የሴቷን ሸክም ያቀለሉ ልማቶች

You are currently viewing የሴቷን ሸክም ያቀለሉ ልማቶች

ሴትነት ትልቅ የተፈጥሮ ፀጋ ነው፡፡ በሴትነት ውስጥ እናትነት አለ፡፡ እናትነት ደግሞ ‘ሰው ሆኖ ሰው መፍጠር’ ያለበት ግሩም በረከት ነው። እናት ልጆቿን ለማሳደግ የማትገፋው ተራራ፣ የማትፈነቅለው ቋጥኝ እንደሌለ ከብዙዎቻችን የልብ ማህደር የማይጠፋው የብዙነሽ በቀለ ‘የእናት ውለታዋ’ የተሰኘው ስራዋ ሚዛን ይደፋል፡፡

የእናት ውለታዋን ባወሳ እወዳለሁ፣

 ደግነቷ ብዙ መሆኑን አውቃለሁ፡፡

 ወላጅ እናት እኮ ፍፁም በመንፈሷ፣

 ልጇን ትወዳለች አስበልጣ ከራሷ፡፡

 ዘጠኝ ወር በሆዷ ከዚያም በጀርባዋ፣

 ጡቷን እያጠባች እኔን ማሳደጓ፡፡

 ዘወትር ይሰማኛል የማዬ ድካሟ፣

 ጥራ በማሳደግ በሴትነት አቅሟ፡፡

 አባቴ ሞቶብኝ በሕፃንነቴ፣

ደክማ አሳደገችን ብቻዋን እናቴ፡፡              ትላለች ብዙነሽ፡፡

በርግጥም ሴቷ በተለያዩ ምክንያቶች ብዙ የችግር ተራራዎችን ትወጣለች፤ ትወርዳለች፡፡ በዚህ ፅሑፍ ዛሬ በመላው ዓለም የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን ምክንያት በማድረግ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በአዲስ አበባ ከተማ የሴቷን ሸክም ለማቅለል ከተከናወኑ ስራዎች መካከል የተወሰኑትን  እንመለከታለን፡፡

ከዝግጅት ክፍላችን ጋር ቆይታ ያደረጉት የማህበራዊ ሳይንስ ባለሙያው አቶ ገነነ ካሳሁን እንደሚሉት እንደ አዲስ አበባ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ለማህበራዊና ለኢኮኖሚያዊ ችግሮች የተጋለጡ ሴቶችን ታሳቢ ያደረጉ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡ በተለይም ‘ለነገዋ’ የሴቶች ተሃድሶና ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል ትልቅ እይታ ነው፡፡ ቀን ጨልሞባቸው ጎዳና የወጡ ሴቶችን ታሳቢ ያደረገ መሆኑ እንደከተማ በቅርብ ዓመታት የሴቶችን ኑሮ ለማሻሻል ከተሰሩ ተግባራት አንዱ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

እንደ ማህበራዊ ሳይንስ ባለሙያው በዓመት አንድ ጊዜ ከሚደረጉ ተግባራት ባሻገር  እንዲህ ወደ ማህበረሰቡ ወረድ ብሎ በዘላቂነት ለውጥ ማምጣት የሚችሉ ተግባራትን ማከናወን ፋይዳው ከፍ ያለ ነው፡፡ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ ሴቶችን ታሳቢ ያደረጉ የተለያዩ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡ በተለይም ሴቶች በአመራርነት ቦታዎች በስፋት እንዲሳተፉ በማድረግ ውጤት እያመጡ ነው፤ በተለይም በአዲስ አበባ ሴቶችን ታሳቢ ያደረጉ በርካታ ስራዎች በመከናወን ላይ ናቸው፡፡

በተማሪዎች ምገባ መርሃ ግብርም የስራ ዕድል የተፈጠረላቸውና ምግቡን የሚያበስሉት እናቶች ከመሆናቸው ባሻገር ይህ መርሃ ግብር ከመጀመሩ በፊት በርካታ ተማሪዎች ባዶ ምሳ ዕቃ ይዘው ወደ ትምህርት ቤት የሚመጡበት፣ በርሃብ ምክንያት ለተለያዩ ችግሮች የሚዳረጉበት ሁኔታ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ በመሆኑም በዚህ ሁኔታ በይበልጥ ለልጆቻቸው የሚቋጥሩት ሲያጡ ልባቸው የሚሰበረው፣ መንፈሳቸው የሚረበሸው እና በተለያየ መልኩ የሚጎዱበት እናቶች ናቸው፡፡ በመሆኑም የምገባ መርሃ ግብሩ በተማሪዎች፣ በመማር ማስተማሩና መሰል ተያያዥ ጉዳዮች እያመጣ ያለው ለውጥ እንዳለ ሆኖ የእናቶችን ሸክም ያቀለለ ነው፡፡

ገላን ጉራ የእንጀራ ማዕከልም በተለይ ለሴቶች አዲስ የስራ ዕድልን የፈጠረ ነው፡፡ በእንጀራ ማዕከሉ የስራ እድል ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል ወይዘሮ ቡዙአየሁ ክብረት አንዷ ናቸው። በማዕከሉ የስራ እድል ተጠቃሚ መሆናቸው ከኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ባሻገር ከሰዎች ጋር ለመተዋወቅ፣ ከቤት ወጥቶ ለመግባት ዕድል እንደፈጠረላቸው ይናገራሉ፡፡ ለወደፊቱም የተሻለ ስኬትን ለማስመዝገብ መነቃቃትና ብርታት እንደሆናቸው ይመሰክራሉ፡፡

በጉለሌ ክፍለ ከተማ እንጦጦ አካባቢ የተገነባው የጉለሌ የተቀናጀ የልማት ስራ ደግሞ  በዋነኛነት በአካባቢው እንጨት ከጫካ በመልቀም ለሚተዳደሩ የአካባቢው ነዋሪዎች የስራ ዕድል የፈጠረ ነው፡፡ ይህ ፕሮጀክት ባሳለፍነው ዓመት ሚያዚያ ወር ላይ ወደ አገልግሎት መግባቱ ይታወሳል፡፡

በማዕከሉ በአካባቢው እንጨት በመልቀም ለሚተዳደሩ 551 እናቶች የስራ እድል  ተፈጥሮላቸዋል፡፡ የእንጀራ ማዕከሉ በውስጡ ሁለት የእንጀራ መጋገሪያ ህንጻዎች፣ የህጻናት ማቆያ፣ የእህል ማከማቻ፣ ወፍጮ እንዲሁም ልዩ ልዩ አገልግሎት የሚሰጡ ግንባታዎችን ያካተተ ነው፡፡ 551 እናቶች በሁለት ፈረቃ ተከፍለው እየሰሩበት ያለው ማዕከሉ 450 ዘመናዊ የእንጀራ መጋገሪያ ምጣድ የተገጠመለት፣ ዘመናዊ የሊጥ ማቡኪያ ማሽን፣ ዘመናዊ የአብሲት መጣያ ማሽንና ሁለት ወፍጮዎች ያሉት ነው፡፡

በከተማዋ የሴቶችን ጫና ለማቅለል የተሰሩ ተግባራት ምን ያህል ችግር እየፈቱ ስለመሆኑ ከዝግጅት ክፍላችን ጋር ቆይታ ያደረጉት በአዲስ አበባ ሽሮ ሜዳ አካባቢ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ አዳነች ተፈራ  ምስክር ናቸው፡፡ ወይዘሮዋ ልጆቻቸውን ለማሳደግ ከቀን ስራ ጀምሮ ያልሰሩት የጉልበት ስራ የለም፡፡ የዕድሜያቸውን ማምሻ ያሳለፉት ግን ቅጠል ለቅመው፣ እንጨት ሰብስበው በጀርባቸው እየተሸከሙ በመሸጥ ነበር።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለተማሪዎች ምግብ፣ ደንብ ልብስ እና የመማሪያ ቁሳቁስ ከማቅረቡ በፊት “እኔ ሳልማር ልጆቼም እንደኔ መሃይም መሆን የለባቸውም በሚል እንጨት ለቅሜ በማገኘው ገቢ ደብተር፣ እስክርቢቶና ለመማር የሚያስፈልጉ ሌሎች ግብዓቶችን ሁሉ አሟልቼ ነበር ልጆቼን የማስተምራቸው” የሚሉት እኝህ እናት ለዚህም ሲሉ ቢታመሙ፣ ነፍሰ ጡር ሲሆኑና ወልደው እንኳን በቂ እረፍት እንደማያደርጉ ተናግረዋል፡፡

አስተያየት ሰጪዋ የልጆቻቸውንና የቤተሰባቸውን ልብስም ሆነ ቀለብ ለማሟላት የሚያስችል ሌላ ገቢ ስለሌላቸው ወልደው እንደሴት በቅጡ አለመታረሳቸውና በተደጋጋሚ የስራ ጫና ማሳለፋቸው ከዕድሜ መግፋት ጋር ተያይዞ ለጉዳት እንደዳረጋቸው ያስታውሳሉ፡፡

እንደ ወይዘሮ አዳነች ሙሉ ቀን ጭራሮ እንጨት ለቅማ በየመንደሩ አዙራ 60 እና 70 ብር የምትሸጥ እናት ከድህነት ለመውጣት ከመቸገሯ በላይ እንጨቱ እየጠፋ፣ ክልከላውም እየበረታ ሲሄድ ከዕድሜ መጫጫን ጋር ተስፋ መቁረጥ እየመጣ መሄዱንም አልሸሸጉም። የጉለሌ የተቀናጀ ልማት ግን ይህንን አስከፊ ሕይወት እንደቀየረላቸው ገልፀውልናል፡፡

በመለሰ ተሰጋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review