የሳይክል ሀገር- ኔዘርላንድስ

You are currently viewing የሳይክል ሀገር- ኔዘርላንድስ

AMN- ግንቦት 26/2017 ዓ.ም

ኔዘርላንድስ ለ18 ሚሊየን ዜጎች መኖሪያ ስትሆን 24 ሚሊየን ሳይክሎች አሏት፡፡

ከ19ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ጀምሮ ሳይክል መጠቀም የጀመሩት ኔዘርላንዳዊያን፣ በፈረንጆቹ 1940 ገደማ 4 ሚሊየን ሳይክል ብቻ ነበራቸው፡፡

በወቅቱ የሀገሪቱ ህዝብ ቁጥር 8 ሚሊየን ነበር፡፡

በተለይም በፈረንጆቹ 1971 ላይ በአንድ ዓመት ብቻ 500 ህፃናትን ህይወት የቀጠፈው የትራፊክ አደጋ ያስከተለው “የህፃናት ሞት ይቁም” የተሰኘው የህዝብ ተቃውሞ እና የነደጅ እጥረት የሀገሪቱ መንግስት የትራንስፖርት ፖሊሲውን እንዲከልስ አስገድዶታል፡፡

ትኩረቱን በሳይክል መሠረተ ልማት ላይ በማድረግም አሁን ላይ 35 ሺህ ኪሎ ሜትር የሳይክል መንገድ በሀገሪቱ ተገንብቷል፡፡

ዜጎች ሳይክልን ከሌላው ትራንስፖርት ይልቅ አብልጠው ይወዳሉ፡፡

በርካታ ኪሎ ሜትሮችንም በየቀኑ በሳይክል መጓዝ እጅግ የተለመደ ነው፡፡

ወጣቶች ብቻ ሳይሆኑ አዛውንቶችም ጭምር በሳይክል ሲጓዙም ሲዝናኑም ማየት ብርቅ አይደለም፡፡

ሳይክል በአንድ ወቅት የሀገሪቱ ብሔራዊ ምልክት ተደርጎ ይቆጠር ነበር፡፡

አሁን የኔዘነርላንድስ ህዝብ ቁጥር 18 ሚሊየን የደረሰ ሲሆን፣ የሳይክል ብዛት ደግሞ 24 ሚሊየን ነው፡፡

በዚህ ልዩ ልማዳቸው ከፍተኛ ጎብኚዎችን ከመሳባቸውም በላይ፣ በየዓመቱ 6 ሺህ 500 ሞት መቀነስ የቻሉ ሲሆን፣ የመኖር ዕድሜ ጣሪያቸውም ተሻሽሏል፡፡

ጃፓን እና ጀርመን በሳይክል ትራንስፖርት ረገድ ከኔዘርላንድስ ቀጥሎ የተሻለ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሀገራት ናቸው፡፡

ከአፍሪካ ደግሞ ኢትዮጵያ “መንገድ ለሰው ” በሚል መርህ በመንግስት ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶት በኮሪደር ልማቱ በተለይም አዲስ አበባ ላይ የሳይክል መንገዶች ተሠርተዋል፡፡

ይህ ይበል የሚያሰኝ ተግባር በክልል ከተሞችም ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡

ዜጎችም ሳይክልን የተሻለ የትራንስፖርት አማራጭ አድርገው መጠቀም ጀምረዋል፡፡

ጋና፣ ሩዋንዳ፣ ዩጋንዳ እና ኬኒያም የሳይክል መሠረተ ልማት ላይ እየሰሩ ከሚገኙ ሀገራት መካከል ናቸው፡፡

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የዓለም ሳይክል ቀን ሁሌም በየዓመቱ ሰኔ ሶስት ላይ እንዲከበር የወሰነው በፈረንጆቹ 2018 ነው፤ እነሆ ዛሬ የዓለም የሳይክል ቀን ነው፡፡

ዋና ዓላማውም የሰው ልጅ እንቅስቃሴ እየተገደበ የመጣባትን ዓለም ነባራዊ ሁኔታ ለመቀየር እና ጤናውንም ለመጠበቅ ዓላማ ያደረገ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በማሬ ቃጦ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review