የምንገነባው አገረ መንግስት ለሁሉም ዋስትና የሚሰጥ እና ሁሉንም የሚያግባባ ነው፡- አቶ ሞገስ ባልቻ

You are currently viewing የምንገነባው አገረ መንግስት ለሁሉም ዋስትና የሚሰጥ እና ሁሉንም የሚያግባባ ነው፡- አቶ ሞገስ ባልቻ

AMN – ጥር 20/2017 ዓ.ም

የምንገነባው አገረ መንግስት ለሁሉም ዋስትና የሚሰጥ እና ሁሉንም የሚያግባባ መሆኑን የብልጽግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ከተማ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሞገስ ባልቻ ተናገሩ፡፡

አቶ ሞገስ ባልቻ የብልጽግና ፓርቲ ቅድመ ጉባኤን አስመልክተው ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የአገረ መንግስት ግንባታችን ሰላማችንን ማስጠበቅ እና የፖለቲካ መግባባት ላይ መድረስ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዚህም አሁን የተጀመሩ እንደ አገራዊ ምክክር፤ የሽግግር ፍትህ እና መሰል ያላግባቡን እና ያቃረኑን ጉዳዮችን በሰለጠነ አግባብ መፍታት የሚያስችሉ አካሄዶች ተጠናክረው ከቀጠሉ ወደ ሰላም መምጣት እንደሚቻል አውስተዋል፡፡

የምንገነባው አገረ መንግስት ለሁሉም ዋስትና ሊሰጥ የሚችል ሁሉም የሚግባበት እንደሆነም አመልክተዋል፡፡

መንግሰት ከታጠቁ ሀይላት ጋር በተለያዩ ጊዜያት ባደረገው የሰላም ውይይት ውጤት መገኘቱንም ተናግረዋል።

ምንጊዜም ቢሆን ለሰላም በሩ ክፍት እንደሆነም አቶ ሞገስ ጠቅሰዋል፡፡

የፕሪቶሪያው ስምምነት ለዚህ ምሳሌ እንደሆነም አውስተዋል።

በፈተና ውስጥም ሆነን መልካም እድሎች እንዲመጡ ከፍተኛ ስራ መሰራቱንም አውስተዋል፡፡

አገሪቱ በፈተና ውስጥ በአሸናፊነት እንድትወጣ እና ኢኮኖሚው እንዲያንሰራራ እንዲሁም አገርን ከብተና መዳን መቻሉ ትልቅ ስኬት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በፈተና ውስጥ ሆነን ትልቅ ስኬት ያስመዘገብንበት ሁኔታ አለ ያሉት አቶ ሞገስ በኢኮኖሚው መስክ ከመጡ ለውጦች መካከል ስንዴን በስፋት በማምረት ወደ ውጭ መላክ ፤ በሌማት ትሩፋት እና የህዳሴ ግድብ እንዲያንሰራራ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ውጤት ተገኝቷል ብለዋል፡፡

አስተማማኝ ሰላምን የማረጋገጥ ፤ የኑሮ ውድነትን የመቅረፍ እና ምርት እና ምርታማነትን በማሻሻል የኢትዮጵያን ብልጽግና እውን ማድረግ ቀጣይ የቤት ስራ መሆኑንም አውስተዋል።

በጥቅሉ በአፍሪካ ተምሳሌት የሆነች አገር መገንባት የመጪው ዘመን ትልቁ ስራ መሆኑን አንስተዋል፡፡

በሰለሞን በቀለ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review