የሚዲያ ሚና ለሀገር ግንባታ

ߵየሚዲያና የኮሙኒኬሸን ስራዎች ተቀናጅተው ለሀገር ግንባታ አዎንታዊ ድርሻ አበርክተዋልߴ

                              በብልፅግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ

አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክም በአርዓያነት የሚወሳ ተግባር አከናውኗል

የሚዲያና የኮሙኒኬሸን ስራዎች ተቀናጅተው ለሀገር ግንባታ አዎንታዊ ድርሻ አበርክተዋል፣ አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክም በአርዓያነት የሚወሳ ተግባር አከናውኗል ሲሉ በብልፅግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅ/ፅ/ቤት ኃላፊ እና የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ የቦርድ ሰብሰቢ አቶ ሞገስ ባልቻ ተናገሩ፡፡

የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ በየደረጃው  የሚገኙ ኃላፊዎች እና ሰራተኞች “የተደራጀ ኮሙኒኬሽንና ሚዲያ የሀገራዊ መግባባት ካስማ ፤ የትውልድ ግንባታ መሰረት ነው” በሚል ርዕስ በወቅታዊ፣ ከተማዊና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት ተካሂዷል። በውይይቱ ላይ የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ የስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ሞገስ ባልቻ፣

የሚዲያው የማኔጅመንት አባላት እንዲሁም አጠቃላይ የሚዲያ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።

የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ካሳሁን ጎንፋ በበኩላቸው መብትና ግዴታውን የሚያውቅ ትውልድ ለመቅረፅና በሀገር ግንባታ ሂደት አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ እያደረገ የሚገኘውን ብርቱ ጥረት ባቀረቡት የመወያያ ሰነድ ላይ ገልጸዋል።  ህዝቡ ለሀገር ግንባታው አሻራውን እንዲያሳርፍ፣ የከተማዋ ፈጣን ዕድገት ተጠናክሮ እንዲቀጥል አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ የድርሻውን እየተወጣ እንደሚገኝ ያስረዱት አቶ ካሳሁን የከተማ አስተዳደሩ እያደረገ ለሚገኘው ያልተቆራረጠ ድጋፍ አመስግነዋል።

አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ህብረ ብሔራዊነትን እያረጋገጠ፣ ተደራሽነትን እያሳደገ በአበረታች ሪፎርም ላይ የሚገኝ ተቋም መሆኑን የገለፁት የውይይቱ ተሳታፊዎችም በከተማና በሀገርአቀፍ ደረጃ በየቀኑ እየተመዘገቡ የሚገኙ አዳዲስ ስኬቶችን በማሳወቅ፣ ሀገር አፍራሽ ሀሰተኛ መረጃዎችን በማጋለጥ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ገልፀዋል።

የሀሳብ የበላይነት የማይከበርበት፣ መጠላለፍ የሚስተዋልበት የፖለቲካ ስብራት ተፈጥሮ ያለንን ፀጋ በአግባቡ እንዳንጠቀም አድርጎን ቢቆይም በለውጡ መንግስት እየተተገበረ በሚገኘው ከነባራዊ ሁኔታው ጋር የተጣጣመ እሳቤ ስብራቶች እየተጠገኑ ተጨባጭ ውጤቶች እየተመዘገቡ መሆኑንም ጠቅሰዋል አቶ ሞገስ፡፡

አዲስ አበባን የብልፅግና ተምሳሌት እናደርጋታለን የሚለው እሳቤ በህዝብ ዘንድ ሰርፆ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ አበርክቶ ላቅ ያለ ስለመሆኑም ገልጸዋል። ሚዲያው አዲስ አበባ ያስመዘገበችውን ሁለንተናዊ ለውጥ አጉልቶ በማውጣት እንደ ሚዲያ የተወጣው ኃላፊነት የሚያስመሰግነው ስለመሆኑም የተቋሙ ስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ሞገስ ባልቻ ተናግረዋል። በለውጥ ጎዳና ላይ የምትገኘውን አዲስ አበባ ከተማን በየቀኑ የምታስመዘግበውን ለውጥ በማነፍነፍ አዳዲስ መረጃዎችን እያደረሰ የሚገኝ ሚዲያ ነውም ብለዋል።

የተሳሳቱ መረጃዎችን መታገል ሀገር ወዳድ ከሆነው የሚዲያ ባለሙያ እንደሚጠበቅ የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ካሳሁን ጎንፋ ተናግረዋል፡፡ ዋና ሥራ አስፈፃሚው በሀገር እና በከተማ ደረጃ ለተመዘገቡ ውጤቶች የሚዲያ ባለሙያው አስተዋፅኦ የላቀ መሆኑን በማውሳት ይህም ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አሳስበዋል።

የሚዲያ ባለሙያው የሙያ ሥነ-ምግባርን የጠበቁ ተዓማኒ መረጃዎችን ለህዝቡ ተደራሽ ማድረግ አለበት ያሉት አቶ ካሳሁን ከጋዜጠኞች ከወገንተኝነት የፀዳ እንዲሁም ሙያ እና ህዝብን መሰረት ያደረገ ዘገባ እንደሚጠበቅ አጽንዖት ሰጥተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ገፅታ መለወጥ ለሀገራችን ገፅታ መዳበር ጉልህ ሚና እንዳለው የጠቀሱት አቶ ሞገስ የከተማችንን ጥልቅ ጉስቁልና በመቀየር፣ የመጥፎ ነገር ማጣቀሻ ከመሆን በማውጣት፣ የፈጣን ልማት ተምሳሌት እንድትሆን እየተደረገ ላለው ርብርብ እና እየተመዘገበ ለሚገኘው አንፀባራቂ ውጤት አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ቅንጅታዊ ርብርቡን ይበልጥ ሊያጠናክር እንደሚገባም ጠቁመዋል።

ከተማችን በፈጣን ዕድገት ላይ ስለምትገኝ ይህንን የሚመጥን የሚዲያና የህዝብ ግንኙነት ስራ እንደሚጠበቅ የጠቀሱት አቶ ካሳሁን የሀገራት መሪዎች ጭምር ምስክርነታቸውን እየሰጡት የሚገኘው ልማት ይበልጥ እንዲሰፋ ቅንጅታዊ ርብርብን ማጠናከር እንደሚገባ አስገንዝበዋል። ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር፣ የኑሮ ውድነቱ እንዳይባባስ በከተማችን የተከናወኑ ሰፋፊ ተግባራት፣ የህዝባችንን ህይወት በማሻሻልና የከተማችንን ውብ ገፅታ በመገንባት በኩል የኮሪደር ልማቱ እያመጣ የሚገኘው አበረታች ውጤት እንዲሁም ሌሎች ሰው ተኮር ተግባራት ከሚዲያ ባለሙያዎች የተሰወሩ እንዳልሆኑ የጠቀሱት ዋና ስራ አስፈፃሚው ይበልጥ እንዲጠናከሩ መትጋት ይገባል ብለዋል።

በድህረ እውነት ዓለም ሀሳብን በነፃነት የመግለፅን መብት ሀሰተኛ መረጃዎችን እንደፈለጉ የማሰራጨት ገደብ አልባነት የሚያስመስሉ አካላትን በትክክለኛ መረጃ መታገል እንደሚገባም አመላክተዋል። አክለውም በኃላፊነትና በመልካም ስነ ምግባር በመስራት፣ ለጋዜጠኝነት ሙያ ተገቢውን ክብር በመስጠት ለከተማችንና ለሀገራችን ከፍታ አሻራን ማሳረፍ እና ማህበራዊ መስተጋብርን የማጠናከር ኃላፊነትን በአግባቡ መወጣት እንደሚገባም አሳስበዋል። በኤዲቶሪያል ፖሊሲው በመመራት፣ ሚዛናዊነትን በመላበስ ፣ ግልፀኝነትን እና ተጠያቂነትን ተግባራዊ በማድረግ ትክክለኛና ወቅታዊ መረጃን ተደራሽ ማድረግ እንደሚገባም አቶ ካሳሁን አስገንዝበዋል።

የከተማ አስተዳደሩ አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ እንዲጠናከር እያደረገ ያለውን ድጋፍ ይበልጥ እንዲያጠናክር ጥያቄዎቻቸውን ያቀረቡት የውይይቱ ተሳታፊዎች አዲስ አበባን የብልፅግና ተምሳሌት በማድረግ የህዝባችንን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል እየተደረገ የሚገኘው ጥረት ተጠናክሮ እንዲቀጥል እንደ ዜጋም እንደ ሚዲያ ባለሙያም ድርብ ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡም አረጋግጠዋል።

የከተማ አስተዳደሩ ለህዝባችን ዘላቂ ተጠቃሚነት በዳበረ የስራ ባህል ቀን እና ሌት እየተጋ እንደሚገኝ የገለፁት አቶ ሞገስ በከተማችን ሁለንተናዊ ሪፎርም አገልግሎት አሰጣጡ ላይ አመርቂ ውጤት ለማስመዝገብ ለተጀመረው ርብርብ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባም አስገንዝበዋል። አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ተደራሽነቱንና ተወዳዳሪነቱን በማሳደግ ለህዝባችን የኑሮ ደረጀ መሻሻል፣ ለሰላም ግንባታው እና ለልማት የሚጠበቅበትን እንዲወጣ በከተማ አስተዳደሩ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል። አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክም የጀመረውን ተግባር አጠናክሮ እንዲያስቀጥልም ነው የተቋሙ የስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢው አቶ ሞገስ ባልቻ ያሳሰቡት።

አንዳንድ አካላት በማህበራዊ ሚዲያዎች ጭምር የተዛባ መረጃ በማናፈስ ወንድማማችነትንና ህብረ ብሄራዊነትን ለመናድ ጥረት እያደረጉ መሆናቸዉን የጠቆሙት አቶ ሞገስ ባልቻ መሬት ላይ ያለው እውነት ኢትዮጵያዊያንን ይበልጥ የሚያቀራርብ መሆኑን አንስተዋል፡፡ እንደዚሁም ጥቂት የግል ጥቅም አሳዳጅ ሀይሎች ለሚፈጥሩት አፍራሽ አጀንዳ ጆሮ ባለመስጠት ኢትዮጵያን ወደታየላት ከፍታ የማድረስ የጋራ ሀላፊነት እንዳለብን ተገንዝበን ትጋታችንን መቀጠል ይኖርብናል ሲሉ አሳስበዋል፡፡

በሳህሉ ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review