AMN – ታኅሣሥ 19/2017 ዓ.ም
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በሩስያ አየር ክልል ውስጥ በተመታው የመንገደኞች አውሮፕላን ዙሪያ የአዘርባጃን ፕሬዝዳንትን ይቅርታ ጠይቀዋል፡፡
ፕሬዝዳንት ፑቲን ስልክ በመደወል ለአዘርባጃኑ አቻቸው ኢልሃም አሊየቭ በደረሰው አደጋ ማዘናቸውንና ለተጎጂ ቤተሰቦች መጽናናትን ተመኝተዋል፡፡ ነገር ግን ለአደጋው በይፋ ሃላፊነት አልወሰዱም።
ፑቲን “አሳዛኝ ክስተት” ላሉት አደጋ ይቅርታ የጠየቁት አደጋው በሩሲያ የአየር ክልል በመከሰቱ መሆኑን አሶሽየትድ ፕሬስ አስነብቧል።
አውሮፕላኑ በቺቺኒያ ለማረፍ ሲሞክር በሩሲያ አየር መከላከያ ተኩስ ስለተከፈተበት ወደ ካስፒያን ባህር አቅጣጫ ለመቀየር ስለመገደዱ ሲዘገብ ቆይቷል፡፡
የአዘርባጃኑ ኢምባሪየር 190 አውሮፕላን ከባኩ ተነስቶ ወደ ቺቺኒያ መዲና ግሮዥኒ ሲያመራ በከተማዋ የነበረው ጭጋጋማ የአየር ሁኔታ የጉዞ አቅጣጫውን እንዲቀይር አድርጎታል የሚሉ ዘገባዎችም ወጥተው ነበር፡፡
አንድ ዓለም አቀፍ የባለሙያዎች ቡድን አደጋውን በተመለከተ ምርመራ መጀመሩ የተነገረ ሲሆን ነገር ግን በአደጋው ዙርያ ዝርዝር መረጃ አልተሰጠም፡፡
ረቡዕ ዕለት ከባኩ ወደ ግሮዝኒ እና በአቅራቢያዋ ማካችካላ በረራ መቋረጡን ተከትሎ የአዘርባጃን አየር መንገድ ለተጨማሪ ስምንት የሩስያ ከተሞችም አገልግሎት እንደሚያቆም አስታውቋል።