AMN – ጥር 9/2017 ዓ.ም
የሰላም አማራጭና የብልጽግና መንገድ የመረጡ ቡድኖች በሀገረ መንግስት ግንባታ ስራዎች ላይ በንቃት እንዲሳተፉ እና የድርሻቸውን እንዲወጡ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ መንግስት አስታውቋል፡፡
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ ሰጥቷል፡፡
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) የሀገሪቱን ሰላምና መረጋጋት በተመለከተ በሰጡት መግለጫ፣ መንግስት ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን በርካታ እንቅስቃሴዎችን ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡
ከብሄርና ፖለቲካ አለመግባባቶች ጋር ተያይዞ በየጊዜው የሚነሱ ግጭቶችን በዘላቂነት ለመፍታት በጸጥታው ዘርፍ ውጤታማ የሆኑ ማሻሻያዎች ማድረጉንም አስታውሰዋል፡፡
በተለያዩ ምክንያቶች ነፍጥ ያነሱ ኃይሎች ጥያቄያቸውን በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ እንዲያቀርቡ መንግስት የሰላም በር ለሁሉም ኃይሎች አኩል ከፍቷል ነው ያሉት ሚኒስትሩ፡፡
በዚህም በጋምቤላ እና ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ታጣቂዎች ጋር የሰላም ስምምነት በመፈጸም ወደ ሰላማዊ ህይወታቸው እንዲመለሱ ማድረግ መቻሉን አንስተዋል፡፡
በተለይም በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የነበሩ ታጣቂዎች ወደ ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅሰቃሴ በመግባት በቅርቡ በተካሄደው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የማሟያ ምርጫ የተወሰኑት የምክር ቤት መቀመጫ ማግኘታቸውንም ሚኒስትሩ አስታውሰዋል፡፡
በተመሳሳይ ከህውሓት ጋር የነበረውን ግጭት በፕሪቶሪያ ስምምነት በመደምደም መንግስት ውጤታማ የሆነ እርምጃ በመውሰድ ለተግባራዊነቱ ያላሰለሰ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡ ስምምነቱ ለህዝብ እፎይታን የሰጠ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
የፕሪቶሪያውን ስምምነት በተሟላ መልኩ ለመተግበርም ሆነ ቀሪ ጉዳዮችን ለማጠናቀቅ መንግስት በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡
በኦሮሚያ ክልል ሲንቀሳቀሱ የነበሩ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ታጣቂዎች እና አመራሮቻቸው የሰላም ጥሪውን ተቀብለው በመግባት የመልሶ መቀላቀል ስልጠናዎችን እየወሰዱ ይገኛሉ ያሉት ሚኒስትሩ በዚህም ረገድ አባገዳዎች፣ ሀደሲንቄዎች ፣ የሃይማኖት አባቶች እና የአካባቢው ነዋሪዎች ሰላም እንዲሰፍን አይተኬ ሚና መጫወታቸውን ተናግረዋል፡፡
በተመሳሳይ በአማራ ክልል በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ታጣቂዎችና አመራሮቻቸው በክልሉ ህዝብና የመንግስት አካላት የቀረበውን የሰላም ጥሪ ተቀብለው ስልጠና ወስደው ወደ ሰላማዊ ህይወታቸው መመለሳቸውን ሚኒስትሩ አስታውቀዋል፡፡ ለዚህም የክልሉ ህዝብ፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና የኃይማኖት አባቶች ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ጠቁመዋል፡፡
በመንግስት በኩል ሰላምን የማስፈን ሂደት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል፡፡
በተሰሩ የህግ ማስከበር ስራዎች በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች የሰላም ሁኔታ በእጅጉ እየተሻሻለ መጥቷል ያሉት ሚኒስትሩ በሸቀጦች ዝውውር፣ በትራንስፖርትና በሰዎች እንቅስቃሴ ላይ ጉልህ ለውጦች በክልሎቹ መታየት መጀመሩን ተናግረዋል፡፡
ይህም መንግስት ለዜጎች ሰላምና መረጋጋት ለመፍጠር ቁርጠኛ አቋም ያለው መሆኑን ያሳያል ነው ያሉት ሚኒስትሩ፡፡
የሰላም አማራጭና የብልጽግና መንገድ የመረጡ ቡድኖች በሀገረ መንግስት ግንባታ ስራዎች ላይ በንቃት እንዲሳተፉ እና የድርሻቸውን እንዲወጡ መንግስት አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርግም ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል፡፡
የሰላም አማራጮችን በመቀበል ለሚገቡ ቡድኖች ዛሬም የመንግስት የሰላም መንገድና በር ክፍት ነው ብለዋል ሚኒስትሩ በመግለጫቸው፡፡
በሰፊና ሁሴን