የሮቤ ከተማ ነዋሪዎችን የንጹህ መጠጥ ውሃ ፍላጎት ሙሉ በሙሉ እንደሚያሟላ የሚጠበቀው የውሃ ፕሮጀክት ግንባታ እየተፋጠነ መሆኑ ተገልጿል፡፡
የመገናኛ ብዙሃንና የኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች በኦሮሚያ ክልል እያደረጉት ያለው ጉብኝት እንደቀጠለ ሲሆን፣ በዛሬው እለትም በባሌ ዞን የሮቤ ከተማ የንጹህ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክትን ተመልክተዋል፡፡
በኦሮሚያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን የሮቤ ከተማ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ሽመልስ በልሁ፣ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቱ ለ140 ሺህ የሮቤ ከተማ ነዋሪዎች ተደራሽ እንደሚሆን ጠቅሰው፣ የግንባታ አፈጻጸሙ ከ80 በመቶ በላይ መድረሱን ተናግረዋል።
ፕሮጀክቱ ከተጀመረ ከ6 አመታት በላይ ያስቆጠረ ቢሆንም በተቋራጭ የአቅም ውስንነት ምክንያት ሲጓተት መቆየቱን የገለጹት ደግሞ የኦሮሚያ ክልል ውሃና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር ሚሊዮን በቀለ ናቸው።
አሁን ላይ የግንባታ ስራው የተሻለ አቅም ላለው ስራ ተቋራጭ እንዲሰጥ በመደረጉ እና በፍጥነት እየተሰራ በመሆኑ እስከ ፊታችን ሰኔ 30 ድረስ እንደሚጠናቀቅ ኢንጂነር ሚሊዮን ጠቁመዋል፡፡
አስተያየት የሰጡ የሮቤ ከተማ ነዋሪዎች እንደገለጹት፣ ከተማዋ ቀደም ሲል ከፍተኛ የመጠጥ ውሃ እጥረት እንደነበረባት ጠቅሰው፣ መንግስት የነዋሪውን የውሃ ችግር ለመፍታት ከፍተኛ በጀት መድቦ በመስራቱ የላቀ ምስጋና እናቀርባለን ብለዋ፡፡
ምትኩ ተሾመ