የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ መጀመሩ ኢትዮጵያ ዘመናዊ የሆነ ኢኮኖሚ ውስጥ እየገባች ለመሆኑ ማሳያ ነው – አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ

You are currently viewing የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ መጀመሩ ኢትዮጵያ ዘመናዊ የሆነ ኢኮኖሚ ውስጥ እየገባች ለመሆኑ ማሳያ ነው – አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ

AMN – ጥር 8/2017 ዓ.ም

የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ በኢትዮጵያ መጀመሩ ሀገሪቱ ዘመናዊ የሆነ ኢኮኖሚ ውስጥ እየገባች ለመሆኑ ማሳያ መሆኑን የምጣኔ ሀብት ምሁሩ አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ ገለጹ።

አቶ ዘመዴነህ በቅርቡ በኢትዮጵያ በይፋ የተጀመረውን የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያን በተመለከተ ከኤ ኤም ኤን ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደተናገሩት፣ ውሳኔው ለበርካታ ዓመታት ሲታለም የነበረ በመሆኑ ታሪካዊ ነው።

በኢትዮጵያ ከ50 ዓመታት በፊት የአክሲዮን ገበያ ይተገበር እንደነበር በማስታወስ፣ አሁን ላይ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ እና ለሁሉም ተደራሽ የሆነ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ መጀመሩ ትልቅ ስኬት ነው ብለዋል።

ይህ ብዙ ጥናት እና ልፋት የተደረገበት ገበያ ዋና ዓላማው የመገበያያ መድረክ መፍጠር መሆኑን ገልጸዋል።

በመድረኩ የግል ድርጅቶች የአክስዮን ድርሻ በመሸጥ የድርጅታቸውን ካፒታል ለማሳደግ እና ለማስፋፊያ ይጠቀሙበታል ብለዋል። እንዲሁም ለኅብረተሰቡም ተደራሽ የመሆን ጠቀሜታ እንዳለው አንሥተዋል።

በሌላ በኩል የመገበያያ መድረኩ ምርት፣ አገልግሎት እና ሐሳብ የሚሸጥበት በመሆኑ ጀማሪ ሥራ ፈጣሪዎች ሐሳባቸውን እንዲሸጡ ዕድል ይፈጥርላቸዋል ነው ያሉት።

ገበያው ከዚህ ቀደም ተቆጣጣሪ አካል አልነበረም ያሉት ምሁሩ፣ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ በመጀመሩ ማንኛውም ድርጅት ለሽያጭ ከመቅረቡ በፊት ተፈትሾ ጥቅም እና ጉዳቱ ተጠንቶ ለገበያ እንደሚቀርብ አብራርተዋል።

በተጨማሪም ገበያው የውጭ ኢንቨስተሮች የኩባንያ ድርሻ እንዲገዙ ዕድል የፈጠረ በመሆኑ የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ያግዛል ብለዋል።

የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ የመንግሥትን ኢኮኖሚ ለማሳደግ ትልቅ አስተዋፅኦ እንደሚያደርግ ነው አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ ያብራሩት።

በኢትዮጵያ የተጀመረው የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ሙሉ በሙሉ ኤሌክትሮኒክስ መሆኑ እና ሂደቱን ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ሕጎች መኖራቸው ደግሞ በበጎ የሚነሳ መሆኑን ተናግረዋል።

በጉዳዩ ዙርያ ለኅብረተሰቡ ሰፊ የሆነ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ በመሥራት ሕዝቡን ማስተማር እንደሚያስፈልግም ምክረ-ሐሳብ ሰጥተዋል።

በሰፊና ሁሴን

May be an image of 1 person

All reactions:

1717

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review