የሩዋንዳ እና የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዝዳንቶች በምስራቃዊ ኮንጎ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ጥሪ አቀረቡ

You are currently viewing የሩዋንዳ እና የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዝዳንቶች በምስራቃዊ ኮንጎ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ጥሪ አቀረቡ

AMN – መጋቢት 10/2017 ዓ.ም

በኳታር የተገናኙት የሩዋንዳው ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ እና የዴሞክራቲክ ሪፓሊክ ኮንጎ ፕሬዝዳንት ፊሊክስ ቼሲኬዲ በምስራቃዊ ኮንጎ ሰላም እንዲሰፍን የተኩስ አቁም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የሁለቱ ሀገራት መሪዎች ፊት ለፊት ተገናኝተው ሲነጋገሩ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው፡፡

ኤም 23 የተባለው አማፂ በሩዋዳ መንግስት ይደገፋል ስትል በተለያዩ ወቅቶች ኮንጎ ሩዋንዳን ከሳለች፡፡ በምሥራቁ ክፍል ያለውን ማዕድን እየበዘበዘች መሆኗንም ትገልፃለች፡፡

ሩዋንዳ በበኩሏ ከቡድኑ ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የለኝም ስትል የቆየች ሲሆን ይልቁንም የሀገሯን ደህንነት ከኮንጎ ሠራዊት እና ታጣቂ ሚሊሻዎች እየተከላከለች መሆኗን ገልፃ ክሱን ታስተባብላለች፡፡

ከጥር ወር ወዲህ ብቻ በምሥራቃዊ ኮንጎ ኤም 23 በከፈተው የጦርነት ዘመቻ 7ሺ ሰዎች መገደላቸውን የኮንጎ ባለሥልጣናት ይናገራሉ፡፡

እንደ ቢቢሲ ዘገባ በሁለት ወራት ውስጥ ጎማ እና ቡካቩ የተሰኙ ሁለት ቁልፍ ከተሞችንም መቆጣጠር ችለዋል፡፡

በኳታሩ ኤሚር ሼክ ታሚም ቢን ሀማድ አል ታሀኒ ግብዣ መሠረት በሁለቱ የአፍሪካ መሪዎች መካከል የተደረገው ውይይት በቀጣይ ሊደረግ ለታሰበው የሠላም ንግግር መሰረት እንደሚጥል ተስፋ የተጣለበት ቢሆንም አማፂው ጥሪውን የመቀበሉ ጉዳይ አጠራጣሪ ነው ተብሏል፡፡

ውይይቱን ተከትሎ የኳታር ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሪዎቹ ተኩስ ዓቁሙ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲካሄድ ቁርጠኛ መሆናቸውን አስታውቋል፡፡ በምን አግባብ ይመራ የሚለው ግን ምላሽ ያላገኘ ጉዳይ ነው ተብሏል፡፡

የኮንጎው ፕሬዝዳንት ፊሊክስ ቼሲኬዲ ውይይቱ በምስራቃዊ ኮንጎ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ወሣኝነት እንዳለው ተናግረዋል፡፡ በቀጣይ ብዙ የንግግር መድረኮች እንደሚጠበቁም አንስተዋል፡፡

ማክሰኞ እለት በኮንጎ መንግስት እና በአማፂው ኤም-23 መካከል በአንጎላ ሲጠበቅ የነበረው የድርድር መድረክ አማፂው ባለመቀበሉ ምክንያት ሳይካሄድ ቀርቷል፡፡ ይህን ተከትሎ ነው ሁለቱ መሪዎች በኳታር ተገናኝተው ሊመክሩ የቻሉት፡፡

በማሬ ቃጦ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review