በመላው ዓለም የሚገኙ ክርስቲያኖች የኢየሱስ ክርስቶስን የስቅለት በዓል በዛሬው ዕለት አስበው ይውላሉ፡፡
በዓሉ ከሚከበርባቸው መካከል ኢየሩሳሌም አንዷ ነች፤ በኢየሩሳሌም የእምነቱ ተከታዮች ከእንጨት የተዘጋጁ መስቀሎችን በመሸከም ኢየሱስ ክርስቶስ ያለፈባቸውን መንገዶች እና ቦታዎች በማለፍ ስቃዩን እና መከራውን በማሰብ እንዲሁም የተለያዩ ሃይማኖታዊ ሥነ-ስርዓቶችን በመከወን ያከብራሉ፡፡
በዓለም ላይ የኢየሱስ ክርስቶስ የስቅለት በዓል ታስቦ ከሚውልባቸው ሀገራት መካከል ሩሲያ ቀዳሚዋ ሀገር ናት፤ በሩሲያ የኢየሱስ ክርስቶስ የስቅለት በዓል በፆም፣ ጸሎት እና ቅዳሴ ይከናወናል፡፡
በዩክሬን ምዕመናኑ ዕለቱን የተለየ የንሰሀ ቀን በማድረግ በጉልበታቸው ተንበርክከው በፆም እና በጸሎት የኢየሱስ ክርስቶስን ስቅለት እና ሞት በማሰብ ያሳልፋሉ፡፡
በአውስትራሊያ ሲድኒ በዝማሬ፣ በፆም እና በጸሎት የፈጣሪያቸውን ስቅለት በማሰብ ይውላሉ፡፡
በፊሊፒንስ ክርስቶስ የሰው ልጆችን ለማዳን የከፈለውን መስዋዕትነት ጀርባቸውን በመግረፍ ስቃዩን እና መከራውን በማሰብ ያከብራሉ፡፡
የስቅለት በዓል ከሚከበርባቸው የዓለማችን ሀገራት መካከል ቤሩት/ሊባኖስ አንዷ ነች፡፡ በሊባኖስ ዕለቱ በቅዳሴ ሥነ-ስርዓት ታስቦ ይውላል፡፡
ፓኪስታን እና አየርላንድ የኢየሱስ ክርስቶስን የስቅለት በዓል አስበው የሚውሉ እና ዕለቱንም በተለያዩ ሥነ-ስርዓቶች ከሚያከብሩ ሀገራት መካከል ተጠቃሾች ናቸው፡፡
በዓሉ በግሪክ እና በስፔን በተለየ መንገድ ታስቦ የሚውል ሲሆን፣ ህዝበ ክርስቲያኑ ወደ አቢያተ ክርስቲያናት በማቅናት በፆም፣ በጸሎት እና በዝማሬ እንዲሁም በተለያዩ ሃይማኖታዊ ሥነ-ስርዓቶች በዓሉን የሚያከብሩበት ጊዜ ነው፡፡
በዓሉ በሀገራችን ኢትዮጵያም፤ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን፣ በካቶሊካዊት ቤተ-ክርስቲያን እና በወንጌላውያን አቢያተ-ክርስቲያናት ህብረት አማኞች ዘንድ በድምቀት ይከበራል፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ዘንድ በዓሉ ከጠዋት ጀምሮ በፆም፣ በጸሎት፣ በስግደት እና በተለያዩ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች ነው የሚከበረው፡፡
በካቶሊካዊት ቤተ-ክርስቲያንም በፆም፣ በጸሎት፣ በስግደት እና በተለያዩ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች ይከበራል፡፡
በወንጌላውያን አቢያተ-ክርስቲያናት ህብረት አማኞች ዘንድም የስቅለት በዓል በጸሎት፣ በዝማሬ እና በትምህርት ታስቦ ይውላል፡፡
በታምራት ቢሻው