“የባህር በር ባለቤት ከሆንክ ዓለምን ታገለግላለህ፤ ባህር በርና ወደብ አልባ ከሆንክ ግን ለጎረቤቶችህ እንኳን የምትሰጠው ጥቅም እንዳለ እርግጠኛ መሆን አይቻልም።” ይህንን ያሉት በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት ምሁሩ ፖል ኮሊየር ናቸው፡፡
‹The Bottom Billion› መጽሐፍ ደራሲው በዚሁ መጽሐፋቸው ላይ በተለይ ድህነት ባጠላበት ቀጠና እየኖሩ ወደብ አልባ መሆን ሀገር ስኬታማ የልማት ጉዙ እንዳይኖራት ወደ ኋላ ከሚመልሱ የልማት “ወጥመዶች” መካከል ዋነኛ ስለመሆኑም ያስረዳሉ። “የባህር በር ባለቤት ከሆንክ ዓለምን ታገለግላለህ” የሚለው ሀሳብ ምን ማለት እንደሆነ ሲያብራሩም የባህር መዳረሻ ለዓለም አቀፍ ትስስር እና ንግድ ወሳኝ መሆኑን ለማሳየት ስለመሆኑ ይገልጻሉ፡፡
ወደብ ለሌላቸው ሀገሮች ከሌላው ዓለም ጋር በሚያደርጉት የንግድ እንቅስቃሴ ላይ የተገደበ በመሆኑ ተፅዕኖው ጠንካራ ነው። የባህር በር የሌላቸው በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት በባህር ዳርቻ ከሚገኙ አቻ ሀገራት ጋር ሲነፃፀሩ ለዓለም አቀፍ የሸቀጥ ትራንስፖርት ከፍተኛ ወጪ አለባቸው። ከባህር የራቁ ሀገራት ታሪክም የሚያሳየው ይህንኑ ነው። በአጠቃላይ የባህር መዳረሻ ማጣት ለአንድ ሀገር በፖለቲካ፣ በወታደራዊ እና በኢኮኖሚ ትልቅ ኪሳራ ስለመሆኑም ፖል ኮሊየር ያስረዳሉ።
ሰፊው ክፍሏ በባሕሮች እና በውቅያኖሶች በተሸፈነው ዓለም ላይ ከሚገኙት ወደ ሁለት መቶ ከሚጠጉ ሉዓላዊ ሀገራት መካከል 44ቱ የባሕር በር የላቸውም ይላል የዓለም አቀፉ የንግድ ድርጅት ይፋ ያደረገው መረጃ። ከእነዚህ ውስጥ 31 ያህሉ ደግሞ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ናቸው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ካዛኪስታን በቆዳ ስፋቷ ትልቅ ሆና ወደብ የሌላት ሀገር ስትሆን ኢትዮጵያ ደግሞ ትልቅ የሕዝብ ብዛት እና ሠፊ ግዛት ይዛ የባሕር በር ከሌላቸው የዓለም ሀገራት ዋነኛዋ ናት።
ወሳኙ ጥያቄ ታዲያ ዓለም እነዚህን ወደብ አልባ ሀገራት በምን መልኩ ልታስተናግዳቸው አሰራር ዘረጋች የሚለው ይሆናል፡፡ ወደ 169 የዓለም ሀገሮች የፈረሙበትና እ.ኤ.አ. በ1982 የወጣው ዓለም አቀፍ የባህር ሕግ (United Nations Convention on the Law of the Sea/UNCLOS)፣ የዓለም ሀገሮች የባህር ክልልና ወሰንን በምን መንገድ መጠቀም እንደሚገባቸው መሠረታዊ መርሆዎችን አስቀምጧል፡፡ እ.ኤ.አ. በ1994 ወደ ሥራ የገባው ሕጉ የጠረፍንና የዓለም አቀፍ ውኃ ክልልን ምንነትና አጠቃቀም፣ እንዲሁም በባህር ወሰኖች የሚነሱ ውዝግቦችና የችግር አፈታት ሒደቶችን በዝርዝር አስፍሯል፡፡
የአንድ ሀገር የውኃ ክልል ከባህር ጠረፍ እስከ 22 ኪሎ ሜትር ድረስ ያለውን የውኃ አካል ያጠቃልላል ይላል ይህ ሕግ፡፡ በዚህ የአንድ ሉዓላዊ የሀገሮች የባህር ክልል ላይ የትኛውም ሀገር ለሰላማዊ ጉዳይ እስከሆነ መተላለፊያ ሊከለከል እንደማይችል ተመልክቷል። ከአንድ ሀገር የየብስ ወይም የባህር ጠረፍ ተነስቶ እስከ 370 ኪሎ ሜትር በሚረዝመው የባህር አካል ላይ ደግሞ፣ አንድ የባህር በር ያለው ሀገር የራሱን የኢኮኖሚ ዞን (exclusive economic zone-EEZ) መመሥረት እንደሚችል ተገልጿል፡፡
የባህር በር ያላቸው ሀገሮች መብትና ዓለም አቀፍ ግዴታን በግልጽ የሚያስቀምጠው ይህ ሕግ በተለይ ከአንቀጽ 24 እስከ 26 ባለው ክፍል የባህር በር ባለቤት ነኝ በሚል ብቻ ሀገሮች እንዳሻቸው የመሆንና የማድረግ መብት እንደሌላቸው በቀጥታ ያብራራል፡፡ የባህር ወሰናቸውን ለሰላማዊ እንቅስቃሴ እስከሆነ ድረስ ለሌሎች ሀገሮች ዝግ ማድረግ በፍጹም እንደሚከለከሉ ያትታል፡፡ የባህር ክልላቸው ለባህር እንቅስቃሴ ሰላማዊና ምቹ ስለመሆኑ ለመላው ዓለም መረጃ የመስጠት ግዴታ አለባቸውም ይላል፡፡
በሌላ በኩል በባህር ድንበራቸው ላይ ነዳጅ መሙላትን ጨምሮ የወደብና የትራንዚት አገልግሎት ለሚፈልግ መርከብ ያለ ልዩነትና ያለ አድልኦ ባወጡት ተመን ምክንያታዊ ክፍያ በመሰብሰብ አገልግሎት መስጠት እንደሚችሉ ይፈቅዳል፡፡ በአጠቃላይ ሀገሮች የባህር በር አለን በሚል ብቻ በሌሎች ሀገሮች ላይ ጫና እንዳያሳድሩ ሕጉ ልጓም አበጅቷል፡፡ ይህ ድንጋጌ እንደ ቀይ ባህር ስላሉ ጠባብ የባህር መተላለፊያዎች፣ የሀገሮች ትብብርና የውኃ አጠቃቀም የሚመለከት ነው፡፡ በጥቅሉም የባህር በር የሌላቸው ሀገሮች መብቶች፣ እንዲሁም የባህር በር ካላቸው ሀገሮች ጋር የሚኖራቸው ግንኙነቶች በዝርዝር ሰፍሮ ይገኛል፡፡
እ.ኤ.አ. በ1963 በተቋቋመው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (OAU) ወይም በአፍሪካ ህብረት (AU) ቻርተር መግቢያ ላይ በግልፅ እንደሰፈረው የአፍሪካ ሀገራት የባህር በር የሌላቸውን ጨምሮ የባህር ላይ ተጠቃሚ የመሆን መብት እንዲኖራቸው በተለይ የባህር በር የሌላቸው ሀገራት በባህር ላይ የመጠቀም መብታቸው እንዲጠበቅ እውቅና ይሰጣል፡፡
እነዚህን የዓለም አቀፍ ህግጋት መሰረት በማድረግና በተጨማሪ አንዳንድ ሀገራት በስትራቴጂክ ወዳጅነት እና በዲፕሎማሲያዊ ጥረት ችግሮቻቸውን ማቃለል ችለዋል፡፡ በዓለም ላይ ያሉ በርካታ ሀገራት ወደብ ከሌላቸው መንግስታት ጋር ድንበር ይጋራሉ። የንግድ ስምምነቶች፣ የፖለቲካ ድርድርና ውይይት አማራጮችንም ተጠቅመው ለችግሮቻቸው እልባት ሰጥተዋል፡፡ የተወሰኑትን በማሳያነት እናቅርብ፡፡
መነሻችንን ከአንደኛው የዓለም ጦርነት በኋላ እናድርግ፡፡ የቬርሳይ ስምምነትን የአውሮፓ ሀገሮች ሲፈራረሙ ፖላንድ ወደብ አልባ ነበረች፡፡ እናም ከጀርመን መተላለፊያ (ኮሪዶር) ተሰጥቷት ወደብ እንድታገኝ ተደረገ፡፡ በቬርሳይ ውል፣ “የፖላንድ ኮሪደር” ተብሎ የተሰየመው የጀርመን ክፍል ለሁለተኛው የፖላንድ ሪፐብሊክ ወደ ባልቲክ ባህር ለመግባት የቻለችውም በዚሁ ስምምነት ነበር፡፡
እ.ኤ.አ. በ 2005 ከዩክሬን ጋር በተደረገው የመሬት ልውውጥ ምክንያት ሞልዶቫ 600 ሜትር (650 ያርድ) ርዝመት ያለው በዳኑቤ መዳረሻ ተቀብላለች። ዳኑቤ ዓለም አቀፍ የውሃ መንገድ ሲሆን ስለዚህም ወደብ አልባዎቹ ኦስትሪያ፣ ሃንጋሪ፣ ሞልዶቫ፣ ሰርቢያ እና ስሎቫኪያ ወደ ጥቁር ባህር አስተማማኝ መዳረሻ አላቸው።
ለአብነትም በመካከለኛው አውሮፓ የምትገኘው ጀርመን ኦስትሪያን፣ ስዊዘርላንድን እና ሉክሰምበርግን ጨምሮ ከበርካታ ወደብ ከሌላቸው ሀገራት ጋር ድንበር ትጋራለች። ምንም እንኳን ጀርመን የራሷ የሰሜን ባህር እና የባልቲክ ባህር መዳረሻ ቢኖራትም ወደብ የሌላቸው ጎረቤቶቿ ዓለም አቀፍ የንግድ መስመሮችን ለማግኘት በወደቦቿ እና በመሠረተ ልማት አውታሮች እንዲጠቀሙ ታደርጋለች።
የአውሮፓ ህብረት እ.ኤ.አ 2020 ይፋ ያደረገው መረጃ መሰረት ስዊዘርላንድ ምንም እንኳን ወደብ አልባ ብትሆንም በጀርመን ወደቦች እንደ ሃምበርግ እና ብሬመን የመሳሰሉትን ወደቦች ለዕቃ ማጓጓዣ ትጠቀምባቸዋለች። በተመሳሳይ፣ ኦስትሪያ የጀርመን ወደቦችን ለዓለም አቀፍ ንግዷ በተለይም በራይን-ዳኑብ ኮሪደር በኩል ለመጓጓዣ ቁልፍ የሆነውን የውሃ መንገድ ትጠቀማለች። በመሆኑም ጀርመን እና ወደብ አልባ ጎረቤቶቿ በአውሮፓ ህብረት እና በአውሮፓ ኢኮኖሚ ማዕቀፍ ውስጥ በሚደረጉ ስምምነቶች ውስጥ በመሳተፍ ወደብን በጋራ ይጠቀማሉ፡፡
የንግድ ስምምነቶችንም እንደ አማራጭ በመጠቀም በጎረቤት ሀገራት በነፃ የትራንስፖርት አገልግሎት ለማቅረብ ሀገራት ስምምነቶችን ይፈጽማሉ፡፡ የቬርሳይ ስምምነት ጀርመን ቼኮዝሎቫኪያን በሃምቡርግ እና ስቴቲን የሚገኙትን የወደብ ክፍሎች ለ99 ዓመታት የሊዝ ውል እንድታቀርብ ያስገድድ ነበር፣ ይህም በኤልቤ እና ኦደር ወንዞች በኩል የቼኮዝሎቫኪያ የባህር ንግድ እንዲኖር አስችሏል።
በፖለቲካ ድርድርና ውይይት አማራጭን ስንመለከት ደግሞ በደቡብ እስያ የምትገኘውን አነስተኛዋን ወደብ አልባ ከተማ ቡታንን እናገኛለን፡፡ በሶስት ጎን ከህንድ እና በሰሜን ከቻይና ጋር ድንበር ትጋራለች። ነገር ግን ደግሞ በሀገራቱ መካከል በተደረገ ውይይትና ድርድር መነሻነት የባህር ድንበር በመጋራት አገራቱ የንግድ፣ ቱሪዝም እና የባህር ውስጥ ሃብትን በጋራ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እንዳስቻላቸው የቢቢሲ ዘገባ ያትታል፡፡
አፍሪካ ውስጥም ለምሳሌ ኮንጎ ኪንሻሳና ኮንጎ ብራዛቪልን ማንሳት ይቻላል፡፡ ኮንጎ ኪንሻሳ የቤልጂየም ግዛት ነበር፡፡ ብራዛቪል ደግሞ የፈረንሣዮች ነበር፡፡ ኮንጎ ብራዛቪል ወደብ አልነበረውም፡፡ ሁለቱም ተስማምተው ከኮንጎ ኪንሻሳ የተወሰነ መሬት ወስደው ኮንጎ ብራዛቪል ወደ ባህር እንድትዘልቅ ተደረገ፡፡
በአጠቃላይ ከላይ የዓለም አቀፍ ህግጋትና ተግባራዊ ማሳያዎች እንደሚያሳዩት የባህር በር ያለው ሀገር የባህር በር የሌለውን ሀገር የባህር ንግድ እንቅስቃሴ ማወክ እንደማይችል ማረጋገጫ የሚሰጥ ነው፡፡ የወደብና ትራንዚት አገልግሎት ላይ ሆን ብሎ መጓተት መፍጠር፣ ያልተመጣጠነ ክፍያ መጠየቅ እንደዚሁም ሆነ ከስምምነት ውጪ የሆኑ ነገሮችን ካላስፈጸምኩ ማለት የተከለከለ መሆኑንም ያመለክታል፡፡ ሕጉ የባህር በር ያላቸው ሀገሮች የባህር በር የሌላቸው ሀገሮችን ህልውናና ብሔራዊ ጥቅም አደጋ ላይ የሚጥል እንቅስቃሴ ከማድረግ መቆጠብ እንዳለባቸውም ያስታውቃል።
በሳህሉ ብርሃኑ