AMN ጥር 11/2017 ዓ.ም
የሰው ልጅ ዘላቂ ሕይወትን መቀዳጀት የሚችለው ፈርሃ እግዚአብሄርን መላበስ ሲችል መሆኑን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘ ኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት አስገነዘቡ፡፡
የዘንድሮው የጥምቀት በአል ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በተገኙበት በአዲስ አበባ ጃንሜዳ በልዩ ልዩ ዝግጅቶች ተከብሯል ፡፡
ብፁእነታቸው በበአሉ ላይ እንዳሉት ቤተክርስቲያኗ በአደባባይ ከምታከብራቸው ሃይማኖቶታዊ በዓላት መካከል ጥምቀት አንዱ መሆኑንና በአሉ ኢየሱስ ክርስቶስ በባህረ ዮርዳኖስ በዮሃንስ እጅ መጠመቁን በማሰብ የሚከበር ታላቅ ሃይማኖታዊ በዓል ነው።
በአሉ በልዩ ልዩ ሀይማኖታዊ ክንዋኔዎች በድምቀት በመከበር ላይ እንደሚገኝም አስታውቀዋል ።
የሰው ልጅ ዘላቂ ሕይወትን መቀዳጀት የሚችለው ፈርሃ እግዚአብሄርን መላበስ ሲችል ነው ያሉት ብፁእ ወ ቅዱስ አቡነ ማቲያስ እርስ በእርስ በመፋቀርና በመከባበር የፈጣሪን ትእዛዝ መጠበቅ እንደሚገባ አስታውቀዋል ፡፡
ሁሉም ዜጋ በፍቅርና በአብሮነት ለሀገር ሰላም እና እድገት በመቆም የሚጠበቅበትን ሃላፊነት መወጣት እንዳለበትም አስገንዝበዋል።
ህብረተሰቡ ፈጣሪ የሰጠውን ጸጋ በመጠቀም እርስ በእርስ በመተሳሰብና በአብሮነት ለሀገር ሰላም እና እድገት ማነቆ የሆኑ ችግሮችን መቅረፍ እንደሚኖርበት በማስገንዘብ የእንኳን አደረሳችሁ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል ፡፡