AMN- ህዳር 11/2017 ዓ.ም
2ኛው የምስራቅ እና የደቡብ አፍሪካ ሃገራት የጤና ድንገተኛና ፈጣን ምላሽ ዝግጁነት ኮሚቴ ጉባኤ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል
በጉባኤውን የመክፈቻ ንግግራቸውን ያደረጉት የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባየጤና፣ የድንገተኛና ፈጣን ምላሽ ዝግጁነት ሥራዎች ድንበር ዘለል ትብብሮችን የሚጠይቁ በመሆናቸው በቅንጅት መሥራት የግድ ነው ብለዋል፡፡
እነዚህን ድንገተኛ የጤና አደጋዎች ለመከላከል ከሀገራዊ ወሰን በላይ የሆነ እና የጋራ ሃላፊነትን የሚጠይቅ የተቀናጀ እና የትብብር ምላሽ ያስፈልጋል ብለዋል።
የዛሬው ጥረታችን አሁን ያሉትን ስጋቶች ከማስወገድ ባለፈ ነገ ሊያመጣቸዉ የሚችሉትን የጤና ድንገተኛ አደጋዎች በማሰብ ከአሁኑ ቅንጅታዊ ዝግጅት እንደሚያስፈልግ ጠቅሰዋል፡፡
ለችግር የማይበገር ጠንካራ የጤና ስርዓትን ለመመስረት እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ላይ ማተኮር ያስፈልጋል ያሉት ዶ/ር መቅደስ፤ የቀጠናው ሃገራት እርስ በርስ የተያያዙ ተግዳሮቶች እንደሚያጋጥሟቸው እና እነዚህ ተግዳሮቶች የተዋሃደ እርምጃ እንደሚያስፈልጋቸው ጠቁመዋል።
የጉባኤው ግብ የሃገር ውስጥ የመድሃኒት ማምረት እና የቁጥጥር አቅም ግንባታ፣ የጤና አቀራረቦችን ማቀናጀት፣ የሥርዓተ-ፆታ ክፍተቶችን ለመፍታት ትኩረት መስጠት፣ የጤና የሰው ኃይል ልማት፣ እና የድንበር ተሻጋሪ ትብብርን፣ ክትትልን እና የላብራቶሪ አቅምን ማሳደግ ላይ አህጉራዊ ቅንጅትን ማበረታታት እንደሆነም ሚኒስትር መቅደስ ተናግረዋል፡፡
በግንቦት 2024 በናይሮቢ የተካሄደው የመጀመሪያው የHEPR ክልላዊ አማካሪ ኮሚቴ ስብሰባ ለድንበር ተሻጋሪ ትብብር፣ አቅም ግንባታ እና የአደጋ ጊዜ ዝግጁነት ጠንካራ መሰረት ጥሏልም ብለዋል ፡፡
የኢሲኤስኤ(ECSA) ዳይሬክተር ሲቡሲሶ ሲባንዲዜ፤ ይህ ሁለተኛው ስብሰባ የክልላዊ ተነሳሽነቶችን ሂደት በመገምገም፣ ቁልፍ ክፍተቶችን በመለየት ሃገራት ልምድ የሚለዋወጡበት ነው ብለዋል፡፡
በጉባኤው ኢጋድን (IGAD) በመወከል ንግግር ያደረጉት ፋቲሃ አልዋል ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን እና የአእምሮ ጤናን የመለየት እንዲሁም የማከም እና የምርምር፣ የመረጃ ሥርዓቶች እና የዲጂታል የጤና መሠረተ ልማትን ማጠናከር ላይ የኢጋድ ሃገራት በትብብር እንደሚሰሩ አስረድተዋል፡፡
የአለም ባንክ የህዝብ የጤና እና የስርአተ ምግብ ሀላፊ ዶ/ር ራሚሽ ጎቪንዳራዥ በበኩላቸው ሌሎች የቀጠናው ሃገራት ፕሮግራሙን እንዲያጸድቁ እና ተሳትፏቸውን እንዲያሳድጉ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን፤ በፕሮግሙ እስካሁን ከ42 ሚሊዮን ዶላር በላይ ለሃገራት ተደራሽ መደረጉን መግለፃቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ከዛሬ ጀምሮ ለሶስት ቀናት በሚቆየው በዚህ ጉባዔ በጤናው ዘርፍ ድንገተኛና ፈጣን ምላሽ አሰጣጥን አስመልክቶ ስለሚኖሩ ተግባራትና አፈጻጸም ግምገማ የሚካሄድ ሲሆን፤ የጤና ተቋማት እና የቂሊንጦ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ጉብኝት በፕሮግራሙ መርሀ ግብር ዉስጥ ተካተዋል።