የማዕድን ሚኒስቴር ገቢ ለማሳደግ የፖሊሲ እና የህግ ማዕቀፍ ሥራዎችን በልዩ ትኩረት ማከናወን ይጠበቅበታል- ቋሚ ኮሚቴው

AMN- ህዳር 5/2017 ዓ.ም

የማዕድን ሚኒስቴር ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ የፖሊሲ እና የህግ ማዕቀፍ ሥራዎችን በልዩ ትኩረት እንዲያከናውን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።

ቋሚ ኮሚቴው የ2015/16 በጀት ዓመት በማዕድን ሚኒስቴር ከማዕድን የሚገኝ ገቢን ማሳደጉንና መሰብሰቡን በተመለከተ በዋና ኦዲተር መስሪያቤት የተከናወነ የክዋኔ ኦዲት ሪፖርትና የተወሰዱ የማስተካካያ እርምጃዎች ላይ ውይይት አካሂዷል።

የማዕድን ሚኒስቴር የማዕድን ሃብት ክምችት በመለየት፣ የቅድመ አዋጭነት ጥናት አካሂዶ ተደራሽ ከማድረግና ለዘርፉ ፖሊሲ ከማዘጋጀት አኳያ ክፍተቶች መኖራቸውን የክዋኔ ኦዲት ሪፖርቱ አመላክቷል።

በተመሳሳይ በማዕድን ኢንቨስትመንትና ልማት የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ማሳደግ የሚያስችል ቀልጣፋና ውጤታማ የአሰራር ስርዓት አለመዘርጋቱንም የኦዲት ሪፖርቱ አሳይቷል።

የማዕድን ምርቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ስርዓት ዘርግቶ አፈጻጸሙን ከመከታተል አኳያም ክፍተት እንዳለ ነው የተገለጸው።

ህገ-ወጥነትን ከመካላከል፣ ተኪ ግብዓት ከማቅረብ፣ ለባህላዊ ማዕድን አምራቾች ከክልሎች ጋር በመተባበር ክትትል ከማድረግ አንጻርም ክፍተት እንደነበረ በሪፖርቱ ተመላክቷል።

የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላትና በመድረኩ የተገኙ ባለድርሻ አካላት ማዕድን ሚኒስቴር በኦዲት ግኝቱ መሰረት የወሰዳቸው የማስተካከያ እርምጃዎች ላይ ማብራሪያ ጠይቀዋል።

የማዕድን ሚኒስትር ዴኤታ ሚሊዮን ማቲዎስ በኦዲት ግኝቱ የተለዩ ክፍተቶችን ለማስተካከል በእቅድና ፕሮጀክት በማካተት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ጠንካራ አሰራር ለመዘርጋት ተቋሙ ያሻሻለው አዋጅ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እስኪጸድቅ መመሪያዎች እየተዘጋጁ እንደሆነም ተናግረዋል።

የማዕድን ሃብት ክምችትና አለኝታ ቦታዎችን መረጃዎች አደራጅቶ ተደራሽ በማድረግ የዘርፉን የኢንቨስትመንት ፍሰት ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑንም አንስተዋል።

ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ ለመተካት በድንጋይ ከሰል ላይ እየተከናወነ ያለውን ኢንቨስትመንት በማሳያነት ጠቅሰዋል።

ህገ-ወጥ የማዕድን ዝውውርን ለመከላከል እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን ጠቅሰው፥ ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግም ሰፊ ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።

የፌደራል ዋና ኦዲተር መሰረት ዳምጤ በበኩላቸው፤ ሚኒስቴሩ በኦዲት ግኝቱ መሰረት ማስተካከያ ለማድረግ የተቀናጀ አደረጃጀት ዘርግቶ መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሺመቤት ደምሴ(ዶ/ር) ኢትዮጵያ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ትኩረት ከሰጠቻቸው ዘርፎች አንዱ ማዕድን በመሆኑ በኦዲት ግኝቱ ለተመላከቱ ጉዳዮች ልዩ ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review