የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የነዋሪውን ቀጥተኛ የህዝብ ውክልና ተቀብሎ ወደ ስራ ከገባ ወዲህ በርካታ ውጤታማ ተግባራት ማከናወኑን አስታውቋል።
በተለይ በባለ በጀት ኦዲት ተደራጊ ተቋማት ላይ በዋና ኦዲተር ግኝት ተገኝቶባቸው እርምት እርምጃ ያልወሰዱ ተቋማትን ተከታትሎ የመንግስትን ሀብት የሚያስመልሰውና በምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ የሚመራው የኦዲት ፎረም ውጤታማ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ፎረሙ በዛሬው ዕለትም የበጀት ዓመቱን ሁለተኛ ስብሰባውን የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤና የፎረሙ ሰብሳቢ ወ/ሮ ቡዜና አልከድር በተገኙበት አካሂዷል።
በመድረኩም ከ2011 እስከ 2013 ዓ.ም ድረስ በከተማ አስተዳደሩ በተለያዩ ተቋማት የተከማቹ የኦዲት ግኝቶችን ለማጥራትና እርምጃ ለመውሰድ በሁለት ዙር ከተለዩ 134 ተቋማት ውስጥ 111 ተቋማት ለፎረሙ ምላሽ የሰጡ መሆናቸውና ከነዚህ ውስጥ 41 ተቋማት ምላሽ ያለመስጠታቸው በቀረበው የቴክኒክ ኮሚቴው ሪፖርት ተመላክቷል።
በዚህም የፎረሙ ሰብሳቢ አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ቡዜና አልከድር፤ የሚታዩ የኦዲት ግኝቶችን ቀድሞ ከመከላከል አንፃር የተጀመረውን የውስጥ ኦዲት አደረጃጀት የማጠናከር ስራን በልዩ ትኩረት መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በሌላ በኩል ለፋይናንስ አሰራር እክል የሆኑ የተወዘፉ እና ራይት ኦፍ የሚደረጉ ግኝቶችን የሚያጠራና የሚያስተካክል ንዑስ ኮሚቴ እንዲቋቋምና በአፋጣኝ ወደ ስራ እንዲገባ ሃሳብ ቀርቧል፡፡
እንዲሁም እርምጃ ያልወሰዱ ተቋማትንም በሚመለከት የምክርቤቱ የመንግስት በጀት አስተዳደርና ቁጥጥር ቋሚ ኮሚቴ ገምግሞ በአጭር ጊዜ ሪፖርት እንዲያደርግ እና ይህን አቅጣጫም የክፍለ ከተማ ምክር ቤቶችም እስከ ታችኛው መዋቅር እንዲያስተባብሩ የሚል የውሳኔ ሀሳብ ቀርቧል፡፡
የውሳኔ ሃሳቡንም ፎረሙ በሙሉ ድምጽ አጽድቆታል፡፡
በወንድማገኝ አሰፋ