ብዙዎች ባርነትን ቡጢ የገጠመው ቦክሰኛ ሲሉ ይጠሩታል፤ በቀለሙ ምክንያት መገለልና መድሎ፣ ባስ ሲልም ለእስር ጭምር ተዳርጎ የነበረውን ጥቁር አሜሪካዊውን ጃክ ጆንሰንን፡፡ እ.ኤ.አ በ1870 የተወለደው ጃክ ጆንሰን ከነጭ ወንዶች ልጆች ጋር ነው ያደገው። በጄፍሪ ዋርድ የተጻፈው “ጥቁርነት፣ የጃክ ጆንሰን አነሳስና ፍጻሜ” የተሰኘው መጽሐፍ ላይ እንደሰፈረው መረጃ ጃክ የቀለም ጉዳይ የማያሳስበው፣ በወቅቱ ለነበረው የነጭ እና ጥቁር ስርዓታዊ ልዩነት ግድ የሚለው ሰው አልነበረም፡፡ የኋላ ኋላ ግን በቀለሙ ምክንያት ይደርስበት የነበረው መገለልና መድሎ ቡጢኛውን ወደ ነጻነት ታጋይነት ቀይሮታል፡፡
ጥቁሮች ከነጻነት በፊት በየትኛውም ስፖርት አይነት ላይ የመሳተፍ መብት አልነበራቸውም፡፡ ከነጮቹ ጋር ተሰልፎ መጫወት እንደ መገዳደር ይቆጠር ስለነበር የሚታሰብ አልነበረም፡፡ የነጭ የበላይ ለዘመናት ተንሰራፍቶ በቆየበት በዚህ ወቅት ይህንን የተሳሳተ አካሄድ የሚቀለብስ አጋጣሚ በኢትዮጵያ ሰማይ ስር ተከሰተ። በኢትዮጵያዊያን ብርቱ ክንድ የተገኘው የዓድዋ ድል በመላው ጥቁር ህዝቦች ዘንድ የነፃነት ትግል ችቦን አቀጣጠለ፡፡ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ዝነኛ፣ ጠንካራና ስመ ጥር ጥቁር ስፖርተኞች ለጥቁር ህዝብ መብትና ነፃነት መታገል እና በየአጋጣሚው ዘረኝነትን ማውገዝ ስለመጀመራቸው የ“Sport, Colonialism and Struggle” መፅሐፍ ደራሲ ሲ.ኤል.አር ጄምስ በመፅሐፋቸው አስፍረዋል፡፡ ቦክሰኛው ጃክ ጆንሰን ከእነዚህ ስፖርተኞች መካከል አንዱ ነው።
ጃክ ጆንሰን የራሱንና የችግረኛ ቤተሰቡን ህይወት ለማሸነፍ ብዙ ውጣ ውረድ አሳልፏል፡፡ ለቦክስ ስፖርት በ16 ዓመቱ ወደ ኒውዮርክ ከተማ ያቀናው ጆንሰን ፈረሶችን ስፖርት የማለማመድ ስራ ሰርቷል፡፡ በፅዳት ሰራተኛነት ተሰማርቶም የቦክስ ጓንቶችን ለመግዛት ገንዘብ ይቆጥብ እንደነበር የህይወት ታሪኩ ያወሳል።

ተስፋ የማይቆርጠው ጃክ ጆንሰን በአንድ ጀርመናዊ ግለሰብ ይተዳደር በነበረ ጂም ውስጥ ሲቀጠርም አጋጣሚውን ተጠቅሞ ይፈልገው ወደነበረው የቦክስ ስፖርት ገብቷል፡፡ ጆንሰን ለመጀመሪያ ጊዜ ፕሮፌሽናል ቦክሰኝነት ውድድር የጀመረው እ.ኤ.አ በ1890 ነበር። በቀጣዩ ዓመት ራሱን “ጥቁር የከባድ ሚዛን ሻምፒዮን” ብሎ ካወጀው ክሎንዲክ ጋር ተፋልሞም አሸንፏል። ይሁንና ጃክ ጆንሰንም ለቦክስ ግጥሚያ ብዙ ቦታ ተንከራቷል። “ነጭ ቦክሰኞች ጥቁር ስለሆንክ ካንተ ጋር የቦክስ ውድድር አንገጥምም” ብለው ፊት ነስተውትም ያውቃል፡፡ አንዳንድ ጊዜም ከነጮች ጋር መፋለም ብቻ ክፍያው ሆኖም ተቧቅሶ ያውቃል፡፡ በ72 ፍልሚያዎች ድል ያደረገው ቡጢኛ ጃክ ጆንሰን በ68 ዓመቱ በመኪና አደጋ ህይወቱ አልፏል፡፡
ዓለም በአንድ ወቅት የሰዎችን ቀለም የልዩነት መስፈሪያ አድርጋ ተጠቅማም ታውቃለች፡፡ አውሮፓውያን አፍሪካን በቅኝ ግዛት ተቀራምተው በነበሩበት ወቅት የጥቁር ስፖርተኞች ቁጥርም አነስተኛ ነበር፡፡ በጊዜ ሂደት እየተቀየረ ይምጣ እንጂ በስፖርት ዘርፍ ጥቁሮች ከነጮች ጋር እኩል አይሳተፉም የሚል ህግ እስከመውጣት ደርሶም ያውቃል፡፡ ይሁንና እንደ ጆስ ኦነስ ያሉ ጥቁር አፍሪካ አሜሪካዊያን ስፖርተኞች ይህንን ታሪክ ለመቀየር ታግለዋል፡፡
ጆስ ኦነስ ጥቁር አፍሪካ አሜሪካዊ ሲሆን፣ እ.ኤ.አ በ1913 በአሜሪካ ኦክቪል አልባማ ግዛት ውስጥ ነበር የተወለደው። በወላጆቹና በአካባቢው ባለው ምቹ ሁኔታ በስፖርት ታንፆ ያደገው ኦነስ እ.ኤ.አ በ1936 በበርሊን ከተማ በተካሄደው የኦሎምፒክ ስፖርት ውድድር አራት የወርቅ ሜዳሊያዎችን ጠራርጎ በመውሰድ በዓለም የተወደሰ ስፖርተኛ ሆነ፡፡ ዘመኑ የጥቁር ጥላቻም ያየለበት ወቅት ነበርና ከድሉ በኋላም የወቅቱ የጀርመን መሪ የነበሩት አዶልፍ ሂትለር የእጅ ሰላምታ ሰጥተው እንኳን ደስ አለህ ለማለት አልፈቀዱም። ለዚህ ዐቢይ ምክንያቱ ደግሞ የኦነስ የመልኩ ቀለም ጥቁር መሆኑ ነበር።
በኦሎምፒክ ውድድሩ ሁለተኛ ቀንም ኦነስ ድጋሚ ያሸንፋል፤ በዚህ ጊዜ በነጭ የበላይነት መንፈስ የተሞሉት አዶልፍ ሂትለር እሱን እንኳን ደስ አለህ ላለማለት ይወስናሉ። ከዚያም በሜዳ ውስጥ ማንንም አሸናፊ ሰላምታ ላለመስጠትና በአደባባይ እንኳን ደስ አላችሁ እንደማይሉ ያስታውቃሉ። በዚህ ውሳኔያቸውም የዓለም አቀፍ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት በሂትለር ያልተገባ ውሳኔ ደስተኛ አልነበሩም። ለዚህ ብስጭታቸው መነሻ ደግሞ ሂትለር ስታዲየሙን ለቅቀው ከመውጣታቸው በፊት የጀርመን እና የፊላንድ ዜግነት ላላቸው ስፖርተኞች ሰላምታ መስጠታቸው እና እንኳን ደስ አላችሁ ማለታቸው ነበር።
እንደዚህ ዓይነት የዘር ጥላቻ ሳይበግረው በበርሊኑ ኦሎምፒክ በርካታ ድሎችን የተጎናፀፈው ኦነስ በመጀመሪያ በዓለም አቀፍ አማተር ከአትሌቲክስ ፌዴሬሽን በመቀጠል ደግሞ ከዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ማህበር ፌዴሬሽን ከፍተኛ እውቅና ተበርክቶለታል። እንደ አውሮፓ ዘመን አቆጣጠር በ1976 የነፃነት ሜዳሊያን ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት የመሸለም ዕድል አግኝቷል። መልካም ስራና ስም ከመቃብር በላይ ያስጠራል እንዲሉ ኦንስ ከሞተ በኋላም እ.ኤ.አ በ1990 ስለ መልካም ስራው ከአሜሪካ ምክር ቤት የወርቅ ሜዳሊያ ተበርክቶለታል።
ሌሎቹ የጥቁርን መድሎ በመቃወም ትግል የፈፀሙት ቶሚ ስሚዝና ጆን ካርሎስ ናቸው። እነዚህ ሁለት ጥቁር ወጣቶች እንደ አውሮፓዊያን ዘመን አቆጣጠር በ1967ቱ ኦሎምፒክ የወርቅና የነሃስ ሜዳሊያን አግኝተዋል። ታዲያ በዚህ ወቅት በጥቁሮች ላይ የሚፈፀመው የጥቁር ጥላቻ ያንገፈግፋቸው ስለነበር ይህንን ግፍ እና በደል ለመቃወም ጥቁር የእጅ ጓንት አድርገው በብዙ ሺህ ህዝብ ፊት ተቃውሟቸውን አሳይተዋል። “መብታችንን ለማስከበርና ነፃነታችንን ለማወጅ አቅም አግኝተናል” የሚሉት እነዚህ ወጣቶች በኦሎምፒክ መድረኩ ላይ ባሰሙት የነፃነት ተቃውሞ በአክራሪ ነጮች ዘንድ በሰፊው ተወግዘዋል።
በስፖርቱ ዘርፍ ዘረኝነትን በብርታት የታገለው ሌላኛው ስፖርተኛ ቦክሰኛው ሙሀመድ አሊ (ካሴስ ክሌይ) ነው። ሙሀመድ አሊ ከዝነኛ የቦክስ ስፖርተኛነት ባሻገር የሰብዓዊ መብት ተሟጋችና በመልካም ስብዕናውም ለዓለም ተምሳሌት የሚሆን ቡጢኛ ሆኖ መዝለቅ የቻለ ነው። ከቦክስ ስፖርቱ ባሻገርም ለኃይማኖት ነፃነት እና የዘር መድሎዎችን በስፋት ይታገልም እንደነበር ጆሴ ማርቲኔዝም “ዓለምን የቀየሩ ጥቁር አትሌቶች” በሚል ርዕስ ባወጣው ጽሑፍ ላይ ሰፍሯል፡፡
ጥቁር አፍሪካ አሜሪካዊ የሆነው ሙሀመድ አሊ በሚያደርገው የነፃነት ትግልም ለብዙ ጥቁሮች የነፃነትን መስኮት እንደከፈተም ይነገርለታል። ሙሀመድ አሊ በዚያ ስምና ዝናው በናኘበት ወቅት በአብዛኛው የነጭ ማህበረሰብ ዘንድ ጥቁር መሆን የተሰጠውን የተዛባ ትርጉም ያለ አንዳች ማወላወል ታግሏል። ሙሀመድ አሊ ሊስተንን በማሸነፍ ሻምፒዮናነቱን ባረጋገጠበት ወቅት ስለጥቁር ነፃነት አምርሮ መናገሩ ለሌሎች ጥቁር አትሌቶች መነሳሳትን ፈጥሯል። በርካቶች ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ከሙሀመድ አሊ ጎን በመቆም የጭቆና ቀንበሩን ተቃውመዋል።
ከላይ እንደጠቀስነው የኋላ ኋላ በብዙ ትግል በስፖርቱ እኩል የመሳተፉ መብቱ ቢመጣም ወደ አሸናፊነት ለመምጣት ግን ፋና ወጊ ስፖርተኞች አስፈልገው ነበር። የፋናወጊነቱን ሚና ለመወጣት ደግሞ ኢትዮጵያውያን አትሌቶችም የነበራቸው ድርሻ ቀላል አልነበረምና ጥቂቶቹን አስታውሰን ጽሑፋችንን እንቋጭ፡፡
የመጀመሪያው ኦሎምፒክ በግሪኳ አቴንስ ከተማ ከ128 ዓመታት በፊት በ14 ሀገራት ተሳትፎ እንደተጀመረ ታሪክ ያወሳል፡፡ በዚሁ ወቅት ከአንድ ወር ቀደም ብሎ ባሉት ጊዜያት ኢትዮጵያ በቅኝ ለመያዝ የወረረቻትን ጣሊያን በዓድዋ ተራሮች ግርጌ ድል አድርጋት ነበር፡፡ 60 ዓመታት አልፈው ኢትዮጵያ በታላቁ የኦሎምፒክ መድረክ እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር በ1956 በአውስትራሊያዋ ከተማ ሜልቦርን ለመጀመርያ ጊዜ የተሳተፈችበት የኦሎምፒክ መድረክ ነበር፡፡
እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር ከ4 ዓመታት በኋላ በ1960 ኢትዮጵያ የኦሎምፒክ ተሳትፎዋን በወርቃማ ድል ጀመረች፡፡ በወቅቱ የክቡር ዘበኛ ወታደር የነበረው አበበ ቢቂላ ሮም ባስተናገደችው ኦሎምፒክ በባዶ እግሩ ሮጦ ማራቶንን አሸንፎ ዳግም ለነጻነት ተምሳሌት የሆነችበት ታሪክ ይታወሳል። በዓድዋ ድል አብነት ነፃነቷን እንዳገኘች ሁሉ አህጉረ አፍሪካ ዓለምን በአትሌቲክስ ማሸነፍን በኢትዮጵያዊያን ተጋድሎ ጀመረች፡፡
በሳህሉ ብርሃኑ