AMN – የካቲት 15/2017 ዓ.ም
የሰላም ሰራዊት አደረጃጀት በተባበረና በተቀናጀ የፀጥታ አስተዳደር ስርአት የአዲስ አበባን ሰላም የሚያፀና መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ሀላፊ ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ ገለጹ፡፡
ቢሮው፣ በ2017 በጀት ዓመት የተካሄዱ ህዝባዊ፣ ሀይማኖታዊና ባህላዊ የአደባባይ በዓላትን እና አህጉር አቀፍ ጉባኤዎች እንዲሁም ኮንፈረንሶች ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲከበሩ አስተዋፆኦ ላበረከቱ የሰላም ሰራዊት አባላትና አመራሮች የእውቅናና የምስጋና መርሀ ግብር እያካሄደ ይገኛል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ የህግ የበላይነትን በማረጋገጥ በመዲናዋ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ከተለያዩ ባለ ድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ ያነሱት የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ሀላፊ ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ፣ በተለይ ህዝቡን የሰላም ባለቤት በማድረግ እና በሰላም ሰራዊት መዋቅር በማደራጀት በከተማዋ የፀና ሰላም እንዲሰፍን ማድረግ ስለመቻሉ አንስተዋል፡፡
የሰላም ሰራዊት አደረጃጀት በሀቀኝነት፣ በቅንነት፣ በታማኝነት እንዲሁም በፈቃደኝነት እና በተነሳሽነት ሰላሙ በእጄ ነው በማለት የሚተጋና የሰላም ዋጋ የገባው መሆኑን የገለጹት ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ፣ ይህንም በመዲናዋ የተከናወኑ ህዝባዊ፣ ሀይማኖታዊ እና ባህላዊ የአደባባይ በዓላት እንዲሁም አህጉር አቀፍ ጉባኤዎችና ኮንፈረንሶች ያለምንም የፀጥታ ችግር በሰላም መጠናቀቃቸው ትልቅ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
ከተማ አስተዳደሩ በልዩ ሁኔታ በመደገፍ የስነ ልቦናና የአካል ብቃት ስልጠናን እየሰጠ ማህበረሰቡ የሰላም ባለቤት እንዲሆን ስለማስቻሉም ሀላፊዋ ጠቁመዋል፡፡
የሰላም ሰራዊቱ በውል ታሪክ የሚያምን የሰላምና የአንድነት ማስተሳሰሪያ ገመድ መሆኑ በመድረኩ የተነሳ ሲሆን የእውቅና መርሀ ግብሩም ይህንን ተነሳሽነት በማጠናከር በፈጣን ለውጥ ውስጥ የምትገኘው የአዲስ አበባ ከተማ የሰላም አምባሳደር እንድትሆን የተጀመረውን ትጋት ማጠናከር እንደሚገባም በመድረኩ ተመላክቷል፡፡
በራሄል አበበ