የቀይ ባሕር አካባቢን የጂኦ-ፖለቲካ ሰላምና ደኅንነት ለማስጠበቅ የቀጣናው ሀገራት ትብብር ወሳኝ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ጃፋር በድሩ ተናገሩ።
3ኛው የቀይ ባሕር ቀጣናዊ ጂኦ-ፖለቲካ ፎረም “የቀይ ባህር እና የኤደን ባህረ ሰላጤ ቀጣና ሀገራት ለኢኮኖሚያዊ፣ ለደኅንነት ትብብር እንዲሁም መልካም አጋጣሚዎች፣ ተግዳሮቶች እና የቀጣይ አቅጣጫዎች” በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ የምክክር መድረክ እየተካሄደ ይገኛል።
በመድረኩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የስራ ኃላፊዎች፣ የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት የስራ ኃላፊዎች፣ የመከላከያ ሠራዊት መኮንኖች፣ በኢትዮጵያ የሚገኙ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች፣ ምሁራንና ሌሎች አካላት በመሳተፍ ላይ ናቸው።
የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ጃፋር በድሩ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የቀይ ባሕር አካባቢን የጂኦ-ፖለቲካ ሰላምና ደኅንነት ለማስጠበቅ የቀጣናው ሀገራት ትብብር ወሳኝ ሚና አለው።
ኢትዮጵያ የቀጣናውን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ፣ የጋራ ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ አኳያ ከቀጣናው ሀገራት ጋር በትብብር እየሰራች መሆኗን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የቀይ ባሕርን ደኅንነት ከማስጠበቅ አኳያ የባህር ላይ ዝርፊያዎችን ጨምሮ ሌሎች ሕገ-ወጥ ተግባራትን ለመከላከል የሚኖራት አስተዋጽኦ ትልቅ መሆኑን መጠቆማቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡