የቆዩ ጉዳዮችን እንደ አዲስ በማንሳት፣ በከተማዋ ሠላም እንደሌለ አድርገው በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ የተዛባ መረጃ የሚለቁ ሁሉ ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ የአዲስ አበባ ፖሊስ አሳስቧል፡፡
የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ “ተቋማዊ ሪፎርም ለተልዕኳዊ ስኬት” በሚል መሪ ሀሳብ በሪፎርምና ተቋማዊ ለውጥ አተገባበር ዙሪያ የተገኙ ስኬቶችን ለማስቀጠል እና አንዳንድ ከሪፎርሙ ትግበራ ጋር በተያያዘ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለማረም የሚያስችል ስራ ለመስራት የሚያግዝ በአስራ አንዱም ክፍለ ከተሞች ፖሊስ መምሪያዎች፣ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሌጅ፣ በቋሚና ተወርዋሪ ኃይል፣ በትራፊክ ቁጥጥር መምሪያ እንዲሁም በማዕከል የስራ ክፍሎች በልዩ ልዩ መድረኮች 6 ሺህ 036 አባላት የተሠጠው አራተኛው ዙር ግምገማዊ ስልጠና ተጠናቋል።
የስልጠናው ዓላማ ከህዝብ የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ እና የፖሊስ አገልግሎት ፈላጊውን ማህበረሰብ እርካታ ለመጨመር ያለመ ሲሆን በወንጀልና ትራፊክ አደጋ መከላከልና ምርመራ፣ በማህበረሰብ አቀፍ የፖሊስ አገልግሎት እና የፖሊስ ዶክትሪን ጋር በተያያዘ በቂ ግንዛቤን ለአባሉ ለማስጨበጥ እንዲሁም የስነ ምግባር ችግር ውስጥ የገቡትን ለማጥራት ያለመ እንደሆነ ተገልጿል።
በስልጠናው ማጠቃለያ የስራ መመሪያ የሰጡት የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ የለውጡ መንግስት ወደ ስልጣንና ኃላፊነት ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ ተቋማዊ ሪፎርምን መሠረት አድርጎ ወደ ተግባር መግባቱን ገልጸዋል፡፡
ተቋሙን በሰው ኃይልና በሎጀስቲክስ በማደራጀት፣ የፖሊስ አሠራርና አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ማነቆ የነበሩ ችግሮችን በማስወገድ የወንጀል መከላከል ስራን በቴክኖሎጂ በማስደገፍ ባከናወነው ተግባር በከተማዋ ሊፈጸሙ ታቅደው የነበሩ አስከፊ የሽብር ሴራዎችን ከመሰረታቸው ከማክሸፍ ጀምሮ በከተማው ላይ በርካታ ህዝብ የታደመባቸው ሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ስብሰባዎችና ሁነቶች በስኬትና በድል መወጣት ተችሏል ብለዋል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ሙያዊ ተልዕኮን መሰረት ያደረገ የወንጀል መከላከልና ምርመራ ስራዎችን በቴክኖሎጂ ጭምር በመታገዝ በማከናወኑ ከዚህ በፊት በከተማዋ ይፈፀሙ የነበሩ ወንጀሎች በከፍተኛ ሁኔታ መቀናሳቸውንም አመላክተዋል፡፡
ለዚህ ውጤት መገኘትም መላው የከተማዋ ነዋሪዎች ድርሻቸው የጎላ መሆኑን እና በከተማችዋ ያለው ጠንካራና አስተማማኝ ሠላም እንቅልፍ የነሳቸው አንዳንድ አካላት ወቅታዊነት የሌላቸውና የሀሰት ወሬዎችን በመፈብረክ፣ የቆዩ ጉዳዮችን እንደ አዲስ በማንሳት፣ በከተማዋ ሠላም እንደሌለ አድርገው በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ የተዛባ መረጃ የሚለቁ ሁሉ ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡም ማሳሰባቸውን ከአዲስ አበባ ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡