የሠላም ሠራዊት ለከተማዋ ሠላም የጀርባ አጥንት ሆኖ እያገለገለ ይገኛል- ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ

You are currently viewing የሠላም ሠራዊት ለከተማዋ ሠላም የጀርባ አጥንት ሆኖ እያገለገለ ይገኛል- ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ

AMN- ጥር 15/2017 ዓ.ም

የሠላም ሠራዊት ከማህበረሰቡ የተወጣጣ በመሆኑ ለከተማዋ ሠላም የጀርባ አጥንት ሆኖ እያገለገለ እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ከተማ ሰላም እና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ ተናገሩ።

የአዲስ አበባ ከተማ የሰላም እና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ ከአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ የአገልጋይ ዝግጅት ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለፁት ፣ በአሁኑ ሰዓት በመዲናዋ ከ420ሺ በላይ የሠላም ሠራዊት አደረጃጀቶች አሉ።

አደረጃጀቶቹ በአሥራ አንዱም ክፍለ ከተሞችና በሁሉም ወረዳዎች በሶስት ፈረቃ ጥበቃ ያደርጋሉም ነው ያሉት ኃላፊዋ፡፡

ይህም በመዲናዋ ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ከባድ ወንጀል በ48 በመቶ እንዲቀንስ ማስቻሉን አብራርተዋል፡፡

በሌላ በኩል ህዝባዊ እና ሃይማኖታዊ የአደባባይ በዓላት በአንድነትና በሠላም እንዲከበሩ የሠላም ሰራዊቱ አስተዋጽኦ የጎላ እንደነበርም ኃላፊዋ አንስተዋል፡፡

በመዲናዋ ከ32 በላይ የሚሆኑ ኮንፈረንሶች ያለ ምንም የጸጥታ ችግር በስኬት መከናወናቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡

በተያዘው በጀት ዓመትም ህግና ደንብን በተከተለ መልኩ 22 ሺ የሚሆኑ ምልምል የሰላም ሠራዊት አባላት ሥልጠና እየወሰዱ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡

በመዲናዋ የተገነባው የኮሪደር ልማት ለጸጥታው ሥራ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን የገለፁት ኃላፊዋ በዚህም በርካታ ቱሪስቶች ወደ ከተማዋ እየመጡ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡

የሠላም ሠራዊት አደረጃጀት ተጠሪነቱ ለማህበረሰብ አቀፍ የፖሊስ አገልግሎት በመሆኑ ተቋሙ ከተሰጣቸው ተልእኮ እንዳይወጡ ያደርጋል ያሉት ወ/ሮ ሊዲያ አልፎ አልፎ በግለሰብ ደረጃ ከሥነ ምግባር ጋር የተያያዘ ችግር ያለባቸውን በማህበረሰቡ ዘንድ ተቀባይነት ባላቸው ሰዎች የመተካት ሥራ መከናወኑንም ከኤኤምኤን አገልጋይ ዝግጅት ጋር ባደረጉት ቆይታ ገልጸዋል፡፡

በማሬ ቃጦ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review