“ዓላማ ተኮር ተግባቦት ለሀገር ግንባታ” በሚል መሪ መልእክት የፌዴራል ተቋማት የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን የሥራ ኃላፊዎችና ከፍተኛ ባለሙያዎች ውይይት ተካሂዷል፡፡
በአፍሪካ የአመራር ልሕቀት አካዳሚ ዛሬ የተካሄደዉ የውይይት መድረክ ላይ የዘርፉን አጠቃላይ አቅጣጫ ያመላከቱት የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሠ ቱሉ (ዶ/ር) ባለፉት ጥቂት የለውጥ ዓመታት በተመዘገቡ ሁለንተናዊ ስኬቶች የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ ጉልህ ሚና መጫወቱን አውስተዋል፡፡
ኢትዮጵያ በተፈጥሮ እና ሰው ሠራሽ ችግሮች እየተፈተነች ወደ ለውጥ ምዕራፍ በገባችበት ወቅት ብዝኃነትን የሚያስናግድ የፖለቲካ ምኅዳር እውን እንዲኾን፣ ለዘመናት በተጠራቀመ የዕዳ ጫና ውስጥ የነበረዉ ኢኮኖሚ በስኬት ሪፎርም እንዲደረግ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየናረ የነበረዉ የዋጋ ግሽበት እንዲቀንስ፣ ሰው ተኮር ማኅበራዊ አገልግሎቶች እንዲስፋፉ እና ጥራታቸዉ እንዲሻሻል፣ የመረጃ እና የሐሳብ ነፃነት እንዲረጋገጥ በተሠሩ ሁሉን አቀፍ የሪፎርም ሥራዎች ሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ ጉልህ ሚና መጫወቱን ዶክተር ለገሠ አንስተዋል፡፡
ይሁን እንጅ ከዓለማቀፋዊ ነባራዊ ሁኔታዎች መለዋወጥ እና ከተጀመሩ ዘርፈ ብዙ የለውጥ ሐሳቦች ስር አለመስደድ አንጻር የሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ዘርፉ አመለካከት የመቅረጽ፣ ብሔራዊ ጥቅሞችን የማስገንዘብ፣ የመንግሥትን ፖሊሲና ዕቅድ የማስተዋወቅ እና የማስረጽ ሚናውን በላቀ ደረጃ መወጣት አለበት ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከነበረችበት ዳገት እየወጣች እንደምትገኝ ያመለከቱት ሚኒስትሩ ለውጡን ከማጽናት ወደ ማንሰራራት ለማሸጋገር በሁሉም የሚዲያ አማራጮች ምልዓተ ሕዝቡን በማሳወቅ በመረጃ ላይ ተመሥርቶ እንዲወስን ማነሣሣት እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡
ለዚህም የዘርፉን ዐቅም በዕውቀት በአመለካከት፣ በክሕሎት እና በሚዲያ ቴክኖሎጂ ማሳደግ ትኩረት እንደተሰጠ መግለፃቸውን የአገልግሎቱ መረጃ ያመለክታል።