አቶ ልዑል ተፈሪ በተቀጠሩበት የስራ መስክ ውጤታማ ቢሆኑም፤ ከሥራቸው ጎን ለጎን ህይወታቸውን ለመለወጥና ለማሻሻል ጥረት ያደርጉ ነበር፡፡ ከልጅነታቸው ጀምሮ አባታቸው እና ታላቅ ወንድማቸው ልብስ ሲሰፉ እየተመለከቱ ማደጋቸው ለልብስ ስፌት ሙያ ፍቅር እንዲያድርባቸው አድርጓል፡፡ ከተወሰነ ጊዜ በኋላም ትኩረታቸውን ሙሉ በሙሉ የልብስ ስፌት ላይ አደረጉ፡፡
“ከቅጥር ስራ ወጥቶ የግል ስራ ለመስራት መወሰን ከባድ ነበር” የሚሉት አቶ ልዑል፣ ስራ ሲለቁ በእጃቸው የነበራቸው ገንዘብ የተወሰኑ ወራትን የቤት ኪራይ ክፍያ መሸፈን እንኳን የሚያስችል አልነበረም፡፡ ነገን አርቀው ይመለከቱ ስለነበር የነበሩበት ሁኔታ አላስደነገጣቸውም፡፡
“ከቤተሰብና ከጓደኛ ብድር በማፈላለግ የስፌት ማሽን በመግዛት ሰሚት አካባቢ ባለ ሶስት መኝታ ቤት ተከራየሁ፡፡ አንዱን ክፍል እንደ መስሪያ ቦታ ሌላውን ደግሞ በመኖሪያነት በመጠቀም ብትን ጨርቅ እየገዛሁ፣ ሸሚዝ እየሰፋሁ መሸጥ ጀመርኩ።” ይላሉ አቶ ልዑል ስለ ስራ አጀማመራቸው ሲያስረዱ፡፡ ለሶስት ዓመት ያህልም ቤት ውስጥ ልብስ እየሰፉ ይሸጡ ነበር፡፡ በወቅቱ ለሸሚዝ የሚሆነውን ጨርቅ ከመርካቶ አምጥተው ሰፍተው ገበያ ላይ ሲያቀርቡ ከውጭ ከሚገባው ጋር በዋጋ መወዳደር አልቻሉም፡፡ ከዚያ በኋላ በተለያየ ዲዛይን የወንድና የሴት ቲ-ሸርቶችን በማምረት ይሰሩ እንደነበር ይናገራሉ፡፡
አሁን ወደተሰማሩበት የስፖርት አልባሳትን ወደ መስፋት የስራ መስክ ሲገቡም ገበያው ላይ ያለውን ፍላጎት እና የጥሬ ዕቃ አቅርቦት መገኘትን በማየት ነበር፡፡ ምርታቸው በገበያው እየተወደደላቸው ሲመጣ ከቤት ወጥተው ተከራይተው መስራት ጀመሩ፡፡
በ2010 ዓ.ም ከአራት ጓደኞቻቸው ጋር በመሆን “የልዑል፣ ሰላማዊትና ጓደኞቻቸው ጋርመንት የህብረት ሽርክና ማህበር”ን መሰረቱ። ማህበሩን ሲመሰርቱ 50 ሺህ ብር እና በግል የገዟቸው አምስት የልብስ ስፌት ማሽኖች እንደነበሯቸው የማህበሩ ስራ አስኪያጅ በመሆን እየሰሩ ያሉት አቶ ልዑል ይናገራሉ፡፡ በዚህ መልኩ ለሁለት ዓመታት ከሰሩና ልምድ ካካበቱ በኋላ ስራቸውን ለማስፋፋት ተጨማሪ ማሽኖች ያስፈልጋቸው ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ያላቸው ካፒታል ተጨማሪ ማሽን ለመግዛት የሚበቃ አልነበረም፡፡ በዚህን ጊዜ ነበር ማሽን በብድር በመግዛት እና ያላቸውን ውስን ካፒታል ለስራ ማስኬጃ በመጠቀም ወደ አዲስ ካፒታል ዕቃዎች ንግድ አክሲዮን ማህበር ያቀኑት፡፡
የማሽኑን ዋጋ 15 በመቶ በመቆጠብ፤ 300 ሺህ ብር ዋጋ ያላቸው 15 የተለያዩ የልብስ ስፌት ማሽኖችን በመጀመሪያው ዙር በመውሰድ በአጭር ጊዜ ብድሩን መለሱ፡፡ እንደገና ዲዛይን የተደረጉ ልብሶችን በክር አትሞ የሚያወጣ “ኢምብሮደሪ” የተሰኘ 2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር የሚሆን ዋጋ ያለው ማሽን በብድር ወሰዱ፡፡ በአሁኑ ወቅትም ከወሰዱት ብድር ውስጥ ከ75 በመቶ በላይ የሚሆነውን መልሰዋል፡፡
ስራቸው እያደገና ውጤታማ እየሆኑ ሲመጡ ከመንግስት የመስሪያ ቦታ ድጋፍ አገኙ፡፡ ለ3ኛ ጊዜም 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው 25 የተለያዩ የልብስ ስፌት ማሽኖችን በብድር በመውሰድ በተለያየ መጠንና ዲዛይን ቁምጣ፣ ቲ- ሸርት፣ ቱታዎችን እያመረቱ ለገበያ እያቀረቡ ይገኛሉ፡፡
“ይህንን ሁሉ ማሽን በራሳችን ወጪ ከፍለን እንግዛ ብንል አቅም አይኖረንም ነበር፡፡ ያለንን ጥቂት ካፒታል ለማሽን መግዢያ አውለን ለጥሬ ዕቃ መግዢያና ሰራተኛ ደመወዝ የሚሆን ወጪዎችን መሸፈን አንችልም ነበር፡፡ ማሽን በሊዝ ማግኘታችን ያለንን ካፒታል ለጥሬ ዕቃ እና ስራ ማስኬጃ እንድንጠቀምበት አግዞናል” ሲሉ ያገኙት ብድር ያስገኘላቸውን ጥቅም ያስረዳሉ፡፡
በአሁኑ ወቅትም በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 ላይ በተሰጣቸው 160 ካሬ ሜትር ስፋት ያለው የመስሪያ ቦታ ላይ ስራቸውን እያከናወኑ ይገኛሉ፡፡ 40 ለሚሆኑ ወጣቶች በቋሚነትና በጊዜያዊነት የስራ ዕድል ፈጥረዋል፡፡ ስንነሳ ራሳችን ተጠቅመን ሌሎችንም ለመጥቀም ነው። ከቤተሰብ ባሻገር ለወገኖቻችን የስራ ዕድል ፈጥረናል ያሉት አቶ ልዑል፣ ማሽንና መኪናን ጨምሮ በአሁኑ ወቅት ማህበሩ ያለው ካፒታል ከ8 ሚሊዮን ብር በላይ ደርሷል፡፡
የስፖርት ትጥቆችን በሀገር ውስጥ በማምረትና ከውጭ የሚገባውን በማስቀረት የራሳቸውን ሚና እየተጫወቱ እንደሚገኙ የሚናገሩት አቶ ልዑል፤ ወደፊት ከዚህ በበለጠ ዘመናዊ ማሽኖችን በመጠቀም ጥራቱን የጠበቀ ምርት አምርቶ ለውጭ ገበያ የማቅረብ እቅድ አላቸው፡፡
ሌላኛው የማሽን ብድር ድጋፍ በማግኘት ውጤታማ ከሆኑ ኢንተርፕራይዞች መካከል ሜትፋብ የብረታ ብረት ውጤቶች ማምረቻ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ነው፡፡ ማህበሩ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመርቀው በወጡ ሶስት ወጣቶች በ2013 ዓ.ም ተመሰረተ። የማህበሩ ስራ አስኪያጅ ወጣት ናትናኤል ካሳሁን በ2011 ዓ.ም ከዲላ ዩኒቨርሲቲ በሲቪል ኢንጂነሪንግ የመጀመሪያ ድግሪውን አግኝቷል። ቀሪዎቹ ሁለት የማህበሩ መስራች አባላትም በመካኒካልና ኤሌክትሪካል ኢንጂነሪንግ ከተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተመርቀዋል፡፡

ወጣት ናትናኤል እንደተናገረው፤ የማህበሩ አባላት ከምርቃት በኋላ ከሁለት እስከ አራት ዓመታት በተለያዩ ድርጅቶች ተቀጥረው ሰርተዋል፡፡ በዚህም በራሳቸው ስራ ለመጀመር የሚያግዛቸውን ጥሪት ይዘዋል፡፡ አሁን ወደተሰማሩበት የስራ መስክ ለመግባት መነሻ የሆናቸው በኢንዱስትሪው ዘርፍ በተለይም የብረታ ብረት ውጤቶችን በትክክል መቁረጥ፣ በተለያየ ቅርፅ፣ በጥራትና በፍጥነት ለማምረት የሚያስችል ሲ ኤን ሲ (Computer Numeric Controlled) ማሽን አገልግሎት በበቂ ደረጃ ገበያው ውስጥ አለመኖሩን ማየታቸው ነበር። በተጨማሪም ሁለቱ የማህበሩ አባላት የመመረቂያ ጽሑፋቸውን የሰሩት በዚሁ ማሽን አጠቃቀም ላይ ነበር፡፡
ስራ የጀመሩትም በ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር መነሻ ካፒታል ነው፡፡ ወደ ስራው ከገቡ በኋላ ለማስፋት ከአዲስ የካፒታል ዕቃ ፋይናንስ ንግድ አክሲዮን ማህበር ብድር አግኝተዋል፡፡ በተለያየ ዙር ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ ከ9 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ “ፋብር ሌሰር ከቲንግ ማሽን”፣ “ፓንኪንግ”፣ “ሲ ኤን ሲ ፕሬስ ብሬክ”፣ የተለያዩ የቅርፅ ማውጫ (ሞልድ) ማሽኖችን በብድር ወስደዋል፡፡
ወጣት ናትናኤል እንደገለፀልን፤ ማሽኖችን በብድር ማግኘታቸው በስራቸው ውጤታማ እንዲሆኑ አግዟቸዋል፡፡ ከራሳቸው አልፈውም ብረቶችን በመጫንና በማውረድ፣ ዲዛይን በማድረግና ማሽኖችን በማንቀሳቀስ በቋሚነት ለ6፤ በጊዜያዊነት ለ12 በድምሩ ለ18 ዜጎች የስራ ዕድል ፈጥረዋል፡፡ በአሁኑ ወቅትም የማሽኖችን ዋጋ ጨምሮ 20 ሚሊዮን ብር የሚደርስ ካፒታል ማፍራት ችለዋል፡፡ ብረታ ብረቶችን በመቁረጥና በተለያየ ቅርፅ በማውጣት አገልግሎት ከመስጠት በተጨማሪ የቴሌቪዥን ማስቀመጫ (ቲቪ ስታንድ)፣ የሰርቨር ሳጥን፣ የበር ጌጣጌጦች ያሉ ከብረት የሚሰሩ ከውጭ የሚገቡ እቃዎችን አምርቶ ለገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሪን በማዳን የራሳቸውን ድርሻ እየተወጡ እንደሚገኙ ተናግሯል፡፡
ወደፊትም አገልግሎቱን የሚፈልጉ በርካታ እንደመሆናቸው ገበያው ውስጥ ያለውን ፍላጎት ከመሙላት ባሻገር ምርቶቻቸውን ለውጭ ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሪ ማዳንና ለበርካታ ወገኖች የስራ ዕድል ለመፍጠር ዓላማ መያዙን ገልጿል፡፡
የስራ ዕድል ፈጠራ አበርክቷቸው
በሜትፋብ የብረታ ብረት ውጤቶች ማምረቻ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር የስራ ዕድል ከተፈጠረላቸው ወጣቶች መካከል ሙሉጌታ አስናቀ አንዱ ነው፡፡ በወሎ ዩኒቨርሲቲ በመካኒካል ኢንጂነሪንግ በ2015 ዓ.ም የመጀመሪያ ድግሪውን የያዘው ወጣት ሙሉጌታ፣ ከተመረቀ ከስድስት ወር በኋላ ወደ ስራ የገባው በማህበሩ ተቀጥሮ ነው፡፡ ረዳት ኦፕሬተር እና በአሁኑ ወቅት ደግሞ የወርክሾፑ ተቆጣጣሪ በመሆን እየሰራ ይገኛል፡፡ በሚያገኘው ደመወዝም ራሱን ችሎ ከመኖር በተጨማሪ ታናናሽ ወንድሞቹን በተለያየ መንገድ ለመደገፍ አስችሎታል፡፡ “በንድፈ ሀሳብ የማውቃቸው ትምህርቶች በተግባር ምን እንደሚመስሉ አይቻለሁ፡፡ ከዚህ ቀደም ስለምሰራበት ማሽን የነበረኝ እውቀት አናሳ ነበር፤ አሁን የማሽኑን አጠቃቀም በደንብ ተረድቼአለሁ። ወደፊት ከድርጅቱ ጋር አብሮ ማደግና ክህሎቴን በማሳደግ ትልቅ ደረጃ ላይ መድረስ እፈልጋለሁ” ሲል ድርጅቱን ተቀላቅሎ በመስራቱ ስላገኘው ጥቅም ያስረዳል፡፡
ወጣት ወርቄ ኪኒ ደግሞ በ“ልዑል፣ ሰላማዊትና ጓደኞቻቸው ጋርመንት የህብረት ሽርክና ማህበር” የስራ ዕድል ከተፈጠረላቸው እንስቶች መካከል አንዷ ናት፡፡ በድርጅቱ የልብስ ስፌት ባለሙያ ናት፡፡
ወጣቷ በማህበሩ እየሰራች በምታገኘው ደመወዝ የቤት ኪራይና የሚያስፈልጋትን ወጪ በመሸፈን ኑሮዋን እየመራች ትገኛለች፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በማህበሩ በቆየችባቸው ጊዜያት ስራዎችን እንዴት መስራት እንደሚቻል እውቀትና ልምድ አግኝታበታለች፡፡ ወደፊትም በግሏ የራሷን ስራ ለመጀመር እቅድ እንዳላት ለዝግጅት ክፍላችን ተናግራለች፡፡
ከላይ ያነጋገርናቸው የኢንተርፕራይዝ አባላት እንደገለጹልን፣ የሚሰጠው የማሽን ብድር ምርትና ምርታማነታቸውን አሳድጓል። ለበርካታ ወገኖች የስራ ዕድል እንዲፈጥሩ አስችሏቸዋል፡፡ ዛሬ ለደረሱበት ስኬታቸውም መሰረት ሆኗቸዋል። የማሽን ብድር ለመውሰድ የሚሰጠው አገልግሎትም መልካምና የሚመሰገን ነው ብለዋል፡፡
ከዚህ ባሻገር በተለይ አዳዲስ ኢንተርፕራይዞች ብድር ለመውሰድ የመስሪያ ቦታ ኪራይ ውል ካሳዩ በኋላ ማሽነሪዎችን በቶሎ ገዝቶ ከማቅረብ አንፃር የሚታየው መዘግየት መፍትሄ ሊያገኝ እንደሚገባ ያነሳሉ። ነባር ኢንተርፕራይዞች ባላቸው ማሽን እየሰሩ ይቆያሉ፤ አዳዲሶቹ ግን ቤት ከተከራዩ በኋላ ማሽን ሳያገኙ፣ ወደ ስራ ሳይገቡ በባዶ ቤት ኪራይ እየከፈሉ ከስድስት ወር በላይ ጊዜ ሊቆዩ ይችላሉ። ይህም ብዙ ወጪ የሚያስወጣቸው በመሆኑ አሰራሩን ማየት እንደሚያስፈልግ ያነሳሉ፡፡
አቅርቦቱና የተገኘው ውጤት
አዲስ የካፒታል ዕቃ ፋይናንስ ንግድ ስራ አክሲዮን ማህበር በ2016 በጀት ዓመት እስከ 1 ቢሊዮን ዋጋ ያላቸውን ማሽነሪዎች 1 ሺህ 200 ለሚሆኑ ኢንተርፕራይዞች ለማቅረብ አቅዶ፣ 669 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው ማሽነሪዎችን ለ611 ኢንተርፕራይዞች ማስተላለፍ ችሏል። በተደረገው ድጋፍም ኢንተርፕራይዞች ከ2 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠር ችለዋል፡፡ ማሽነሪዎቹም በአብዛኛው በብረታ ብረት፣ አልባሳት፣ በቆዳና ቆዳ ውጤቶች፣ ቆሻሻን መልሶ በመጠቀም፣ የህትመት ውጤቶችና በሌሎች የአምራች ዘርፍ ለተሰማሩ ኢንተርፕራይዞች እንዲሁም በኮንስትራክሽንና አገልግሎት ዘርፍ ለተሰማሩ የተሰጡ መሆኑን የአዲስ የካፒታል ዕቃ ፋይናንስ ንግድ ስራ አክሲዮን ማህበር ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ መሳይ እንሴኔ ይናገራሉ፡፡

እንደ አቶ መሳይ ገለፃ፤ የተያዘውን የተለጠጠ ዕቅድ በፋይናንስ እጥረት ምክንያት ማሳካት ባይቻልም፣ በ2015 በጀት ዓመት ቀርቦ ከነበረው 690 ሚሊዮን ብር ብድር ጋር ሲነፃፀር በ2016 በጀት ዓመት የተሰጠው ተቀራራቢና ከዚያ በፊት ከነበሩ ዓመታት አንጻር ከፍተኛ በመሆኑ አፈፃፀሙ ጥሩ የሚባል ነው፡፡
ፈተናዎችና እየተወሰዱ ያሉ መፍትሔዎች
አዲስ የካፒታል ዕቃ ፋይናንስ ንግድ ስራ አክሲዮን ማህበር የአምራች ዘርፉን ለመደገፍ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትልቁን ድርሻ በመያዝ፣ ስኬት ባንክና ሌሎች የከተማ አስተዳደሩ የልማት ተቋማት ጋር በመሆን በ500 ሚሊዮን ብር ካፒታል ነው በ2006 ዓ.ም የተቋቋመው። ከተቋቋመ እስከ አሁን ድረስ ከ2 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ ማሽነሪዎችን ገዝቶ ለኢንተርፕራይዞች አስተላልፏል። ከ1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ የሚሆን ገንዘብ በደንበኞች እጅ የሚገኝና የሚሰበሰብ እንደሆነም አቶ መሳይ ያነሳሉ፡፡
የመጀመሪያዎቹ አምስት ዓመታት ኢንተርፕራይዞች ማሽን በብድር እንዲወስዱ እንለምን ነበር፡፡ ከሶስት ዓመት ወዲህ ፍላጎቱ እየጨመረ በመምጣቱ ተቋሙ መስጠት ከሚችለው አቅም በላይ ሆኗል፡፡ በአሁኑ ወቅት ከ141 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ ማሽኖች በግዥ ሂደት ላይ ናቸው። የቢዝነስ ፕላን ፀድቆላቸው ወደ ቀጣይ ሂደት ለመግባት በዝግጅት ላይ የሚገኙ ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ የሚጠይቁ የማሽን ግዥ ጥያቄዎች አሉ፡፡
ስራ ለመስራት ማሽን ፈልጎ የሚመጣውን ወጣት ለማስተናገድ የተቋሙን የፋይናንስ አቅም ማሳደግ እንደሚገባ የሚያነሱት የተቋሙ ዋና ስራ አስፈፃሚ፤ ይህንንም በመገንዘብ ካፒታሉን ወደ 1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ለማድረስ የከተማ አስተዳደሩ፣ ስኬት ባንክና ሌሎች አበዳሪ ተቋማት ድጋፍ እንዲያደርጉ በጠቅላላ ጉባኤ ተወስኖ ገንዘቡን ለማግኘት እየተሰራ ይገኛል፡፡
ሌላኛው ለኢንተርፕራይዞች የሚቀርቡ ማሽኖች ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ ከማድረግ ጋር በተያያዘ የአሰራር ክፍተቶች ነበሩ፡፡ አብዛኞቹ የነበሩ የህግ ችግሮች በአዲሱ የታሪፍ ህግና የገንዘብ ሚኒስቴር ባወጣቸው መመሪያዎች ተፈትቷል፡፡ ነገር ግን አሁንም የአፈጻጸም ችግሮች አሉ፡፡ በተለይ ማሽነሪዎች ከሀገር ውስጥ የተገዙ ከሆነ፣ አቅራቢዎች ማሽኑን ሲሸጡ ለገቢዎች ቢሮ ማሳወቅ አለባቸው። ይህንን ሲያደርጉ ዕቃው ሲገዛ የተጨመረው የተጨማሪ እሴት ታክስ ዋጋው ለተቋሙ ተመላሽ ይሆናል። ይሁን እንጂ አቅራቢዎችን ይህንን ስለማያደርጉ የተጨማሪ እሴት ታክስ (ቫት) ተመላሽ የማይደረግበት ሁኔታ ያጋጥማል። ይህም በዋናነት የኢንተርፕራይዙን ከተጨማሪ እሴት ታክስ ነፃ የመሆን መብት የሚያሳጣ በመሆኑ በቀጣይ ችግሩን ለመቅረፍ እንደሚሰራ አቶ መሳይ ተናግረዋል፡፡
“የማሽን ብድር ጥያቄ ከቀረበ በኋላ በቶሎ ማሽኑ ኢንተርፕራይዞች እጅ አይገባም” በሚል የሚነሳውን ጥያቄም በተመለከተ አቶ መሳይ እንዳብራሩት፤ ተቋሙ የኢንተርፕራይዞችን የቢዝነስ ፕላን ግምገማ ለመጨረስ ከሰባት ቀን በላይ አይወስድበትም፡፡ የአቅራቢውን ህጋዊነት፣ ለማሽኑ የተጠየቀው ዋጋ በገበያው ልክ እና ጥራት ያለው መሆኑን ክትትል ያደርጋል፡፡ ቅድመ ሁኔታዎችን ማሟላትና ውሳኔ የመወሰን ኃላፊነት የኢንተርፕራይዞች ነው፡፡ ኢንተርፕይዞች የማሽን ብድር ለመወሰድ ትልቁ ያለባቸው ችግር የመስሪያ ቦታ ነው፡፡ የማሽን ብድር ለማግኘት የመስሪያ ቦታ ያላቸው መሆኑን ከቤተሰብ፣ ከመንግስት ወይም በኪራይ ሊሆን ይችላል ማሳየት ይኖርባቸዋል፡፡
አንዳንድ ኢንተርፕራይዞች ማሽኑ ከውጭ ከገባ በኋላ የመስሪያ ቦታ እንከራይ እያሉ የሚጠይቁ አሉ፡፡ ከዚህ ቀደም ማሽኑ እንዲገባ ከተደረገ በኋላ የመስሪያ ቦታ ተከራይተው እንዲሰሩ ተፈቅዶ ነበር። ነገር ግን በቶሎ የመስሪያ ቦታ አጥተው ምንም ሳይሰሩ የማሽን ብድሩ እየቆጠረ ዕዳ ውስጥ ይገባሉ። በካፒታል ዕቃ ፋይናንስ አዋጅም እንደተቀመጠው ኢንተርፕራይዞች ሁሉንም ነገር አሟልተው ማሽን ለመግዛት የካፒታል እጥረት ሲያጋጥማቸው ነው የካፒታል ዕቃ ብድር የሚሰጣቸው፡፡
በተለይ ለጀማሪ ስራ ፈጣሪዎች የመስሪያ ቦታ ማግኘት ፈታኝ እንደሆነ ያነሱት አቶ መሳይ፣ አዲስ የካፒታል ዕቃ ፋይናንስ ንግድ ስራ አክሲዮን ማህበር ቦርድ ዋና ሰብሳቢ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የሚመራ ሲሆን፤ የአዲስ አበባ የፋይናንስ ቢሮ፣ የስራና ክህሎት ቢሮ፣ የኢንዱስትሪ ቢሮ፣ የኢንቨስትመንት ኮሚሽንና ሌሎች ባለድርሻ ተቋማት ኃላፊዎች ያሉበት በመሆኑ ከኢንተርፕራይዞች ጋር በተያያዘ ያሉ ችግሮች እንዲፈቱ በጋራ እንደሚሰራ ጠቁመዋል፡፡
አቶ መሳይ እንደገለፁት፤ አዲስ ኢንተርፕራይዝ የማሽን ብድር ለማግኘት የመስሪያ ቦታ አግኝቶ ከተከራየ በኋላ ማሽኖችን በፍጥነት ከማቅረብ አኳያ ያለው ችግር፣ በሀገራችን ማሽን የሚያመርቱ እና የሚያቀርቡ ድርጅቶች ስለሌሉና አብዛኞቹ ከውጭ የሚገቡ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ የሚያጋጥም ችግር ነው፡፡ የውጭ ምንዛሪ እጥረትና ማሽኖቹ ተመርተው አስፈላጊ ሂደቶች ተሟልተው ወደ ሀገር ውስጥ እስኪገቡ ድረስ ከስድስት እስከ አስር ወር የሚቆዩበት ጊዜ አለ፡፡
አቶ መሳይ እንዳብራሩት፣ መንግስት የውጭ ባለሀብቶች በሀገር ውስጥ ንግድና ችርቻሮ እንዲሰማሩ መፈቀዱ በውጭ ሀገር ያሉ አምራቾች ማሽነሪዎችን በሀገር ውስጥ የሚሸጡበትን ሁኔታ ይፈጥራል። እንደ የሊዝ ፋይናንስ ማህበር የውጭ ባለሀብቶች ማሽነሪዎችን በሀገር ውስጥ የሚያቀርቡበት ሁኔታ እንዲፈጠር እየተሰራበት ይገኛል፡፡
አዲስ የካፒታል ዕቃ ፋያናንስ ንግድ ስራ አክሲዮን ማህበር በ2017 በጀት ዓመት 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር የሚያወጡ ማሽኖችን ከ1 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ኢንተርፕራይዞች ለማቅረብ ዕቅድ ይዟል፡፡
በ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ኩባንያው 121 አባላት ላሏቸው 69 ኢንተርፕራይዞች ከ69 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ 549 የተለያዩ የማምረቻና ለአገልግሎት ተግባር የሚውሉ ማሽነሪዎችን አስተላልፏል፡፡ በዚህም 573 ዜጎች የስራ ዕድል ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡
አቶ መሳይ እንደሚያስረዱት የማሽን ሊዝ ፋይናንስ የትውልድ ፋይናንስ (Generational Finance) ነው፡፡ አንድ ቤተሰብ በመኖሪያ ቦታው አካባቢ ማሽን ተከለ ማለት ልጆቹ በቅርበት ስራውን እያዩ፣ እየሰሩና እየተማሩ የሚያድጉበትን ዕድል ይፈጥራል። በንድፈ- ሀሳብ ሳይሆን በተግባር የስራ ባህልን እየለመዱ ይሄዳሉ፡፡
የማሽን ሊዝ ፋይናንስ የኢንተርፕራይዞችን ውጤታማነትና ምርታማነታቸውን የሚያሳድግ፣ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን እንዲላመዱ እንዲሁም ሀብታቸውን እንዲቆጥቡ የሚያግዝ አገልግሎት ነው። በብድር ማሽን ወስደው በረጅም ጊዜ እየከፈሉ ሀብት የሚያከማቹበት፣ ያላቸውን ውስን ካፒታል ለስራ ማስኬጃ የሚያውሉበትን ሁኔታ የሚፈጥር፣ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው አገልግሎት በመሆኑ ሊጠናከርና በስፋት ሊሰራበት ይገባል መልእክታችን ነው፡፡
በስንታየሁ ምትኩ