩን አንዲያቋርጥ መደረጉን ባለስልጣኑ ለኤኤምኤንኤ ዲጂታል ገልጿል፡፡
በዚህም መሰረት ባለስልጣኑ ግንቦት 20 ቀን 2017 ዓ.ም ለሁሉም ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤቶች፣ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽ/ቤት፣ ፍትህ ቢሮ፣ ለፖሊስ ኮሚሽን፣ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሲቨል ሰርቪስ ኮሚሽን እና ለንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ንግድ ጽ/ቤት በፃፈው ደብዳቤ፣ በኮሌጁ ላይ አስፈላጊውን የህግ ማስከበር እርምጃ በመውሰድ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጠይቋል።
ባለስልጣኑ እስከ 2007 ዓ.ም ድረስ የተቀበላቸውን ተማሪዎች እንዲያስጨርስና በህጋዊ አግባብ የተመረቁ ተማሪዎችን መረጃ ፈቃድ ወዳለው የከፍተኛ ትምህርት ተቋም እንዲያዘዋወርና ለባለስልጣኑ ሪፖርት እንዲያደርግ በተደጋጋሚ ኮሌጁን መጠየቁን አስታውሷል።
ይሁን እንጂ ተቋሙ የተላለፈበትን ውሳኔ ተግባራዊ እያደረገ ባለመሆኑ ከላይ በደብዳቤው የተገለጹ የመንግስት አካላት በተቋሙ ላይ አስፈላጊውን የህግ ማስከበር እርምጃ እንዲወስዱ ጠይቋል፡፡