የቻይናው ሻንሀይ ላውንች ዲዛይን አውቶሞቲቭ ኩባንያ በኢትዮጵያ ውስጥ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በማምረት ላይ መሰማራት እንደሚፈልግ የኩባንያው ሥራ አስኪያጅ ው ሻውሀን ገልፀዋል፡፡
የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር አለሙ ስሜ (ዶ/ር) የሻንሀይ ላውንች ዲዛይን አውቶሞቲቭ ኩባንያ ተወካዮችን በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡
በውይይቱም ሚኒስትሩ፣ መንግስት አረንጓዴ ትራንስፖርትን ለማስፋፋት በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የኩባንያው ስራ አስኪያጅ ው ሻውሀ እና የኩባንያው አመራሮችም፣ በትራንስፖርት እና ሎጂስክስ ዘርፍ በተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ ገለፃ ተደርጎላቸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ጂኦግራፊያዊ መገኛ፣ እያደገ የመጣ ሀገራዊ ኢኮኖሚ፣ ጠንካራ የመንግስት ድጋፍ፣ የታክስ ማበረታቻዎች፣ በዘርፉ በቂ የሰው ሃይል መኖር ለኢንቨስትመንት አስቻይ ሁኔታዎች እንደሆኑ ተገልጾላቸዋል፡፡
በሀገሪቱ ያለውን እምቅ የሆነ ታዳሽ የኃይል ምንጭ በመጠቀም አረንጓዴ ትራንስፖርትን ለማስፋፋት በቁርጠኝነት እየተሰራ እንደሚገኝም ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ላይ መዋዕለ ንዋይን ማፍሰስ አዋጭ መሆኑን ያነሱት ሚኒስትሩ፣ መንግስት በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ማምረት ላይ የሚሰማሩ ኩባንያዎችን ይደግፋል ብለዋል፡፡
ሻንሀይ ላውንች ዲዛይን አውቶሞቲቭ ኩባንያ የተለያዩ ዓይነት ተሽከርካሪዎችን በማምረት ለገበያ የሚያቀርብ እንደሆነ የኩባንያው ተወካዮች አብራርተዋል፡፡
ኩባንያው በኤሌክትሪክ የሚሰሩ የአየር ታክሲ እና ሰው አልባ ተሽከርካሪዎችን ጨምሮ፣ አውቶሞቢሎችን፣ አውቶብሶችን እና የጭነት ተሽከርካሪቸዎችን እንደሚያመርት ገልጿል፡፡
የሻንሀይ ላውንች ዲዛይን አውቶሞቲቭ ኩባንያ ስራ አስኪያጅ ው ሻውሀን፣ ኩባንያቸው በኢትዮጵያ ውስጥ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በማምረት ላይ መሰማራት እንደሚፈልግ ገልፀዋል፡፡
የትራንስፖርት እና ሎጂስክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶክተር) ኩባንያው የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በማምረት ስራ ቢሰማራ የበለጠ አዋጭ እንደሚሆንለት እና ድጋፍ እንደሚደረግለት ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም ኢትዮጵያና ቻይና ካላቸው ኢኮኖሚያዊና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አንፃር ኩባንያው በሚያደገው የኢንቨስትመንት ተሳትፎ ከሚያገኘው ኢኮኖሚያዊ ትርፍ ባሻገር የሁለቱን ሀገራት ወዳጅነት የበለጠ ያጠናክራል ማለታቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡