የማህበረሰብ መገናኛ ብዙሃን በሰላም ግንባታ ሂደት ከፍተኛ ሚና ሊጫወቱ ይገባል- የሰላም ሚኒስቴር

You are currently viewing የማህበረሰብ መገናኛ ብዙሃን በሰላም ግንባታ ሂደት ከፍተኛ ሚና ሊጫወቱ ይገባል- የሰላም ሚኒስቴር

AMN – ታኅሣሥ 8/2017 ዓ.ም

የማህበረሰብ መገናኛ ብዙሃን ለማህበረሰቡ የመረጃ ምንጭ ከመሆን ባለፈ በሰላም ግንባታ ሂደት ውስጥ ከፍተኛ ሚና ሊጫወቱ ይገባል” ሲሉ የሰላም ሚኒስትር አቶ መሐመድ እድሪስ ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ከሰላም ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በሰላም ግንባታ ዙሪያ ለማህበረሰብ መገናኛ ብዙኃን ኃላፊዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ውይይት በቢሾፍቱ ከተማ አካሂዷል።

በመድረኩ የሰላም ሚኒስትር አቶ መሐመድ እድሪስ፤ የማህበረሰብ መገናኛ ብዙሃን ለማህበረሰቡ የመረጃ ምንጭ ከመሆናቸው ባለፈ በሚደረገው የሰላም ግንባታ ሂደት ውስጥ ከፍተኛ ሚና ሊጫወቱ እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡

ትልቁ ስኬት ችግር ከተፈጠረ በኋላ ችግሩን ለማብረድ መሞከር ሳይሆን፣ ችግር ከመፈጠሩ በፊት የመከላከል ስራ መስራት እንደሆነም አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናታን ተስፋዬ፣ በበኩላቸው በውይይቱ የተሳተፉ የማህበረሰብ መገናኛ ብዙሃን ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ወደ መጡበት ሲመለሱ በመገናኛ ብዙኃኑ የሚተላለፈው ሀሳብ ላሉበት አካባቢ ብቻ የሚሰራ ሳይሆን እንደሀገር ሁሉንም የሚያስማማ ሀሳብ የሚንፀባረቅበት ሊሆን ይገባል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በመድረኩ ለተሳታፊዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሰነድ ቀርቦ ውይይት መደረጉን ከኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

*በመገናኛ ብዙኃን ይዘቶች ላይ የህግ ጥሰት፣ የሙያ ስነ-ምግባር ግድፈት፣ የጥላቻ ንግግር እና የሐሰተኛ መረጃ ሲመለከቱም በ9192 ነፃ የስልክ መስመር በመደወል እንዲያሳውቁም ተጠቁሟል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review